
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለጥበብ ደቀ መዝሙሯ ኾነላት፣ አልጋ ወራሽ ኾናት፣ በከበረው ዙፏኗ ላይ ተቀመጠባት፣ ለተወደዱ ዓመታት በተወደደ ለዛው ነገሠባት፣ በሚያሳስር ፍቅር ልብን ገዛት፣ በማይጠፋ ትዝታ ነብስን አስጨነቃት። ከጥበብ ከምንጯ እየጨለፈ በምድር አረሰረሳት፣ ልብ በተባለ ማሳ ውስጥ መልካም ዘሯን ዘራላት፣ ዘርቶ አሳደገላት፣ አሳድጎ መልካም ፍሬ አሳያት። እሸት አቅምሶ አስደሰታት፣ በመልካም አንደበቱ አስጌጣት፣ በየሰው ልብ አዳረሳት፣ አሽሞነሞናት፣ ከፍ ከፍ አደረጋት፣ ስሜት በሚንጡት ግጥሞቹ፣ ልብን በሚሰውሩት ዜማዎቹ እያዋዛ ጥበብን አኮራት። ጥበብም በደቀመዝሙሯ ላይ አደረች፣ ደቀ መዝሙሯን አከበረች፣ ክብሯን በደቀ መዝሙሯ ላይ ገለጠች፣ ኃያልነቷን አሳየች፣ በየሰው ልብ ውስጥ በደስታ ዘለቀች፣ ዳግም ላትወጣ ተደላድላ ተቀመጠች።
በለጋ እድሜው በጥበብ፣ ለጥበብ አደረ። እስከ እስትንፋሱ መጠናቀቂያ ድረስ ላይለያት ቃል ኪዳን አሰረ፣ እርሷ በሰጠችው መንገድ ይጓዝ ዘንድ መንገድ አሰመረ። ጥበብም ተቀበለችው፣ ተቀብላ አሳደገችው፣ አሳድጋ አጎመራቸው።
በተሰጠው ጥበብ ስንኝ እየቋጠረ ሕዝብን በፍቅር አስተዳደረ፣ ዜማ እየደረሰ ትውልድን በመውደድ አሰረ። እርሱ ጥበብን አልከዳትም፣ ከክብሯም አላወረዳትም፣ አኮራት፣ አከበራት፣ ኃያልም አደረጋት እንጂ። ስላከበራት አከበረችው፣ ስለ ጠበቃት ጠበቀችው፣ ስለወደዳት ወደደችው።
በሁሉም መወደድ ምን አይነት መታደል ነው? በሁሉም መመረጥ ምን አይነት መባረክ ነው? ለሁሉም ማዘንስ ምን አይነት መከበር ነው? ለብዙዎች ያልተሰጠች ጥበብ ተሰጠችው፣ ለብዙዎች ያልተቸረች ጎሮሮ ተቸረችው፣ ለብዙዎች ያልታደለች ለዛ ታዳለችው። በሚዛኗ ለክታ ብዙዎችን ከአጠገቧ ያራቀችው ጥበብ እርሱን ግን በልጅነት አቀረበችው። ከፍ ከፍ አደረገችው፣ አብዝታ ወደደችው፣ ያገኘ እጅ የሚነሳለት፣ የተመለከተው ሁሉ የሚሳሳለት፣ የሰማው ሁሉ በደስታ የሚያነባለት አደረገችው።
ተሰረቅራቂ ድምፁን የሰሙት በደስታ አነቡለት፣ በፍቅር አለቀሱለት፣ በአሻገር ኾነው ናፈቁት፣ ስሙን ደጋግመው አነሱት፣ ክበር አሉት። ብዙዎች አንደኛው ዜማውን ሰምተው ወደሌላኛው ለመሄድ ይቸኩላሉ፣ ወደ ሌላኛው ሲሄዱም የሰሙትን መልሰው ይናፍቃሉ። እየደጋገሙ ሰሙት፣ እየደጋገሙ አደነቁት፣ እየደጋገሙ ተደሰቱበት፣ በትዝታ ሄዱበት፣ ታሪክ ተማሩበት፣ ሀገር አወቁበት፣ በጀግንነት ተነሱበት። እርሱ ዘፋኝ ብቻ አይደለም። እየዘፈነ ታሪክ ይናገራል፣ እየዘፈነ ሀገር ያሳየል፣ እየዘፈነ ጀግንነት ያስተምራል፣ በሀገር ፍቅር ያቃጥላል፣ ለአንድነት ያስነሳል እንጂ።
ኢትዮጵያን አብዝቶ ይወዳታል፣ በዜማና በግጥሞቹ ያነሳታል፣ ጌጦቿን ይጠራላታል፣ ጀግኖቿን ያደንቅላታል፣ ልጆቿን ያጀግንላታል፣ በአንድነት በፍቅር ያስተሳስርላታል፣ ታሪኳን ይዘክርላታል። በለጋ እድሜው አዜመላት፣ በወጣትነቱ አሰባት፣ ተቀኘላት። ሀገሩን እየወደዳት፣ ጥበብን እያከበራት ኖረ።
የተገኘው ከካህናት ወገን ነው። የእርሱ ዘመዶች ኪዳን አድራሾች፣ ቅዳሴ ቀዳሾች ናቸው። በዚያ ቤት ውስጥ ልብን የሚያርድ ዜማ መስማት የተለመደ ነው። ልጆችም የካህናቱን መንገድ ይከተላሉ፣ ፈርዓ እግዚአብሔርን በልጅነት ይማራሉ። አባቱ እንደ ዘመዶቻቸው ሁሉ ካህን ናቸው፤ ቄስ አፈወርቅ መንግሥቱ። እናቱ ደግሞ አገርነሽ ዋሴ ይባላሉ። አባቱ ቄስ መንግሥቱ ፈጣሪያቸውን በክህነት እያገለገሉ እያለ ሀገር በጠላት ተወረረች በተባለ ጊዜ ዘመቻ ሄደው ወታደር ኾኑ። ይህ ነው በቤተ ክህነትን በቤተ መንግሥትን መመረጥ። ከውትድርና መልስ መቀደሱና ታቦት መሸከሙ ቢቀርባቸውም በደግነት ከመኖር ያገዳቸው የለም። በአያት፣ በአጎት በካህን በተመላ ቤተሰብ ውስጥ አንድ ፍሬ ተገኘ።
አቶ አፈወርቅ እና ወይዘሮ አገርነሽ ከአብራካቸው መልካም ልጅ ተሰጣቸው። መልካም ልጃቸውን የተሰጡት በጎንደር አዘዞ ነበር። ትንሹ ስጦታቸው የሦስት ወር ልጅ እያለ ወደ ደብረ ታቦር አቀኑ። የብላቴናው እድገትም በጥንታዊቷ ከተማ በደብረታቦር ኾነ። ጥንዶቹ ከአብራካቸው የተገኘውን ልጅ ተገኔ ሲሉ ጠሩት። እኒያ ባለ ጥበብ አባቱ አንተ ለእኔ ተገን ነህ፣ ለቤተሰቡም ተገን ነህ ሲሉት ነበር ተገኔ የተባለው። ተገን ያስጠልላል፣ ተገን ይከልላልና። ተገኔ በተሰኘው ስሙ ያገኘ ይጠረዋል፣ እየመረቀ ይስመዋል፣ የስሙን ምስጢር ይኖር ዘንድ ይመርቀዋል። በካህናት በተከበበ ቤተሰብ ውስጥ የተገኘው ብላቴና በለጋ እድሜው ፆም እየፆመ ቅዳሴ እያስቀደሰ አደገ። ካህናቱ ሲያዜሙ በለጋ እድሜው ጥበብን በምትናፍቅ ነብሱ ያዳምጥ ነበር። ከደብሩ አፀድ የሚንቆረቆር ዜማ ሲሰማ ኖረ። ያን ዜማም በልቡ ውስጥ አኖረ።
ዘመኑ የደርግ ሥርዓት የመጨረሻው ነበር። ታናሹ ብላቴና እትብቱ ወደተ ቀበረባት አዘዞ አቀና። በለጋ እድሜው በአራተኛ ሜካናይዝድ ክፍል ጦር ውስጥ የኪነት ቡድን አየ። ሕልሙን ይኖር ዘንድ መዝፈን እችላለሁ አላቸው። አዘፈኑት፣ እውነትም ይችላል። ወድደው ተቀበሉት። ተንከባክበው አሳደጉት። በአጭር ጊዜ በክፍለ ጦሩ ተወደደ። በዚያ እድሜው ብዙዎች የተደነቁበትን ሥራ እያቀረበ መድረኩን ናኘበት። ትንሹን ድምፀ መረዋ እያቀፉ ሳሙት። እየሳሙ መልካም እድል ተመኙለት። ደርግ ዘመን ተፈፀመ። አዲስ መንግሥት ሀገሩቱን ያዘ። ብላቴናው የነበረበት ጦርም ፈረሰ። ጦሩ ሲፈርስ የጥበብ ሥራዬንም ልተወው አላለም። ሌላ እድል ሞከረ እንጂ።
ብላቴናው አባት እና እናቱ ያወጡለት ስም አብሮት አልዘለቀም። የቀደመ ስሙን የሚያስረሳ በዚያም ስም ከፍ ብሎ የሚታወቅበት ስም ተቸረው። ስሙን ስጡኝ ብሏቸው አልሰጡትም፣ በቀደመው ስሜ አልጠራም ብሏቸውም አይደለም አዲስ ስም የሰጡት። በለጋ እድሜው ሲሠራው የነበረው ሁሉ ስሙን ይቀይሩለት ዘንድ አስገደደ እንጂ። ማዲንጎ አሉት። ማዲንጎ ለየት ያለ ስም ለየት ላለ የድምፅ ባለቤት ተሰጠ። ከክፍለ ጦሩ መፍረስ በኋላ ማዲንጎ ወደ ባሕርዳር ሄደ። በዚያም የሕይወት ጥሪውን አስቀጠለ። ወደ አዲስ አበባም ተሻገረ። ከዚያ በኋላማ ማዲንጎን ማን ይዞ ያቆመዋል፣ ማንስ ከሩጫው ያዘገየዋል። ማዲንጎ እያበበ መጣ። ወፈር ብሎ ከጉሮሮው የሚስረቀረቀው ድምፁ በጀሮ እየገባ በልብ ውስጥ መንሳፈፍ ጀመረ።
አስቀድሜ ጥበብን ወደድኳት፣ በመቀጠል ጥበበኞቹን ወደድኳቸው ይላል ያ ባለ መልካም አንደበት። በድንገት የሚመጣ ለውጥ ጥሩ አይደለም፣ ለውጥና እድገት በልፋት ሲሆን መልካም ነው። ከወታደር ጋር ነው ያደኩት፣ ወታደር በአንድ ላይ ይበላል፣ በአንድ ላይ ይተኛል፣ አንድ ላይ ይሞታል፣ እኔም ብቻዬን መብላት አልወድም። በመልካም ባሕሪ ታንፀህ ስታድግ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ ትሠራለህ ይላል ድመፀ መረዋው ማዲንጎ።
ታሪክ፣ ባሕል፣ እሴት አንድነት እና ኢትዮጵያዊነት በሚገልፁ ሥራዎቹ ስሙ ገነነ። በልጅነት እድሜው ተገኔ ያሉት አባቱ የልጃቸውን ተገን አገኙ። ከፍ ብሎ ለቤተሰቦቹ ተገን ኾናቸው። የስሙን ምስጢር ተገን ኾኖ አሳያቸው። ማዲንጎ ትናንቱን ያከብራል፣ በሥራዎቹ ይኮራል፣ ሰዎችን ይወዳል። የእናት አባቴን ውለታ የመክፈል ግዴታ አለብኝ፣ ለእነርሱ ትልቅ ክብር አለኝ፣ እናትና አባቴን በጣም እወዳለሁ፣ እህት ወንድሞቼንም በጣም እወዳቸዋለሁ ይላል ነበር። በክብር ላሳደጉት ወላጆቹ ኖረላቸው። እርሱ ለቤተሰቦቹ ብቻ ሳይሆን ለተቸገሩት ሁሉ ደረሰላቸው፣ በቀና ልቡ አፅናናቸው።
መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፣ እኔን ስላላስከፋኝ እግዚአብሔር ይመስገን፣ እግዚአብሔር ጤና ከሰጠኝ ተወዳጅ እና ብዙ ዘፈን ቢኖረኝ ደስ ይለኛል ይል ነበር። ዳሩ ተወዳጅነት እንጂ ረጅም እድሜ አልተሰጠውም።
“ስወድላት” የተሰኘው አልበሙ በወጣ ጊዜ አነጋጋሪ ኾነና ስለ ዝናህ ምን ትላለህ ሲባል “ዝናን የመሸከም ጉልበት ይስጠን እያልን እንሠራለን” ነበር መልሱ። ዝናን በደንብ ያልያዙት ይወድቃሉ፣ ወድቀውም ይሰበራሉና። እርሱ ግን ዝናን በጥንቃቄ ያዛት። ተከብሮም ኖረባት።
ማዲንጎ የዘፋኞቹን መሥፈርት ካሟሉ ወጣቶች መካከል አንደኛው ነው፣ ዘፋኝነት የገባው ነው፣ በፈተና ውስጥ አልፎ ብርሃን ኾኗል ይሉታል የሙያ አጋሮቹ። በለጋ እድሜው ጀምሮ ለጥበብ ራሱን የሰጠው ማዲንጎ በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ጎላ ያለ አሻራውን አሳረፈ። ጥበብን ኖሮባት አደመቃት፣ እርሱን ያዩ የእርሱ ተከታዮች ድምፁን እየሰሙ ወደ ጥበብ በር ነጎዱ። ማዲንጎ በዜማው የመንፈስ በሽታ ያደረባቸውን አከማቸው። የተጨነቁትን አፅናናቸው።
በማዲንጎ ፍቅር የተለከፉት፣ በማዲንጎ ዜማ ጭንቀታቸውን የረሱት፣ በማዲንጎ ዜማ ፍቅራቸውን ያጣጣሙት፣ ነገን በተስፋ የተመለከቱት፣ አንድነትን ያዩት፣ ሠንደቃቸውን ያከበሩት፣ ኢትዮጵያን የዞሩት ዛሬ ላይ አልታደሉም። ዛሬ ልባቸው ተሰብራለች፣ ዛሬ ጆሯቸው መሪር ነገርን ሰምታለች፣ ዛሬ ላይ ዓይናቸው እንባን ታፈስሳለች። በሌላ ዜማ በስስት የጠበቁት፣ የሞቱን መርዶ ሰሙት።
ኢትዮጵያ እየወደደችው ተለያት፣ እየናፈቀችው ራቃት፣ እየጠበቀችው ጠፋባት፣ እየሳሳችለት፣ እየተጣራችው ዝም አላት።
ሀገሩ ተነካች በተባለች ጊዜ ወደ ጦር ሠራዊቱ ዘምቶ አበረታትቷል፣ በሙዚቃው ወኔ የሀገር ፍቅርን፣ ለሀገር መሞትን፣ ለሀገር መሰዋትን አስተምሯልና ልጄ ወዳጄ ወዴት አለህ አለችው። በእርሱ ዜማ የተደሰቱት፣ የሀገር ፍቅርን የተማሩት፣ ለሀገርና ለሕዝብ የሚኖሩት ጀግኖችን ለምን ጥለህን ትሄዳለህ የት ነህ አሉት።
እርሱ ግን መልስ ሳይሰጥ አሸለበ። እስትንፋሱ ተቋርጣለች፣ እጅና እግሩ በክር ታስራለች እና ሲጠሩት ዝም አለ። እርሱ ግን በእኩለ ቀን መተኛትን፣ በአፍላ እድሜ መሰናበትን፣ እየተወደዱ መሞትን፣ እየተናፈቁ አፈር መልበስን ናፈቀ መሰለኝ ሳይታሰብ ላይመለስ ጋደም አለ። ዝናውን እንጂ ሞቱን ማንም እሰማለሁ ብሎ የጠረጠረ አልነበረም። ሞት እንደ ሙላት ደርሶ ተወዳጁን፣ ባለ ተስፋውን ጥበበኛ ይዞት ጠፋ አንጂ።
ሰው እፀ ከንቱን ይመስላል። እፀ ከንቱ ዕለቱን በቅላ፣ ዕለቱን አብባ አፍርታ ደርቃ ወድቃ ታድራለች። የሰው ሕይወትም በዚህ ትመሰላለች። ሳይጠገብ ያልፋል፣ ሲወደድ ይጠፋል፣ አበባው ይረግፋል። የሀገሬው ሰው ሰው በሞተ ጊዜ ሙሾ ሲደረድር፣ የሐዘን ስንኝ ሲቋጥር እንዲህ ይላል።
“ክምር ከማሪ እና እግዜር አንድ ናቸው፤
መልሰው ሊያፈርሱት ምን አደከማቸው?” አዎን መልሰው ሊያፈርሱት ምን አደከማቸው? ለምን አስዋቡት? ለምን አስወደዱት? ዘላለም ላያስቀምጡት ከሚወደው ጋራ ላያኖሩት ለምን አሳመሩት?
የተወደደችው የማዲንጎ ልሳን ዳግም ላትሰማ ምድርን ተሰናብታለች። ወደ ናፈቋት ጀሮ ላትደርስ ላትመለስ ኮብልላች። ሰውን ወስዶ የማይረካው መቃብር ያን የመሰለ እንቁ ለመዋጥ ተከፍቶ እየጠበቀው ነው። የሚወዱት፣ የሚሳሱለት፣ የሚያደንቁት እንባ እንደ ጎርፍ እያፈሰሱ አፈር ሊመልሱበት፣ ድንጋይ ሊጭኑበት፣ ዳግም ላያገኙት ሊሰናበቱት ነው። ጥበብ ደቀ መዝሙሯን አጥታለች፣ መከበሬያዋን ተነጥቃለች።
“በል ወንድማለም እንሰናበት፣
አንተም ወደ አፈር እኛም ወደቤት፣
ቀናችን ደርሶ እስክንመጣበት።”
እንዳለ ፎካሪ አንተ በጥበብ የነገሥክ ኾይ ማንባቱ፣ ደረቅ መድቃቱና ፀጉር መንጨቱ ጋደም ካልክበት አላነቃኽምና ደህና ሁን እንልሃለን። ነብስህ በዘላለማዊት ዓለም በክብር ትረፍ እያልን እንሰናበትሃለን። አንተ ሞቶ የማይቀበር፣ ወድቆ የማይሰበር፣ ከአባት የተሠጠህ ወንበር፣ ከጥበብ የወረስከው ስም አለህና ከመቃብር በላይ እየታወስክ፣ እየተወደድክ ትኖራለህ።
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ