
መስከረም 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔራዊ ባንክ 391 የሚደርሱ ሕገወጥ የሐዋላ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የባንክ ሒሳባቸው ተዘግቶ ክስ የመመስረት ሂደት እንደተጀመረ አስታውቋል።
በሕገ ወጥ መልኩ በጥቁር ገበያ ላይ በተሠማሩ አካላት ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወስድም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ 391 የሚደርሱ ሕገ ወጥ የሐዋላ አገልግሎት ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች የባንክ ሒሳባቸው መዘጋቱን ተናግረዋል።
ባንኩ የግለሠቦቹን ስም ዝርዝር ለፍትሕ ሚኒስቴር በመላክ ክስ የመመስረት ሂደት እንደሚጀምር አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በባንክ ቤቶች ውስጥ ያሉ የባንክ ኃላፊዎችና ሠራተኞችም በዚህ ሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትም እንዳሉ ጠቅሰው በነዚህ አካላት ላይ አሥተዳደራዊ እርምጃና ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ይህን ሕገወጥ ድርጊት ለሚጠቁሙ ዜጎች የወሮታ አከፋፈል ሥርዓት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከተፈቀደው በላይ በቤት ውስጥ የብር ክምችት የሚያደርጉ፣ የሐሰተኛ የገንብ ኖቶችን የሚሠሩና የሚያሠራጩ አካላት እንዲሁም በሕገወጥ መልኩ የሐዋላ አገልግሎት የሚሠጡ ወይም በጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለሚጠቁሙ ዜጎች ደኅንነታቸውና ሚስጥራዊነታቸውን በጠበቀ መልኩ የሚሸልምና ወረታውን የሚከፍል መሆኑን አስታውቀዋል።
መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የፈቀደውን የፍራንኮ ቫሉታ ፍቃድ እንደ እድል በመውሰድ በሕገወጥ መንገድ ዶላር በመጠቀም ሸቀጦችን የማስገባት ተግባር የተስተዋለ በመሆኑ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የባንክ ማስረጃ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርቡ የሚደረግ መሆኑም እንደተገለጸ ኢፕድ ዘግቧል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J