
አዲስ አበባ: ጥቅምት 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአፋርኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራምን ዛሬ ጀምሯል፡፡የፕሮግራሙ መጀመርም የሁለቱን ክልሎች ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር እንደሆነ ነው የተገለጸው። በመርሃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ተጠሪነቱ ለአማራ ክልል ምክር ቤት ባለቤትነቱ ደግሞ የአማራ ህዝብ ቢሆንም ተደራሽነቱን በማስፋት አገልግሎቱን በብዝሃ ቋንቋዎች እያደረሰ ይገኛል ብለዋል።
“በሥራችንም የኢትዮጵያዊያንን አንድነት እያጠናከርን እንገኛለን፣ በተጀመረዉ ፕሮግራም የሁለቱን ክልል ሕዝቦች የነበረ ግንኙነት እናጠናክራለን፣ የአፋርን ታሪክ፣ ባህል እና እሴት እናስተዋውቃለን” ነው ያሉት።
ሁለቱ ክልሎች በብዙ ጉዳዮች አብረው እሰሩ ነው ያሉት አቶ ሙሉቀን አሚኮ ደግሞ የሁለቱን ክልሎች ትሥሥር የበለጠ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡ ይህ መልካም ጅምር ነዉ፤ ወደፊት እያደገ ይሄዳል ብለዋል። የሁለቱ ክልሎች በሁሉም ጉዳዮች አብረው እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ሚዲያው ትስስሩን የበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል፤ የአፋርኛ ቋንቋ ጋዜጠኞችም የአማራንና የአፋርን ህዝብን ግንኙነት የማጠናከር ኀላፊነት እንዳለባቸዉ ገልጸዋል።
በፌዴራልም ሆነ በክልል ያሉ የሥራ ኀለፊዎች ግባት የሚሆን መረጃዎችን በማካፈል ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሚኮ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ አቅሙን እና ተደራሽነቱን እያሳደገ ለአድማጭ ተመልካቹ ወቅታዊና ታማኒ መረጃዎችን በማድረስ ህዝባዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
የአድማጭ ተመልካቾቹን ፍላጎት ግምት ዉስጥ በማስገባት በብዝሃ ቋንቋዎች አስተማሪ፣ አዝናኝ እና መረጃ ሰጭ ዘገባዎችን በማድረስ እየተጋ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡
በመረሃ ግብሩ በእንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ባርኦ ሃሰን ባርኦ የአማራና የአፋር ህዝብ መስተጋብር ሁሉን ዓቀፍ ነዉ ብለዋል። የአማራ ህዝብ ዓቃፊ መሆኑን እናቃለን፣ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ደግሞ አፋርኛ ቋንቋን በማሥጀመር አረጋግጧል፣ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የብዙሃኑ ህዝብ አይንና ጀሮ ሆኖ የቆዬ የህዝብ ሚዲያ ነው ብለዋል።
ዛሬ የአፋርኛ ፕሮግራም መጀመሩ ለአፋር ህዝብ ትልቅ ትርጉም አለዉ፤ የሁሉቱን ክልሎች ትስስር በማጠናከር ሚናዉ የጎላ እንደሚሆን እምነቴ የጸና ነዉ ብለዋል፡፡ ሥለተደረገው ሁነትም እናመሰግናለን ነው ያሉት። የአማራና የአፋር ህዝቦች እንኳን ደስ ያላችሁም ብለዋል፡፡ አፋር ክልል ሊሠራበት የሚችል ያልተነካ ሃብት አለ፣ ጋዜጠኞች የአማራ ባለሃብቶች ወደ አፋር ክልል ሂደው የማልማት ዝንባሌ እንዲኖራቸው የማድረግ ኃላፊነት አለባችሁ ነው የሉት፡፡ ጋዜጠኞች ድልድይ ሆነው የሁለቱን ህዝቦች ትስስር የማጠናከር ኀላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የአፋርን ህዝብ ወክላችሁ ክልሉን በደንብ የማሥተዋወቅ ግዴታ አለባቸው፣ የመንግስት የሥራ ኀላፊዎች ደግሞ የበኩላችንን እናደርጋለን ብለዋል። ባህል፣ ቋንቋ እና ማኅበራዊ መሥተጋብር ላይ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።
“የሁለቱ ህዝቦች ታሪካዊ፣ ሰላማዊና የጠነከረ ነው። ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ለዚህም አሚኮ ታላቅ ኃላፊነት ወስዷል፣ የሚደነቅ ነው” ብለዋል።
የተደረገዉ ሁነት ታሪካዊ እና የአመራር ቁርጠኝነት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል። የሁለቱ ክልል ሕዝቦች ግንኙነት ድንበር ከመጋራት በላይ ነው፣ ትስስራቸው የደም ነው። ብዙ ጥሩና አሰቸጋሪ ሁነቶችን በጋራ አሳልፈዋል። የአፋርኛ ቋንቋ በአሚኮ መጀመር ደግሞ የነበረውን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል ነው ያሉት። ሊበረታታ የሚገባው ታሪካዊ ሥራ እንደሆነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:–በለጠ ታረቀኝ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!