
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወርሃ ጥቅምት ሲገባ ቀዳሚው ሰኞ ቀን ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንዲከበር በሕግ ተደንግጓል።
ቀኑ የሚከበረውም በተሻሻለው በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 መሠረት በየዓመቱ የጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሰኞ ቀን ኾኖ በታላቅ ክብር ተከብሮ ይውላል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ታሪክ እና ልዕልና የተሸከመ የቀደሙትም፣ የአሁኑም ትውልድ ልዩ መለያ ነው፡፡ በመኾኑም ኢትዮጵያዊ ከጥንት እስከ ዛሬ በስኬትም፣ በጭንቅ ጊዜም የነደደ የሀገር ፍቅሩን የሚገልጸው የሀገሩን አርማ አጥብቆ በመጨበጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ በሀገሩ አርማ ይማማላል፣ በሀገሩ አርማ ቃል ይገባል፣ በሀገሩ አርማ በአንድነት ለድል ይዋደቃል፣ በሀገሩ አርማ ለስኬት ይፋለማል፣ በድሉ ስለድሉ፣ ስለ መስዋእትነቱ ይመሰክራል፣ በደስታም በሐዘኑም በአርማው ያነባል፣ በአርማው ይፈነድቃል፡፡
ኩራቱ ከአርማው እኩል ነው። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ መልክ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ማለት የሀገር መታወቂያ፣ የሉዓላዊነት፣ የሕዝብ አንድነት መጠበቂያ፣ የክብር መለያ ምልክት ነውና፡፡
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በየዘመኑ ለኢትዮጵያ ልዕልና፣ ለክብሯ፣ ለሉዓላዊነቷ፣ ለነጻነቷ ተዋድቀዋል። እናም የኢትዮጵያ መልክ የኾነውን አርማ በደማቸው ቀለም ስለው በሀገር ፍቅር በልባቸው አትመው ለትውልድ አሻግረዋል።
“…ሀገሬ አርማ ነው የነጻነት ዋንጫ፣
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ቢጫ፣
እሾህ ነው ሀገሬ …
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ፣
ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ፣•••”
እንዲል ታላቁ የጥበብ ሰው ገብረክርስቶስ ደስታ ኢትዮጵያ በታሪኳ የነጻነት ምልክት ናት።
ኢትዮጵያ የአልደፈር ባይነት ምሳሌ ናት፣ ኢትዮጵያ የነጻነት አርማ ኾና በአርዓያነት ትጠቀሳለች። ይህን ደግሞ በየአውዱ ከፍ ብሎ ከነግርማው የሚውለበለበው ሰንደቅ ዓላማዋ ይናገራል። ለሰንደቃቸው በክብር በተዋደቁ ጀግኖች ልዕልናዋ ከፍ ብሎ የተቀመጠው፣ ታሪኳን ዘመን የማያደበዝዘው በደምና በአጥንት የታተመ አርማ ባለቤት ሀገር ስለኾነች ነው።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን “አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን በልባችን የታተመ የኢትዮጵያዊነታችን መልክ ነው” ይሉታል።
ልጅ ዳንኤል ጆቴ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ “የማንነታችን መለያ፣ የታሪካችን ድርሳን፣ የሥነ-ልቦናችን ልዕልና ሁሉ ምልክት ነው”
በእርግጥ ይላሉ ልጅ ዳንኤል ጆቴ “ይህ ምልክት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለበርካታ አፍሪካውያን ሁሉ የነጻነት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።
ሰንደቅ ዓላማው በጀግኖች ኢትዮጵያውያን መስዋእትነት ተከብሮ የኖረ ነውና የአፍሪካ የነጻነት አርማም ለመኾን በቅቷል ይላሉ።
ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከነጻነታቸው በኋላ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማትን በተለያየ ቅደም ተከተል እና አቀማመጥ የመጠቀማቸውን ምክንያት በምሳሌነት በመጥቀስ፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያውያንን ታሪክ፣ ሥነ-ልቦና እና ማንነት የያዘ ምልክት እንደኾነ በልኩ መረዳት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ታላቅ ክብር ለሰንደቅ ዓላማችን ስንል ክብር ለኢትዮጵያችን፣ ክብር ለጀግኖቻችን ማለታችንም ነው የሚሉት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በደምና በአጥንት በክብር ላቆሟት፣ ጥንትም፣ ትናንትም፣ ዛሬም የኢትዮጵያ ክብርና ነጻነት አናስነካም፣ አናስደፍርም ከሀገራችን በፊት እኛ ብለው በየግንባሩ ለሚፋለሙ ሀገራቸውን በክብር በጀግንነት ላስቀደሙ ጀግኖች ማለታችን እንደኾነም ይሰመርበት ባይ ናቸው።
እርግጥ ነው ክብር ለሰንደቅ ዓላማችን ስንል የጠላትን ቅስም ሰብረው ጠላትን ያሳፈሩ፣ ለኢትዮጵያ ነጻነት፣ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ለኢትዮጵያ ክብር በክብር ለተዋደቁ ቀደምቶች፣ በየዘመኑም ጀግንነትን የወረሱ፣ ጀግንነት የማይነጥፍባቸው ጀግና ኢትዮጵያውያን ሞተው ለሚያስከበሩን፣ ሞተው ላኖሩን ሁሉ ክብር ይሁን ማለታችን ነው፡፡
ድምጻዊ ጸጋዬ እሸቱ ስለ ሰንደቅ ዓላማ ባቀነቀነው ሙዚቃው፣
“…ህይወቱን ሸልሞ በደሙ ላኖረሽ
ሰንደቅ ዓላማችን ኑሪ እየመሰከርሽ
… ኑሪ እየተናገርሽ….
ሰንደቅ ናት ሃይማኖት፣ ዓላማ ናት እምነት
አርማ የለሽ ዜጋ የለውም ነጻነት…” ይለናል።
ልጅ ዳንኤል ጆቴ ይናገራሉ ታሪካችን፣ ማንነታችን፣ የሥነ-ልቦና ልዕልናችን አርማ የኾነው የኢትዮጵያ አርማ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብርና ሥነ-ሥርዓት ጠብቆ መከበር አለበት።
በአዘቦቱም ቀን ቢኾን ሲመሽ ሲነጋ በትምህርት ቤቶች፣ በትላልቅ መሥሪያ ቤቶች፣ በመከላከያ፣ በፖሊስ ተቋማት ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀልና ሲወርድ የሚገባውን ክብር እና ሥነ-ሥርዓት በተከተለ የመኾኑ ጉዳይ ሊሸረሸር አይገባውም ይላሉ።
ኢትዮጵያ’ን ሀገሬ ያለ ሰው፣ ኢትዮጵያን እወዳለሁ ያለ ዜጋ ሁሉ፣ ለሀገሩ ምልክት ዓርማ፣ ለሀገሩ መለያ ሰንደቅ ክብር መስጠት ይገባል ባይ ናቸው። እናም ይላሉ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ታሪክ ማንነት፣ ባሕል እና ሙሉውን ኢትዮጵያዊነት የያዘውን ሰንደቅ ዓላማ ክብሩን እያወቁ፣ እያከበሩና እየጠበቁ ለቀጣዩም ትውልድ ማሻገር የትውልዱ ኃላፊነት መኾኑንም በውል መገንዘብ ይገባል።
በክብር ለተረከብነው ባለ ግርማ አርማ፣ ከነሙሉ ነጻነቷ ለተቀበልናት ሉዓላዊት ሀገር ኢትዮጵያ፣ የተከፈለላትን ዋጋ ጠብቀን፣ አክብረን እና የሚገባንን፣ የሚመጥነንን ኢትዮጵያዊነት አጥብቀን ልንይዝ ይገባል።
“…አናሳፍርሽም ታሪክ ይወቅሰናል
ዜጎችሽ ዋርድያ ዘብ ኾነን ቆመናል..” ይላልና ድምጻዊ ጸጋዬ እሸቱ ኢትዮጵያ የማታፍርብን ዜጎች በሚያደርገን አውድ ላይ እንገኝ።
“…አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን አርማ ሰንደቅ
በክብር ለብሸው ለክብሯ ልዋደቅ…” ሲል ድምጻዊ ዳኘ ዋለ እንዳዜመላት ለክብሯ የምንዋደቅ እንሁን፣ የአያት ቅድመ አያት የጀግንነት ወራሽነታችን ሊሸረሸር አይገባውም።
ዘጋቢ፡- ጋሻው አደመ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J