
መስከረም 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ ግርማ እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው የተመደቡ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናውን በአሁኑ ወቅት መውሰድ ጀምረዋል።
በዩኒቨርሲቲው ፈተናውን መውሰድ የጀመሩት ተማሪዎችን ከሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንዲሁም ከወልድያ ከተማ ከ19 ወረዳዎችና ሦስት ክፍለ ከተማዎች የተመደቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ፈተናው በሦስት ማዕከል የሚሰጥ ሲሆን ፤ ሁለቱ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ፣ አንዱ ደግሞ መርሳ ከተማ በሚገኘው ግብርና ካምፓስ መሆኑን ዶክተር አበበ ተናግረዋል።
በዚህ የመጀመሪያ ዙር ፈተናም 6 ሺህ 735 ሴቶችና 5 ሺህ 800 ወንዶች በድምሩ 12 ሺህ 535 ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት መፈተን መጀመራቸውን አመልክተዋል።
እንደ ዶክተር አበበ ገለጻ፥ ማየት ለተሳናቸው ተፈታኝ ተማሪዎች 35 አንባቢዎች ተመድበው ፈተናውን እንዲወስዱ በመደረግ ላይ ነው።
ትምህርት ሚኒስቴር ለፈተናው ያወጣቸው መመሪያዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ መደረጉንም አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በሰላም መሰጠት መጀመሩን አስታውቋል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፈተናው መሰጠት የጀመረው በዩኒቨርሲቲው የመፈተኛ ካምፓሶች ነው፡፡
ለፈተናው 23 ሺህ 488 ተማሪዎች መቀመጣቸውን ጠቁመዋል። ተማሪዎቹ ጎንደር ከተማን ጨምሮ ከማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተመደቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ፈተናውን ማስፈተን የጀመረ ሲሆን ከአንድ ሺህ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች ፈተናው እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ130 ማዕከላት ከ560 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በተረጋጋና በሰላማዊ ሁኔታ እየወሰዱ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J