
ወልድያ: መስከረም 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አዛውንት ናቸው። እድሜያቸው 70 ዓመት ያልፋቸዋል። መኖሪያቸው ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ሮቢት ከተማ ነው።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለሦስተኛ ጊዜ አካባቢውን በወረረበት ወቅት በጭካኔ አስገድዶ መድፈር ፈፅሞባቸዋል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን ያልጠቀስናቸው እኒህ እናት ሁለት ልጆች አሏቸው። ልጆቻቸው ራሳቸውን የቻሉና ከሮቢት ከተማ ውጭ እንደሚኖሩ ነግረውናል።
በአሸባሪ ቡድኑ የጥላቻ ድርጊት የተደፈሩት እናት በእድሜ የገፉ ሊደገፉና ሊጠወሩ የሚገባቸው ናቸው።
አሸባሪው ቡድን ሮቢትን በወረረ በማግስቱ ነሐሴ 23/2014 ዓ ም ነበር፤ ተበዳዩአ እናት እንዳሉት “የቡድኑ አባላት ሁለት ናቸው፤ በሩን ሰብረው ገቡ። በ30ዎቹ እድሜ ክልል ይሆናሉ። “ብር አምጭ አለኙ። ኧረ እኔ ደሀ ነኝ ስላቸው በጥፊ መቱኝ” ነው ያሉን። ገንዘብ ከሌለሽማ በማለት ገፍትረው አስገድደው እናታቸውን ደፈሩኝ” ነው ያሉን።
“እኔ ትልቅ ሰው ነኝ፤ እናታቸውም ነኝ። እኔን ይደፍሩኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ያሰቡትን የጭካኔ ድርጊት ፈጽመው ሲጨርሱ ከቤት ያገኙትን ሀብትና ንብረት ዘርፈው ሄዱ ነው ያሉት።
“እኔ ለየትኛው ቀሪ ህይወቴና ለየትኛው የነገ ትዳሬ አስቤ እደብቀዋለሁ ብየ፤ ወዲያው እየጮሁ ወጣሁ፤ ጎረቤት ተሰበሰበ፤ የተፈጸመብኝንና የአሸባሪዎችን የጥላቻ ድርጊት ተናገርኩ” ነው ያሉን።
“ይልቅ በእኔ ላይ የፈፀሙት ድርጊት ፍላጎታውቸው ማንነትን ማዋረድ እንደሆነ ነው የገባኝ፤ ምክንያቱም ማንነትን መሰረት ያደረገ ስድባቸው ብዙ ነበር። አማራን እያነሱ ይሳደባሉ። በሚፈጽሙት ድርጊት አማራን የተበቀሉ ያክል ነው የተሰማቸው። እኔ ግን ይኸው አንገት አልደፋም። አማራ ግን በደሉ ሊቆጨው ይገባል። እንደ እኔ በአሸባሪው ድርጊት በጭካኔ የተደፈሩም ብዙ ሴቶች አሉ፤ ይህን የጭካኔና የሕዝብ ጠላትነታቸውን የሚያረጋግጥ ድርጊታቸውን ሁሉም እንዲያውቀው ማጋለጥ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ:–ካሳሁን ኃይለሚካኤል
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!