❝እጄን ጠላት ከሚነካት፣ ተከዜ ነብሴን ይውሰዳት❞

367

መስከረም 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ ወንዝ ኾይ ያየኸውን ሁሉ መስክር፣ በዘመናት ጉዞህ የታዘብከውን ሁሉ ተናገር፣ ስንቶች ተሻግረውህ አለፉ? ስንቶች በማዕበልህ ተጠለፉ? ስንቶች ከጥማቸው ለመርካት ተጎነጩህ? ስንቶችስ ለመንጻት ታጠቡብህ? ስንቶች ከዳርህ ቆመው ጭንቀታቸውን አዋዩህ? ስንቶች ምስጢራቸውን ነገሩህ? ስንቶች በውስጥህ እየዋኙ ፍቅር አዩብህ ?

ለዘመናት ያለ እረፍት ተጉዘሃል፣ ለዘመናት በዳርህ ቆመው የሚያዋዩህን ሰምተሃል፣ በፍቅር ውስጥ ኾነው ወደ አንተ የመጡትን ተመልክተሃል፣ የሰጡህን ተቀብለህ ወስደሃል፣ ያዘኑትን አጸናንተሃል፣ የተከዙትን ደስታቸውን መልሰሃል፡፡

ብዙዎች በዳሩ ቆመው እንደ ታማኝ ወዳጃቸው አማከሩት፣ ለችግራቸው መፍትሔ ጠየቁት፣ ጭንቀታቸውን አካፈሉት፣ ስቃያቸውን ነገሩት፣ ደስታቸውን አበሰሩት፣ ፍቅራቸውን አሳዩት፣ መውደዳቸውን ገለጡለት፣ ፍቅረኛሞች ዳሩ ቆመው ቃል ኪዳን አስረውበታል፣ በውስጡ ገብተው እየዋኙ ፍቅር አይተውበታል፣ መልካሙን ጊዜ አሳልፈውበታል፡፡ ላይረሱት ትዝታ ጥለውበታል፡፡

ታላቁ ወንዝ ለዘመናት ታዘባቸው፣ በዳሩ ቆመው ቃል ኪዳን እያሰሩ የሚመለሱትን ሸኛቸው፣ እድሜ አግኝተው ዳግም የሚመጡትን ይቀበላቸዋል፣ የሚፈልጉትን ደስታ ይሰጣቸዋል፡፡ ከመልካሙ ምድር የሚነሳው፣ የደረቀውን ምድር የሚያረሰርሰው ታላቁ ወንዝ ተከዜ ለዘመናት እየተጓዘ ለዘመናት ታዝቧል፣ ወደፊትም ይታዘባል፡፡

አንዳንዶች አምነው ነብሳቸውን ሰጥተውት፣ ታምኖ መልሶላቸዋል፣ ከጭንቅና ከመከራ አውጥቷቸዋል፣ ከሞት አሻግሮ አዲስ ዘመን አሳይቷቸዋል፡፡ እርሱ ታማኝ ባልንጀራ ኾኗቸው ነብሳቸውን ያተረፉበት፣ ከጥም የረኩበት፣ የነጹበት ብዙዎች ናቸው፡፡

ተከዜ ከሞት ካዳናቸው፣ ከጠላት ካራቃቸው፣ አዲስ ሕይወት ካሳያቸው ሰው ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ ከእግራቸው ሥር ኾኜ ታሪካቸውንም ጠይቄያለሁ፤ ነገር ግን የሰማሁትን ሁሉ ብጽፍ ማን ያምነኛል? ያዳመጥኩትን ሁሉ ብናገር ማን ይቀበለኛል? ይሄስ ተረት ነው፣ ካለበለዚያም ሕልም ነው የሚለኝ አይጠፋም፡፡ እኔ ግን ከሰማሁት አንዳችም ነገር አልጨመርኩም፣ የመረረውን እውነት፣ በሞት መካከል የተጓዘችን ሕይወት ጻፍኩ እንጂ፡፡

ሰረበ በየነ ይባላሉ፡፡ ይህችን ምድር የተቀላቀሏት በ1945 ዓ.ም ነው፡፡ የትውልድ ሥፍራቸው ደግሞ በስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ወልቃይት አዲጋባ ጊዮርጊስ ነው፡፡ ወላጆቻቸው ከአዲጋባ ጊዮርጊስ አጸድ ሥር ምህረትን እና ይቅርታን የሚለምኑ ፈሪዓ እግዚአብሔር ያደረባቸው ደጋጎች ነበሩ፡፡ እሳቸውም በወላጆቻቸው ደግነት እና መልካምነት አደጉ፡፡ ከታሪክ አዋቂ ዘመዶቻቸው ሥር እየተቀመጡ ታሪክ ያዳምጡ ነበር፡፡

ዘመኑ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዙፋን ላይ የነበሩበት ዘመን ነበር፡፡ መኳንንቱን፣ መሳፍንቱን፣ የጦር አበጋዙን፣ ሊቃውንቱን፣ ባላባቱን አይተዋል፡፡ ለሀገር ያላቸውን ፍቅር ተመልክተዋል፡፡ እነ ቢትወደድ አዳነ መኮንን እና ሌሎች ጀግኖች በጀግንነት ሲመላለሱና ሲተኩሱ ታዝበዋል፡፡

እድሜያቸው ከፍ እያለ ሄደ፡፡ የንጉሡ ዘመን አልፎ አብዮቱ ፈነዳ፡፡ አዲስ ሥርዓትም ሀገሪቱን ማስተዳደር ጀመረ፡፡ የደርግ ሥርዓት ንጉሡን ተክቶ ሥልጣን እንደያዘ በርካታ ተቀናቃኞች ተፈጠሩበት፡፡ በዚያ ዘመን በትጥቅ ትግል ከተነሱት መካከል የደደቢቱ ፍልፈል ሕወሓት አንደኛው ነበር፡፡ ሕወሓት የትጥቅ ትግሉን ሲጀምር ተከዜን ተሻግሮ ወደ ጎንደር ግዛት መምጣት ከጀለ፡፡ ያን ጊዜ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ጀግኖች አይኾንም፣ አይደረግም አሉ፡፡

እነርሱ የደደቢቱ ፍልፈል አካሄድ ቀድሞ ገብቷቸዋል፣ ሕልሙንና ራዕዩን አስቀድመው ተረድተውታል፡፡ ሕልምህን ከተከዜ ማዶ ታደርጋለህ እንጂ ተከዜን ተሻግረህ የምትረግጣት ምድር የለችህም ብለው በጥይት አሩር ይቆሉት ጀመር፡፡ በዚያ ዘመን ነፍጥ አንስተው ወደ በረሃ ከወረዱት መካከል ሰረበ በየነ አንደኛው ናቸው፡፡

“ጓደኖቼን ይዤ ወደ በረሃ ወጣሁኝ፣ በሕግ እምቢ ሲሉ በየስብሰባቸው እየገባን እንወጋቸው ጀመር፡፡ ጓደኞቼ ጋር ኾኜ እያስተባበርኩ ወጣቱ ሁሉ መሳሪያህን ይዘህ በረሃ ተቀመጥ፣ ከቤትህ እንዳትቀመጥ፣ ወያኔ ሀገርህን እንዳይወስዳት አልን” እነዚያ ጀግኖች በምሬትና በእልህ ተነሱ፡፡ በአደጉበት ቀዬ እየተመላለሱ፣ በዱር በገደሉ እየገቡ ጠላታቸውን አንገበገቡት፡፡ ጠላታቸውን እየደመሰሱ፣ መሳሪያቸውን እየማረኩ እረመጥ ኾኑበት፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ታላላቅ ሰዎችን መሳፍንት፣ ነጭ ለባሽ እያለ ያሰቃያቸው ነበርና ጀግኖቹ የበለጠ አመረሩ፣ ላይመለሱ ተቆጡ፡፡ ሕወሓት መሳፍንት እያለ ሊወስዳቸው የነበሩትን አባቶች በጀግንነት አስቀሯቸው፣ ጠላቶቻቸውን መቱላቸው፡፡

“የቀደሙት አባቶች በጦር በጎራዴ ያቆዩትን ሀገር እኛ ልጆቹ ደርሰን ለጠላት አሳልፈን አንሰጥም፣ እነርሱ ከተከዜ መለስ ሀገራቸው ስላልኾነ እኛ ለሀገራችን እንሞታለን” ነው ያሉት።

“የከፋቸው ጀግኖች፥ ኧረ ተው ተመለስ እርሱ ነው ድንበሩ፣ የሰው ድንበር አፍራሽ ወያኔ ነህ አሉ፣
ሀገራችን ቆላ ወንዛችን ተከዜ፣
ማነው የሚነካን በምንሽር ጊዜ እያሉ ያቅራሩ ነበር፡፡

በእኛ ጊዜ ደግሞ ዓለም አጫዎቾቹ፥
ድሮ አባቶቻቸው ዝሆን አደኑበት፣ አንበሳ አደኑበት፣
ልጆቻቸው ደርሰው ትራክተር ነዱበት እያሉ ገጠሙ፡፡ እኛ የጀግኖች የእነ አጼ ቴዎድሮስ ልጆች ነን፣ የማንንም አንነካም፣ የኛንም አናስነካም” የጋሽ ሰረበ ቃል ነው፡፡

ሰረበ እና ጓደኞቻቸው ያለ እረፍት ከጠላት ጋር መዋደቃቸውን ቀጠሉበት፡፡ የሕወሓትን የሽብር ቡድን ባሕሪ አስቀድመው አውቀውታልና አሻፈረኝ እንዳሉ በትግላቸው ቀጠሉ፡፡ አንድም ቀን ሳያርፉ የደርግ ሥርዓት አልቆ አዲስ ሥርዓት በኢትዮጵያ ላይ መጣ፡፡ እነ ሰረበ ግን ዱር ቤቴ እንዳሉ በዛው ቆዩ፡፡

ከሕወሓት መራሹ መንግሥት ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል እና ለተሻለ ትግል ሲሉ ሰረበ ወደ ኤርትራ ተሻገሩ፡፡ ጊዜውም 1986 ዓ.ም ነበር፡፡ በኤርትራ እምነሃጅርም ተቀመጡ፡፡ በእምነሃጅር እንዳሉም ድንገት በተገዛ ሰው ተያዙ፡፡ ተይዘውም ተከዜን አሻግረው ሊያመጧቸው መንገድ ጀመሩ፡፡ ሕወሓት ሰረበን የመሰለ ታጋይ አግኝቶ እንደማይምራቸው ልባቸው ያውቀዋል፣ ወይ በጨለማ እስር ቤት እስከ ወዲያኛው ያስቀምጣቸዋል፣ ካለበለዚያም አሰቃይቶ ይገድላቸዋል፡፡ ሰረበ በሕወሓት እጅ መሞትን ፈጽሞ አልፈቀዱም፡፡ አንድ ውሳኔ መወሰን እንዳለባቸው ተሰማቸው፡፡ ያለ ፍርሃት ወሰኑት፡፡

ወርኃ ነሐሴ ነው፡፡ ተከዜ ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልቷል፣ በአስፈሪ ግርማ እየተገማሸረ ነው፡፡ እንኳን ዋኝተው ሊሻገሩት ከዳር ቆመው ሲያዩትም ያስፈራል፣ ያስደነግጣል፣ ሰረበ ግን ተከዜን ይወዳጁት ዘንድ ወደዱ፡፡ ከእምነሃጅር ተይዘው ወደ ሁመራ ሊሻገሩ ነው፡፡ ከተከዜ ድልድይ ደረሱ፡፡ በዚያም ከደልድዩ ዘለው ሞልቶ ወደ ሚገማሸረው ተከዜ ተጨመሩ፡፡

“ነሐሴ 28 ቀን 1986 ዓ.ም ነው፡፡ ተከዜ ሞልቷል፡፡ ወደ ሁመራ ሊያሻግሩኝ ሲሉ ከወያኔ እጅ ከመውደቅ መሞት አለብኝ ብዬ እጄን ለተከዜ ሰጠሁ፡፡ የማርያም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊቴ ነበረች፣ ድንግል ማርያም፥ ጉልበት አለኝ ብዬ ሰው በድዬ ከኾነ በዛሬው ቀን ፍረጅኝ ብዬ ገባሁ፡፡ አምኜ ገባሁ፤ ከማዕበል ወጣሁ፡፡ ዘመን አልፎ በእነርሱ መቃብር ላይ ቆሜ ይሄን ለመመስከር በቃሁ፡፡ አሁንም ያለችኝን እድሜ ለትግል አውላታለሁ” ነው ያሉት፡፡

ምን አይነት መጨከን ነው ? ከሚገማሸር ማዕበል ውስጥ የከተታቸው፣ ከወንዝ ውስጥ የጣላቸው፣ እርሳቸው ለሕወሓት እጅ ከመስጠት በወንዝ ተወስዶ መሞት ክብር ነው ብለዋልና አደረጉት፡፡ እርሳቸው የምንጭ ውኃ እየጠጡ ትጥቃቸውን ከጠላታቸው እየነጠቁ የታገሉ ጀግና ናቸው፡፡

ሁመራና ተከዜ ያደኩበት ነው፣ ትንሽ ትንሽ እዋኝ ነበር፤ ተከዜ በወርኃ ነሐሴ ማንም የማይጥሰው ነው፣ በዋና እወጠዋለሁ አይባልም፤ ወያኔ እጄን ከሚይዘው ማዕበሉ ይብላኝ ብዬ ነው የገባሁት፡፡ ዘልዬ ስገባ ይዘውኝ የነበሩት ደነገጡ፡፡ ተኮሱብኝ ማዕበሉ ወዲያና ወዲህ ስለሚያማታኝ ሊያገኙኝ አልቻሉም፡፡ ከዚያ በኋላ የዓሳ ቀለብ ኾኗል ብለው ተውኝ፣ ማዕበሉ ይዞኝ ሲሄድ በዳር ያለው ሰው ይጮሃል፡፡ እድል ካገኘሁ እወጣለሁ፣ ካልወጣሁም ግድ የለም ከሕወሓት እጅ ከመግባት ሞትን እመርጣለሁ ብለው ዘለው ገቡ። ሰባት ኪሎሜትር የሚኾን በማዕበል እየተገፉ ሄዱ፡፡ ከረጅም እንግልት በኋላ ማዕበሉ አውጥቶ ጣላቸው፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ በደለሉ ወድቀው ዝም አሉ፡፡ የሚኾኑትን ማወቅ አልቻሉም ነበር፡፡ ከቆይታ በኋላ መረጋጋት ጀመሩ፡፡ ጀንበር አዘቅዝቃለች፣ ብርሃኗን ከልክላለች፡፡ ሰረበ የትም መሄድ እንደማይችሉ አወቁ፡፡ በዚያውም አደሩ፡፡ ሌላ ጨለማ ሲመጣ ከተቀመጡበት ተነስተው በግምት መጓዝ ጀመሩ፡፡ የሚሄዱበት ሁሉ እሾህ የበዛበት ነበርና መራመድ ተሳናቸው፤ የሚረግጡት ጠፋባቸው፡፡ ስቃያቸው በዛ፡፡

“ስቃዬ በዛ፣ ሁሉም ራቀብኝ፣ ሞትን አጣኋት፣ ምን ላድርግ ” ይላሉ ጋሽ ሰረበ ያን ጊዜ ሲያስታውሱት፡፡

እሾህ በበዛበት፣ አሜካላ በማያላውስበት ምድር በጨለማ ተጓዙ፡፡ ረዘም ካለ የስቃይ ጉዞ በኋላ በጨለማ ውስጥ የምትነድ እሳት ተመለከቱ፡፡ ተስፋቸው ለመለመች፡፡ አንድ ከብቶች ይዞ በበረሃ ከተኛ ኤርትራዊ ገበሬ ጎጆ ደረሱ፡፡ ያን ገበሬ አናገሩት፡፡ ችግራቸውን አዋዩት፡፡ ሰረበ አረብኛ ይችሉ ነበርና በአረብኛ ነበር የተግባቡት፡፡ ከረሃባቸው የሚያስታግሳቸው ምግብ ሰጣቸው፡፡ እሾህ የሚከላከሉበት አሮጌ ጫማም ሰጣቸው፡፡ ከዚያ በበረሃ ከተገኘ ገበሬ ጋር ለሁለት ቀናት ቆዩ፡፡

ሰረበ ዳግም ወደ ሀገራቸው እንደማይመለሱ ያውቁታልና በሕይወት መኖራቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፈው ገበሬው እንዲያደርስላቸው አደራ ብለው ተሰናበቱት፡፡ ያም ገበሬ ወደ ሁመራ አቅጣጫ ያቀና ነበርና አደራውን ተወጣ፡፡ ሀገር የናፈቀች ነብስ ተንከራተተች፡፡ ወደ እምነሃጅር አቀኑ፡፡ ከሕወሓት እጅ የወደቁ ጓደኞቻቸው መሞታቸውን ሰሙ፡፡ ልባቸው በሐዘን እየተሰበረች ከእምነነሃጅር ወደ ተሰነይ በእግራቸው ገሰገሱ፡፡ ከተሰነይ ወደ ከሰላ አቀኑ፡፡ ጉዞው በእግር መሄዱ ብቻ አልነበረም አድካሚው፤ ቀን እንዳይታዩ ስለሚሰጉ ጉዟቸው በሌሊት መኾኑ ነበር ፈታኙ፡፡ የቆረጠች ነብስ ናትና ችግሩን ሁሉ እየተቋቋሙ ገሰገሱ፡፡ በበረሃ እየወረዱ የቀን ሥራም ይሠሩ ነበር፡፡ የሚያገኟትን ገንዘብ ለከፋ የመከራ ቀን ቆጠቧት፡፡ ከከሰላ ወደ ሱዳን የሚወስደውን ጎዳና አገኙ፡፡

መንገድ እየጠየቁ ወደ ሱዳን አቀኑ፡፡ ወደ ገዳሪፍ የምትሄድ መኪናም አገኙ፡፡ በእርሷም ኾነው ገዳሪፍ ገቡ፡፡ ገዳሪፍ መቆዬት እንደሚያስይዛቸው ያውቃሉ፡፡ ራሳቸውን እየደበቁ ለአንድ ወር ያክል ገዳሪፍ ቆዩ፡፡ ወደ ካርቱምም አቀኑ፡፡ ለጥቂት ጊዜ በካርቱም እቆያለሁ ብለው ያሰቡት ሰረበ ቀናት፣ አልፈው ሳምንታት፣ ሳምንታት አልፈው ዓመታት እየተተካኩ በሀገረ ሱዳን መናገሻ ካርቱም ለአሥራ አራት ዓመታት ቆዩ፡፡

ሱዳንን ለቅቀው ወደ ሌሎች ሀገራት ለመሄድ ያደረጉት ትግል አልሳካ ብሏቸው ነበር ለዓመታት ካርቱም መቀመጣቸው፡፡ በስደት ሀገር የከፉ ጊዜያትን አሳለፉ፡፡ በሱዳን እያሉም በርካቶች በሕወሓት ሰዎች እየተያዙ በኮንቴነር ወደ ኢትዮጵያ ተወሰዱ፡፡ ብዙዎች የት እንደደረሱ አልታወቀም፡፡ ከዓመታት ድካም በኋላ ለሌላ ስደት ወደ እስራኤል ጉዞ ጀመሩ፡፡ ሀገረ ግብጽን ሲሻገሩም ጥቃት ደረሰባቸው፡፡ ከጓደኞቻቸው መካከል ከፊሎቹ በጥይት ተመትተው ዳግም ላይመለሱ አሸለቡ፡፡ ገሚሶቹ ተያዙ፡፡ ትረፊ ያላት የሰረበ ነብስ ግን ከሞትና ከመያዝ ተርፋ እስራኤልን ረገጠች፡፡

በሀገረ እስራኤልም ለአሥራ ሦስት ዓመታት ተቀመጡ፡፡ አያሌ ፈተናዎችንም ተጋፈጡ፡፡ የሚወዷት ሀገራቸው፣ ያደጉበት ቀያቸው እየናፈቃቸው ዓመታት ነጎዱ፡፡ ዓመታት ነጉደው በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አዲስ ነገር መኖሩ ተሰማ፡፡ ጋሽ ሰረበ ያን ጊዜ የሚወዷት ሀገራቸውን የሚረግጡበት ዘመን እንደደረሰ አወቁ፡፡ ይመለሱ ዘንድም ወደዱ፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ ሰው ኾነው የሚያኖራቸውን ፈቃድ አላገኙም ነበርና ለመመለስ ተቸገሩ፡፡

ከትውልድ ቀያቸው መታወቂያ ከተላከላቸው ፓስፖርት እንደሚሰጣቸው ተነገራቸው፡፡ ወደ ትውልድ ቀያቸውም መልዕክት ላኩ፡፡ መታወቂያውም ተሠርቶ መጣ፡፡ ዳሩ ከመታወቂያቸው ላይ ወልቃይት ጠገዴ በትግራይ ክልል የሚል ነበረበትና ይሄን ከመቀበል ያለ ነጻነት በስደት ነብሴ ትወጣለች ሲሉ መታወቂያቸውን ቀደው ጣሉት፡፡ ለመከራ የዳረጋቸው ወልቃይት የትግራይ አይኾንም ማለታቸው ነውና በፍጹም ሊቀበሉት አልቻሉም፡፡

ወደ ሀገራቸው ለመመለስ አዳጋች ነበር፡፡ ችግሩን ሁሉ ተቋቁመው መመለስ የሚያስችላቸውን ፈቃድ አገኙ፡፡ ከሀገረ እስራኤል ወደ ሚወዷት ሀገራቸው ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ወዳጆቻቸው ለምን ሞት ወደ አለበት ትሄዳለህ አሏቸው፡፡ እሳቸው ግን አይኾንም በሀገሬ ያለው ተስፋ ታይቶኛል ብለው መጡ፡፡ ሥርዓት ቢያስከፋህ ሀገርህን አትጠላም፣ ማንነትህን አትረሳም ይላሉ ጋሽ ሰረበ፡፡ እርሳቸው ሀገራቸውን አብዝተው ይወዳሉ፡፡

እነኾ ዛሬ በሚወዷት፣ አያሌ መከራ ባሳለፉባት ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ መኖር ጀምረዋል፡፡ ወጣቶችን እያበረታቱ፣ ስንቅ እያቀበሉ፣ አይዟችሁ እያሉ አሸባሪው ሕወሓትን እየታገሉ ነው፡፡

“ታሪክህን እወቅ፣ የአያቶችህን ታሪክ እወቅ፣ መምረር አለብህ፣ ጠላት በከፈተው ቦይ እንዳትፈስ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ ኾኖ ጠላትን ማጥፋት አለብን፣ እንኳን አሸባሪው ሕወሓትን ጣሊያንንም ድምጥማጡን አጥፍተነዋል፣ እናጠፋዋለን ” ነው ያሉት ጋሽ ሰረበ፡፡ ጋሽ ሰረበ ከዓመታት በፊት ወደ ተከዜ ሲገቡ የገቧትን ቃል ያስታውሷታል “ሞት ከእጄ ላይ እያለ ሞትን ከእነርሱ ላይ አለምንም፣ ለእነርሱ እጄን ሰጥቼም ክብሬን አላሳንስም” ጀግኖች ለክብር ሞትን ይንቃሉ፣ ከሞት መልዕክተኛ ጋር ይታገላሉ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous article”ጧሪም ቀባሪም ልጄን ቀሙኝ” በቆቦ ከተማ ልጃቸው በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የተገደለባቸው እናት
Next articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሕገወጥ የሐዋላ ሥራ ላይ የተሰማሩ 391 የሚደርሱ ሰዎች የባንክ ሒሳባቸው መዘጋቱን አስታወቀ።