
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግስታቱ ድርጅት 77ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ እና በሰሜኑ ጦርነት ጉዳይ አቋሟን ያስረዳችበት እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በጉባኤው ኢትዮጵያ ወሳኝ ያለቻቸውን አቋሞች ማስረዳቷን አንስተዋል።
በተለይም ከህዳሴ ግድብ እና ሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ አቋሟን አስረድታለች ነው ያሉት።
በዚህም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኩል የሰሜኑ ጦርነት በሰላም ለመፍታት እንዲሁም የህዳሴ ግድብን በተመለተ የጋራ ተጠቃሚነት ጋር በተገናኘ ተጠቃሚነቱም መፍትሄውም አፍሪካዊ ስለመሆኑ ያስረዳችበት መሆኑን ገልፀዋል።
ዓለም ላይ ያለን ችግር ለመፍታት ከተናጠል አካሄድ ይልቅ የጋራ ጉዞ እንደሚያስፈልግ ያስገነዘበችበት ነው ብለዋል።
ከጉባኤው ጎን ለጎንም የሀገራት መሪዎች ጋር ግንኙነት በማድረግ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደነበሩ ጠቅሰው በዚህም ከ20 በላይ ሀገራት ጋር መወያየት መቻሉን አንስተዋል። መረጃው የፋብኮ ነው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!