“ዘረኝነት መጥፎ ሽታ ያለው ነገር ነውና ራቁት”

272

ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድ ወቅት ነው አሉ፡፡ ነብዩ መሐመድ ከመስጊድ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ በመንገዳቸው ላይ አንዲት ፍየል ሞታ አገኙ፡፡ ወደ ተከታዮቻቸውም ዘወር ብለው ሬሳዋ የተነፋፋውን ፍየል በእጃቸው አነሱና “ከመካከላችሁ ይህችን ፍየል በጨረታ የሚገዛኝ ማነው!?” አሏቸው፡፡

ተከታዮቻቸውም ግራ ተጋቡ፡፡ “ነብያችን ሆይ! ይህች ፍየል እንኳን ሞታ በሕይወቷም ዘመን ዘሯን ፈላጊ የላትም፡፡ አሁንም ሞታ ጥንባቷ መከራ ነው፡፡ እኛ በረከሰ ዋጋም ቢሆን አንገዛም” አሏቸው፡፡ ነብዩም “ዘረኝነትም እንደዚች ፍየል ጥምብ ነው፡፡ እኔ እንድትገዙኝ ሳይሆን ዘረኝነት ጥምብ ነውና እንድትርቁት” በማለት አስተማሯቸው አሉ፡፡

በኢትዮጵያዊቷ በረካ (እሙ አይመን) ሞግዚትነት ያደጉት ነብዩ መሐመድ ከተወለዱና ነብይ ከሆኑ እድሜያቸው ጀምሮ የሰዎችን መልካም ሰብእና በመቅረፅ ተከታዮቻቸው ከዘረኝነት እንዲፀዱ ይመክሩ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የሳቸው ተከታዮች ለፍጥረታት በሙሉ ጉዳትና ጥቃት እንዳይደርስባቸው የሚከላከሉ ነበሩ፡፡ ነብያቸው በዘረኝነት እንዳይታወሩ ዓይናቸውን ገልጠውላቸው ነበርና፡፡

በተወለዱ ማግስት በድርቅ ተመትቶ የነበረው አገር በረከት የሞላበት ሆኖ ነበር፡፡

ወላጅና አሳዳጊዎቻቸው በልጅነታቸው ስለሞቱባቸው ብዙ ችግርና መከራ አይተዋል፡፡

በዘመናቸው ሕዝቡና ተከታዮቻቸው በመልካም ሥነ ምግባር እንዲታነፁ አርዓያ ሆነዋል፡፡

የእስልምና እምነት መመሪያ የሆነው ቁርኣን በመልዕክት የወረደላቸው የመጨረሻው የመደምደሚያ ነብይ ናቸው፡፡

ለሀበሾች ታላቅ ፍቅርና አክብሮት ያላቸው ነብይ ነበሩ፡፡

ነብዩ (ሰ.አ.ወ.) ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ቅን፣ አስተዋይ፣ ለፍጥረታት ሁሉ የሚያዝኑና ክብር የሚሰጡ፣ አንዱን ከአንዱ የማያበላልጡ፣ ዘረኝነትን በጽኑ የሚቃወሙ የመልካም ባህሪያት ባለቤት ነበሩ፡፡

“ዘረኝነት መጥፎ ሽታ ያለው ነገር ነውና ራቁት፤ የሰው ልጅ እንደማበጠሪያ ጥርስ እኩል ነው” በማለትም ተናግረዋል፡፡

ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.አ.ወ.) አምልኮ፣ ሕክምና፣ የሒሳብ ስሌትና ሌሎችንም ነገሮች ትምህርት ቤት ገብተው ሳይማሩና የተፃፉ መጽሐፍት ሳያገላብጡ እንዲሁም ከአዋቂዎች ወይም ከምሁራን ጋር ሳይቀመጡ ያወቁ ናቸው፡፡

በሰዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶችንና ውዝግቦችን ለመፍታት ነብይ ከመሆናቸውም በፊት ጀምሮ የተለየ ችሎታም ነበራቸው፡፡

ነብዩ (ሰ.አ.ወ.) ከመዲና ወደ መካ ሲገቡ ከጠላቶቻቸው ጋር የነበራቸው መግባባት ብቃት እንዳላቸው ያሳዩበት ክስተት ነበር፡፡

ደም መፋሰስ ባለባት ዓለም ላይ ሀሳብ ከኀይል (ከጉልበት) በላይ ኀይል እንዳለው ስላወቁ ከመበቀል ይልቅ በይቅርታ አሻግረዋቸዋል፡፡

በአስተዳደራቸውም ወቅት ነገሮች ሁሉ ውሳኔ የሚያገኙት በምክክር ነበር፡፡ የርሳቸው መንግሥት ሁሉንም ሰው ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የሚመለከት (ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች እንኳ እኩል መብት የነበራቸው) የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ነበር፡፡

ነብዩ (ሰ.አ.ወ.) የሕዝባቸውን ሃይማኖታዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት በሚገባ ጠብቀዋል፡፡

ነብዩ (ሰ.አ.ወ.) ንግግራቸው ጥሩ፣ ምክራቸው ማስረጃ የሚሆን ትልቅ የሆነ የዲፕሎማሲ ችሎታም ነበራቸው፡፡ ከሌሎች ጋር ያደረጓቸውን ውሎችና ስምምነቶች ያፈረሱበት አጋጣሚም አልነበረም፤ ለቃላቸው ተገዥ ነበሩና፡፡

ጠንካራና ከጠላቶቻቸው በተሻለ ሁኔታና አቅም ላይ ሆነው እንኳን አንድም ጊዜ ቀድመው ጦርነት ቀስቅሰው አያውቁም፡፡ ከጦርነት ይልቅ ሰላም ወዳድ እና ተስማምቶ መኖርን የሚመርጡ ሰው ነበሩ፡፡

ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.አ.ወ.) በጌታቸው ላይ ፍፁም የተመኩ፣ ሳይሰስቱ ያላቸውን ሁሉ ለተቸገረ የሚለግሱ፣ ሕፃናትን ጊዜ ሰጥተው የሚያጫውቱ፣ የእንስሳቶችን ስሞታ የሚያዳምጡ፣ የተምር ዛፍ ሳይቀር በናፍቆት ያነባላቸው ተወዳጅ ነብይ ናቸው፡፡

አዛኙ ነብይ እንደ መሪ፣ እንደ አባት፣ እንደ ባል፣ እንደ መንፈሳዊ መሪ የተሟላ ስብዕና የተሰጣቸው ለሰው ልጆች ሁሉ አርዓያ መሆን የቻሉ የአላህ ባሪያ ነበሩ፡፡

ነብዩ የአላህ ሰላምና እዝነት በእሳቸው ላይ ይሁንና ከፈጣሪ የተሰጣቸውን ተልዕኮ እንዳጠናቀቁ ለሕዝቡ ያዘጋጁትን የፈጣሪን ቃል የከተቡበትን ቅዱስ መጽሐፍ (ቁርኣንን) አበርክተው በ63 ዓመታቸው ወደማይቀረው ዓለም ሄዱ፡፡

[ ምንጭ፡- Ethiomuslims.net፣ አፍሪካ ቲቪ፣ ዛውያ ቲቪ ]

በእመቤት አህመድ

ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous article❝ላትችሏት ኢትዮጵያን አትንኳት❞
Next articleየርእሰ መሥተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት!