
ሰቆጣ፡ ጥቅምት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የወያኔ ቡድን ሰቆጣ ከተማን ለመያዝ ከነበረው ፍላጎት የተነሳ ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል። የወገን ጦር ባደረገው ተጋድሎ ከሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ከእክመጽርዋ ቀበሌ አልተሻገረም። ግፍ የማይሰለቸው ቡድን ግን በእክመጽርዋ ወረዳ በቆየባቸው ሁለት ቀናት ወጣቶችን አሰቃይቷል ፣ንብረት ዘርፏል ፣አውድሟል፣ ሴቶችን ደፍሯል።
ከተደፈሩ ሴቶች መካከል ወይዘሮ አልማዝ አለሙ አንዷ ናቸው። ወይዘሮ አልማዝ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ እክመጽርዋ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ከአስ ከተማ ወደ እክመጽርዋ ቀበሌ ያቀኑትም ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ሠርተው የተሻለ ሕይወት ለመኖር ነበር። ምግብ በመሸጥም ኑሮአቸውን ይመራሉ። ወይዘሮዋ ለአላፊ መንገደኛ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምግብ እና መጠጥ በመሸጥ በሚያገኙት ገቢ ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድራሉ።
አሸባሪው የወያኔ ቡድን እክመጽርዋ ቀበሌን ሲወር ወይዘሮ አልማዝ ለገበያ ያዘጋጁትን ምግብ እና መጠጥ የሽብር ቡድኑ አባላት ቀምተው ተመገቡት። በዚህም አልበቃውም ለገበያ ያስቀመጡትን 50 ካሳ ቢራ የቻለውን ጠጥቶ ያልቻለውን ጭኖ ወሰደ። በጠጣው ቢራ ናላው የዞረው የሽብር ቡድን የቤታቸውን በር ሰብሮ ገባ። ምርጫ አቀረበላቸው። “መኖር ወይስ መሞት ነው የምትፈልጊ። የያዝኩት መሳሪያ እሳት ይተፋል ምረጭ አላቸው” እናትህ አይደለሁም አላበላውህም፣ አላጠጣውህም” ብለው ተማጸኑት፣ ለመኑት መመለስ አልፈለገም። ጫፍ የረገጠ ጽንፈኝነቱ እንዲራራ አልፈቀደለትም። ሴትዮዋን አስገድዶ ደፈራቸው።
ግፈኛው አሸባሪ ኀይል በዚህ አልበቃውም “የወገን ጦር አንቺ ቤት ይመገብ ነበር በሚል ሠበብ መሳሪያ ደብቀሻል፣ ብር እና ወርቅ አምጪ በማለት ቁምስቅላቸውን አሳያቸው። ቤቱን በሙሉ አሰሰው ምንም ማግኘት ባለመቻላቸው መሳቢያ ላይ የተቀመጠች 10 ብር እና የምግብ ቁሳቁስ ይዘው ሄዱ” ሲሉ ነበር የደረሰባቸውን በደል ያስረዱት።
ቡድኑ ያደረሰባቸውን ግፍ ህሌናቸው መቀበል ባይችልም ተሰብረው እና አንገታቸውን ደፍተው ላለመቅረት ጥረት እያደረጉ ነው። ካልሠሩ መኖር አይቻልም እና ወደ ሥራ ተመልሻለሁ ብለዋል። የሽብር ቡድኑን መመከት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሌሎች የእሳቸው እጣ ፋንታ የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ አልማዝ ሕክምና እንዲከታተሉ እና ራሳቸውን ከአላስፈላጊ ቁዘማ እንዲያወጡ መክረዋል። በደረሰብን መከራ መሠበር ሳይኾን ፣እነሱን ለመመከት መተባበርና በጋራ መቆም ያስፈልጋል ብለዋል ወይዘሮ አልማዝ።
ሌላው ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የእክመጽርዋ ቀበሌ ነዋሪው ጌታው ነይሽ መስማት የተሳናትን እህታቸውን ወይዘሮ ዘይቱ ነይሽን አስገድዶ እንደደፈረባቸው ተናግረዋል። አቶ ጌታሁን የሽብር ቡድኑን ግፍ ሲገልጹ መብላቱ መጠጣቱ አይደለም ጉዳት ያደረሰው አጸያፊ ድርጊት በመፈጸም የሥነልቦና ጉዳት ማድረሱ፣ የማይበላውን እያረደ በየቦታው መጣሉ፣ ከሰው ትከሻ ላይ ልብስ መግፈፉ፣ ባደረበት ፍራሽ ላይ መጸዳዳቱ ከሰውነት ደረጃ የወረደ አካል መኾኑን እንድንረዳው አድርጎናል ነው ያሉት።
አቶ ጌታው የእሳቸውን ሰባት ፍየሎች፣ የትንሽ እህታቸውን የወይዘሮ እመይቴ ነይሽን 13 ፍየሎች ጨምሮ ከ84 በላይ ፍየሎችን አርዶ እንደበላ እና ቀሪውን ለአሞራ ሲሳይ እንዳደረገውም ተናግረዋል። አቶ ጌታው አሸባሪው ወያኔ እውነተኛ ጠላትነቱን አሳይቶናል፣ በጋራ እንመክተዋለን ብለዋል። በሩቅ የሰማነውን በአይናችን አየነው የሽብር ቡድኑ ለእናቱም የሚመለስ አይደለም፣ ይኽን ቡድን መመከት ይገባል፡፡ ለዚኽ ደግሞ የእኛ አንድነት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል ብለዋል።
አቶ ጌታው የወገን ጦርን በመቀላቀላቸው የሽብር ቡድኑ በቤተሰባቸው ላይ ያደረሰው ግፍ ሕሊና የማይረሳው ቢኾንም መጠኑ ይነስ እንጅ በኹሉም ቤት የደረሰ በመኾኑ ኹሉም በጋራ እንዲነሳ እና ጠላቱን እንዲፋለም ጥሪ አቅርበዋል። የወያኔ የሽብር ቡድን ግፍ ተቀባዮች በጋራ ቆመናል ጠላታችንን መመከት ቀዳሚ ሥራችን ይኾናል ብለዋል። አቶ ጌታው የሽብር ቡድኑ መዝረፉ ፣መድፈሩና ሕዝብን ማዋረዱ አንሶት ወጣቶችን አስከሬን አሸክሞ እንደወሰዳቸውም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር