
መስከረም 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አትንኳት አትችሏትም፣ አትግፏት አትጥሏትም፣ አትግጠሟት አታሸንፏትም፡፡ ስትነኳት ተቆጥተው የሚነሱ፣ እያለሙ የሚተኩሱ፣ ሞትን ንቀው ወደ ጠላት ሠፈር የሚገሰግሱ ጀግና ልጆች አሏት፡፡ ሲገፏት የሚከፋቸው፣ ሲገፏት የሚነዳቸው፣ ሲገፏት እልህና ወኔ የሚተናነቃቸው፣ የአሸናፊነት ግርማን የተላበሱ፣ ጠላቶቿን ከወንዝ ባሻገር የሚመልሱ፣ የክፋትን ግንቦች የሚያፈራርሱ፣ የጠላትን ምሽጎች የሚደረማምሱ ልጆች አሏት፡፡
ሲገጥሟት ሳንጃ አሹለው፣ ጎራዴ ስለው፣ ጠመንጃቸውን ወልውለው፣ ትጥቃቸውን አስተካክለው፣ ጋሻቸውን ጨብጠው እየፎከሩ የሚነሱ፣ በክንዳቸው ጥለው ከአፈር ጋር የሚለውሱ ጀግና ልጆች አሏት፡፡
በክብሯ ላይ ጠላት በተነሳ ጊዜ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድልብ መካሪ ኾነው፣ በኢትዮጵያዊነት ገመድ ተሳስረው፣ ከዳር ዳር ተጠራርተው ይነሳሉ፡፡
ኢትዮጵያዊነት በመከራ ጊዜ በድል ያሻግራል፣ ኢትዮጵያዊነት በጨለማ ዘመን ያበራል፣ ኢትዮጵያዊነት በመለያየት ወቅት እንኳን ይተባበራል፣ ኢትዮጵያዊነት በደከመ ዘመን ይጠነክራል፣ ኢትዮጵያዊነት የችግርን መሰናክሎች ይሰባብራል፣ ኢትዮጵያዊነት መከበሪያ፣ ኢትዮጵያዊነት ማዕበሉን መሻገሪያ፣ ኢትዮጵያዊነት የጠላትን ክንድና ቅስም መስበሪያ፣ አትዮጵያዊነት በድል አድራጊነት መኖሪያ ነው፡፡
ነጮች ያፈሩት፣ ለጥቁር የተንበረከኩት፣ የጥቁሮችን ጉልበት እየሳሙ ይቅርታ የለመኑት፣ መሸነፋቸውን ያመኑት በጠነከረ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ዓለም ለጥቁሮች ፊቷን ያዞረች፣ የክብር ሚዛኗን ወደ ነጭ ያዘነበለች በነበረችበት በዚያ አስከፊ ዘመን ኢትዮጵያዊነት ሚዛኑን አስተካክሏል፣ ኢትዮጵያዊነት እኩልነትን አሳይቷል፡፡
አበው ጥበብ ይኑርህ፣ ጀግንነት አይለይህ፣ አንድነት አይራቅህ ይላሉ፡፡ ጠቢባን በጥበባቸው መንገዱን ያሰላሉ፣ የተደበቀውን ይገልጣሉ፣ የተቆለፈውን ይከፍታሉ፣ ጀግኖች በጀግንነታቸው ድል ያደርጋሉ፣ ሀገር ያስከብራሉ፣ ጠላት ያንበረክካሉ፣ አንድነት ያሻግራል፣ አንድነት ያስከብራል፣ አንድነት ያኮራል፣ አንድነት በግርማ ያኖራልና፡፡
የጠነከረው ኢትዮጵያዊነት የጠነከረች ኢትዮጵያን አጽንቷል፡፡ የጠነከረው ኢትዮጵያዊነት በየዘመናቱ ጠላትን ድል መትቷል፡፡ የጠነከረው ኢትዮጵያዊነት በጥቁሮች ምድር ብርሃን አብርቷል፣ በነጮች ሰማይ ሥር ክብሩን ገልጧል፣ ሞገሱን አሳይቷል፣ ኀይሉን አሳርፏል፡፡
ዘመን ሰጥቶት ኀያል የኾነ ሁሉ እግሩን በኢትዮጵያ ላይ ሊያነሳ ይከጅለዋል፡፡ ኢትዮጵያን በክንዱ አንበርክኮ ለራሱ ማድረግ ያምረዋል፣ በኢትዮጵያ ላይ ድል መጎናጸፍ ይናፍቀዋል፡፡ በስሜን ሞከሯት መታቻቸው፣ በምሥራቅ መጡባት ጣለቻቸው፣ በምዕራብ አሰቡ ሰበረቻቸው፣ በደቡብ ተነሱባት አሳፈረቻቸው፡፡ እርሷ በአራቱም ንፍቅ ለሚመጡት፣ በክፋት ለሚነሱት ጎራዴዋ ስል፣ ጦሯ ሹል ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ፈጽመው ኢትዮጵያን አያስነኳትም፡፡ ደም አፍስሰው ያስከብሯታል፣ አጥንት ከስክሰው ከፍ ከፍ ያደርጓታል እንጂ፡፡
በዚህች በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ደም አፍስሶ፣ አጥንት ከስክሶ ሀገር ማጽናት ማንነት ነው፡፡ “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ” እንዳለ መጽሐፍ ኢትዮጵያዊ ሀገር ማጽናቱን፣ ኢትዮጵያዊ መልካምነቱን፣ ኢትዮጵያዊ አሸናፊነቱን፣ ኢትዮጵያዊ ጀግንነቱን፣ ኢትዮጵያዊ ደግነቱን፣ ኢትዮጵያዊ ሀገሬን ማለቱን፣ ኢትዮጵያዊ ለሠንደቅ መሞቱን አይለውጥም፡፡
በየዘመናቱ ነጋሪት መትተው፣ እየፎከሩ ተነስተው፣ ባሕር ሠንጥቀው፣ የብስ አቋርጠው ጦር አዝምተው በኢትዮጵያ ሠማይ እንዳልነበር የኾኑት ጠላቶች ዛሬ ላይ የጦር ስልታቸውን ቀይረዋል፡፡ ድሮ ልጆቻቸውን ልከው በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ቀርተውባቸዋል፣ ልጆቻቸውን የጀግኖች ጎራዴ በልቷቸዋል፣ ጦሩ አስቀርቷቸዋል፡፡ አባቱ የተሸነፈበት ልጅ የአባቱን ቂም ሊበቀል ዘመተ እርሱም እንደ አባቱ ሞተ፡፡ የአባቱን እና የአያቱን ቂም ለመበቀል ሌላ ልጅ ተነሳ እርሱም እንዳልነበር ኾነ፡፡ በዘር የሚወራረስ ሽንፈት ያስቀጥላሉ እንጂ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ድል እንደማያገኙ ስለ ተደረጉ ዛሬ ላይ የትግል አቅጣጫቸውን ቀይረዋል፡፡
ዛሬ ልጆቻቸውን ሞት ወደ አለበት ሥፍራ አይልኩም፤ ዛሬ ላይ የሚልኩት በኢትዮጵያ የተወለዱትን ባንዳዎች በገንዘብ ገዝተው፣ በጥላቻ ሞልተው ነው፡፡ ባንዳዎች ኢትዮጵያን ያደማሉ፣ ከውጭ ለሚልኳቸው ጌቶቻቸው ጉዳይ ያስፈጽማሉ፡፡ እናታቸውን የሚነክሱት ባንዳዎች የጌቶቻቸውን መልዕክት ተቀብለው በኢትዮጵያ ላይ ተነስተዋል፡፡ አርሰው፣ አፍሰው፣ አልብሰውና አጉርሰው የሚበሉ ንጹሐን አርሶ አደሮችን ይገድላሉ፣ አካል ያጎድላሉ፣ ሃብትና ንብረት ያወድማሉ፡፡
የሕወሓት የሽብር ቡድን፣ ሸኔ እና ሌሎች በኢትዮጵያ ላይ እግራቸውን ካነሱ ውለው አድረዋል፡፡ የውጭ ጋሻ ጃግሬዎቻቸውም አይዟችሁ ግፉበት፣ በሉት፣ ቁረጡት ይሏቸዋል፡፡ በእነርሱ ያልተሳካውን ድል በባንዳዎች ማሳካት ያልማሉና፡፡ ታዲያ በደምና በአጥንት የጸናች ኢትዮጵያን ለመጠበቅ ከአባቶቻቸው ቃል ኪዳን የተቀበሉት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ባንዳውንም ባዳውንም እያሳፈሩ በጀግንነት ይጠብቋታል፡፡
ከሠንደቋ ግርጌ ቃል ገብተው የወጡት የኢትዮጵያ ጀግና ወታደሮች በቀኝም በግራም፣ በፊትም በኋላም በሀገር ላይ የተነሳውን ድባቅ እየመቱ ሀገራቸውን እያስከበሩ፣ ቃል ኪዳናቸውን እያከበሩ፣ ለገቡት መሓላ እየኖሩ ነው፡፡ እንኳን ዛሬ በሰማይ የሚበር፣ በምድር የሚሽከረከር ቴክኖሎጂ በበዛበት፣ መድፍና ታንክ በሚተኮስበት፣ መትረየስና ዲሽቃ በሚያሽካካበት ድሮም ጎራዴ ሥለው፣ ጦር አሹለው እየተነሱ ባንዳና ባዳ አላሸነፋቸውም፡፡ ዛሬም ነገም አያሸንፋቸውም፡፡
የኢትዮጵያ ወታደር ምሽጎች የማያቆሙት፣ ጠላቶች የሚፈሩት ጀግና ነው፡፡ “ላታሸንፏት ኢትዮጵያን አትንኳት” እያለ ይገሰግሳል፣ የመጣውን ጠላት ሁሉ ይመልሳል እንጂ፡፡ ምሽግ ውሎ ምሽግ ያድራል፣ በጀግንነት ተነስቶ የጠላትን ምሽግ ይሰባብራል፣ ሠንደቁን ያስከብራል፡፡ በረሃው ቢበዛበት፣ ብርዱ ቢበረታበት፣ ወንዝ ቢሞላበት፣ ጠላት በፊቱ ቢደረደርበት ወደ ፊት ከመገስገስ የሚያቆመው የለም፡፡
አሸናፊነትን ከአባቶቹ የወረሰ፣ የድል ግርማን የተላበሰ ጀግና ነውና በጀግንነት ይገሰግሳል፡፡ የተተበተቡ የጠላት ወጥመዶችን ይበጣጥሳል፡፡ ኢትዮጵያን በሞታቸው የሚያጸኗት፣ በክንዳቸው የሚያስከብሯት፣ በላብና በደማቸው የሚጠብቋት ጀግና ልጆች አሏትና ማንም አይነካትም፣ ማንም አይደፍራትም፡፡ እርሷ ለማሸነፍ ብቻ የተፈጠረች፣ ለድል አድራጊነት የተመረጠች ሀገር ናትና፡፡
እነኾ ልጆቿ በሰማይና በምድር የሚመጣውን ጠላት ለመመከት በተጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡ ከጀግና ሕዝባቸው አደራ ተቀብለው፣ ጀግና ሕዝባቸውን ደጀን አድርገው በኩራት ይጠብቋታል፣ በድል አድራጊነት ያኖሯታል፡፡ ወታደር የኢትዮጵያ መከታ፣ የኢትዮጵያ አለኝታ መኾኑን የተረዱት ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም ሀገራቸውን ለመጠበቅ የጀግናውን ተቋም እየተቀላቀሉት ነው፡፡ ጀግኖቹ በሰማይ እየበረሩ፣ በምድር እየተሸከረከሩ፣ የጠላትን ጉልበት እየሰበሩ ኢትዮጵያን እንደ ጠበቋት ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያም እንደ አሸነፈች እንደተከበረች ትኖራለች፡፡ ጠላቶቿም እንደ አፈሩ ይኖራሉ፣ የኢትዮጵያን መሸነፍ እንደናፈቁ ይቀራሉ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J