
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር ሲሰረቅባት በኖረች ሀገር ፈተና መስረቅ ምናልባትም አስደንጋጭ ክስተት ላይኾን ይችላል፡፡ የፈተና ስርቆት ልምምድ ግን ያለ እጅ መንሻ ለሕዝብ አገልግሎት መስጠት ነውር የሚመስለው ትውልድ ለመፍጠር መነሻ መኾኑ አይካድም፡፡ ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ሀገርን ለማፍረስ እና ትውልድን ለማዝቀጥ የትምህርት ሥርዓቱን ማቆሸሽ ኾነኛ ስልት ተደርጎ በግልጽ እና በህቡዕ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡
በራሱ የሚተማመን እና በእሳቤ የሚዘምን ትውልድ ከስሞ ሀገርን በፈለጉት መንገድ መዘወር እንዲችሉ የትምህርት ሥርዓቱን የፖለቲካ ካድሬዎች ምቹጌ አደረጉት፡፡ “ድግሪን ማልከስከስ እና ዶክትሬትን ማርከስ” ለሚል መርሃቸው መሳካት በኮታ የትምህርት ማስረጃ የታደለባት ሀገር ዛሬ የመጻዒው ትውልድ ብሔራዊ ፈተና አደጋ ውስጥ ባይገባባት ነበር የሚገርመው፡፡

በተራዘመ ተፅዕኖ ስር ያለፈው የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት መልኩም ግብሩም ተቀይሮ የችግር መፈልፈያ ማዕከል እስከ መኾን ደርሶ ነበር፡፡ ግርሃም ሃንኩክ “የድህነት ከበርቴዎች” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው በድህነት ስም የበለጸጉ ከበርቴዎች አሉ እንዳሉት ሁሉ እንደ ድጎማ በታደለ የትምህርት ማስረጃ መሃይምነታቸው ትውልድ ያመከነ የሥርዓቱ ጀሌዎች ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ አሉ፡፡
በትምህርት ሥርዓቱ እና በትምህርት ቤት አካባቢ የሚስተዋለው ግዴለሽነት፣ ጥቅመኝነት እና ስርቆት እንደ ነውር መታየቱ ቀርቶ ጤነኛ አስተሳሰብ ተደርጎ የተወሰደበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም፡፡ ብርሃኑ ደቦጭ “የድንቁርና ጌቶች፤ ሞገሱን የገፈፉት ዩኒቨርሲቲ” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው የትምህርት ሥርዓቱን ያቆሸሹት የየሥርዓቱ ሎሌዎች ሁሉ በግል ቢሊየነር ቢኾኑም ሀገር ግን የጥቅመኞች መብቀያ ኾናለች ይላሉ፡፡
በብሂላቸው “የተማረ ይግደለኝ” የሚሉት ኢትዮጵያዊያን በትምህርት ላይ የነበራቸውን ጽኑ እና ጠንካራ እምነት አመላካች ነበር፡፡ ያ ጠንካራ እምነት ተሸርሽሮ ትምህርት በየገበያ ማዕከሉ የሚቸበቸብ ሸቀጥ እስኪመስላቸው ድረስ በሂደቱ የተሰላቹበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በአህያ ተጭኖ በእምነት ተሸፍኖ ገጠር ድረስ የሚደርሰው የቀድሞው የፈተና ወረቀት ዛሬ ላይ በየቦታው ተሰርቆ እየወጣ በአደባባይ እንደ አንድ የፖለቲካ መታገያ መስመር በጀብደኝነት ሲገለጥ አይተናል፡፡ በክስተቱ ተገርመውም “አጃአይብ” ድንቁርና ያሉት ኢትዮጵያዊያን በርካቶች ነበሩ፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ ጉድለት እና ክፍተት የትየለሌ ቢኾንም ስለችግሩ አብዝቶ መነጋገር ብቻ በራሱ መፍትሄ አይኾንም፡፡ መፍትሄው በችግሩ መኖር ተማምኖ በአማራጭ ሃሳቦቹ ላይ ማተኮር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣውን የብሔራዊ ፈተና ውዝግብ ለመቀነስ የትምህርት ሚኒስቴር አማራጭ ያለውን የፈተና ሥርዓት እየተገበረ ነው፡፡ የፈተና ቅድመ ዝግጅት ሂደቱ ትምህርት ሚኒስቴር እና አጋሮቹ ቁርጠኛ መፍትሄ ለመውሰድ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያመላከተ መኾኑንም የዘርፉ ሰዎች ሲናገሩ እያዳመጥን ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን በትምህርት ሥርዓት ላይ ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር የተሠራው ሴራ ዓመታትን ፈጅቷል፡፡ በትምህርት ላይ ያላቸውን የቀደመ እምነት ለመመለስ ደግሞ የበለጠ ጊዜ መውሰዱ አይካድም፡፡ ዋናው ነገር መፍትሄ የተባለው ሂደት ዛሬ መጀመሩ ነው፡፡ በሂደቱ ዋጋ የሚከፍል ትውልድ መኖሩ ባይካድም ከነብልሽቱ አብረን እንቀጥል ግን ፈጽሞ መፍትሄ አይኾንም፡፡
ማልኮም ኤክስ እንደሚለው “መጭው ጊዜ ዛሬ እየተዘጋጁ ላሉት ነው” ትምህርት ደግሞ የመጻዒው ትውልድ ዋናው ሂደት እና ዝግጅት ነው፡፡ ነገ እንድትኖር የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ዛሬ እየተዘጋጁ ባሉት ልጆች ትከሻ ላይ ያረፈች ነች፡፡ የፈተና ሂደቱ ጥቃቅን ክፍተቶች ቢኖሩበት እንኳን ታላቁን ራዕይ እና ግብ በማሰብ ከፍተቶቹን መሙላት፤ ጎደሎዎቹን ማቅናት ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው፡፡ የዛሬ ተፈታኝ ልጆችን ሞራል መገንባት እና መጻዒያቸውን ቀናዒ ማድረግ የዜግነት እና የሰዋዊነት ሞራላዊ ግዴታ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!