
ሰቆጣ: መስከረም 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ሕወሓት የሰላም አማራጮችን በመተው ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጦርነት በወረራ በደረሰበት በአማራ እና አፋር ክልሎች የጥፋት አሻራውን አሳርፏል።
በሰዎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈጸም፣ መግደል፣ መዝረፍና ማውደም ዛሬም እንደ ትላንቱ የአሸባሪው ሕወሓት ወራሪ ቡድን ሰይጣናዊ ግብር ኾኖ ቀጥሏል።
በዋግምኽራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ሁሉ እኩይ ዓላማን አንግበው የሚንቀሳቀሱ የሕወሓት ታጣቂዎች ንጹሐንን ገድለዋል፣ አሰቃይተዋል፣ ሕጻናት እና አዛውንት ሴቶች ላይ ክብረነክ የኾነ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ፈጽመዋል፣ ንብረት አውድመዋል፣ የግለሰብ የዕለት ጉርስ ሳይቀር ዘርፈዋል።
የዋግምኽራ ብሔረሰብ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ በርናባስ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችን ጎብኝተው ባዩት፣ በሰሙት ነገር ሁሉ እንዳዘኑ በተለይ ከአሚኮ በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
ብፁዕ አቡነ በርናባስ እንዳሉት ጦርነት ለኢትዮጵያ አዲሷ ባይኾንም እንዲህ አይነት ኢ-ሞራላዊ፣ ዓላማ ቢስ፣ አውዳሚ፣ ንጹሐንን የሚቀጥፍ፣ ሕዝብን የሚያዋርድ ጦርነት ግን ገጥሟት አያውቅም ብለዋል።
በወረራ የቆዩና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችን ተዟዙሬ እንደጎበኘሁት ይላሉ ብፁዕነታቸው “ንጹሐንን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ተፈጽሟል፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትም ተፈጽሟል” ብለዋል።
ሴቶች ላይ አስነዋሪ ድርጊት ፣ ክብረነክ የኾነ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደተፈጸመም አረጋግጫለሁ ነው ያሉት።
ሃብት ንብረታቸው ተዘርፎ፣ ወድሞ፣ የዕለት ጉርሳቸውን ሳይቀር አጥተው ችግር ላይ የወደቁ ወገኖችም አሉ ሲሉ ተናግረዋል።
በእርግጥም በተለያዩ አካባቢዎች በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለአሚኮ እንደተናገሩት የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች የእናቶችን መቀነት አስፈትተው ሽራፊ ሳንቲም ሳይቀር ቀምተዋል።
የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች እናቶች ጓዳ ውስጥ ገብተውም ሊጥ ጠጥተዋል፣ ተሸክመው ወስደዋል፣ ደፍተዋል፣ ቤት ውስጥ ያለ ጥሬ ጨው አልቀራቸውም ሲሉ ነው ተጎጂዎቹ የተናገሩት።
እኒያ የሽብር ቡድኑ እኩይ ዓላማ ፈጻሚዎች በየአርሶ አደሮች ቤት ገብተው ዶሮ እያባረሩ ይዘዋል፣ የወተት ላሞቻቸውን፣ የእርሻ በሬዎቻቸውን ሁሉ የሚበሉትን አርደው በልተው ያልቻሉትን በጥይት ገድለዋል።
በንጹሐን ላይ ባደረሱት ጥቃትም ከአንድ ቤት እስከ 6 ቤተሰብ በግፍ መግደላቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው። ሞትን ሽሽት ከቀያቸው ተፈናቅለው በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ላይ በነበሩ ወገኖች ላይ በደረሰ ጥቃት የ18 ንጹሐን ሕይወት መቀጠፍም የሚዘነጋ አይደለም።
ብፁዕ አቡነ በርናባስ በተከፈተው ጦርነት ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ፣ ቤተ-እምነቶችንም ዒላማ ያደረገ ጥቃት ስለመፈጸሙም ተናግረዋል።
በሃይማኖት አባቶች ላይ እንግልት መፈጸም፣ ቤተ-እምነቶችን መዝረፍና ማውደም፣ ቤተ-እምነቶችን የጦርነት ቀጣና፣ ምሽግ ማድረግ ሁሉ ተፈጽሟል ነው ያሉት።
በአበርገሌ ወረዳ ላይ የምትገኘዋን ጥንታዊቷ ገዳም፣ ደብረ ሐመልማል ባር ኪዳነምሕረት ላይ ያደረሰውን ጉዳትም በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
በዚች ገዳም በእምነቱ አባቶች ላይ እንግልት ደርሷል፣ የገዳሟ የገቢ ማስገኛ ሱቆች እና የቤተክርስቲያኗ ሙዳየ ምጽዋት ሁሉ ተዘርፏል።
በዚህም ከደረሰው ውድመት ባሻገር ገዳሟ ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ዘረፋ እንደተፈጸመባት መዘገባችን የሚታወስ ነው።
ብፁዕ አቡነ በርናባስ ጦርነቱ መቋጫ እንዲያገኝ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በዚህ ጦርነት በሁለቱም ወገን የሚሞተው ሰው ነው ያሉት ብፁዕነታቸው የሕዝብ እልቂት የሚያበቃበትን ጊዜ ማሳጠር ይገባል ብለዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ሰብዓዊም ቁሳዊም ውድመት ደርሷል ያሉት ብፁዕነታቸው ለወገን ደራሹ ወገን ነውና ለተጎዱት ልንደርስላቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ጦርነቱ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ የተሰደደ፣ ጎዳና ላይ የወደቀ፣ ሀብት ንብረቱ ወድሞበት የዕለት ጉርስን የተቸገረ፣ ጧሪ ቀባሪ ያጣ አዛውንት፣ አሳዳጊም የሌለው ሕጻን እንዲፈጠር አድርጓል።
በመላው ኢትዮጵያ፣ በዓለም ሁሉ ያሉ ለጋሾች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በሞራልም በገንዘብም ድጋፍ እንዲያደርጉ ብፁዕነታቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼