
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) ስለ አማራ ክልል ሕዝብ የተነገራቸው እና በአካል ያረጋገጡት የተለያዬ መሆኑን ከትግራይ ክልል የመጡ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡
የትግራይ ክልል መንግስት “በ2012 የትምህርት ዘመን ዓዲስ የተመደቡ የክልሉ ተማሪዎች ጥቃት ሊደርስባቸው ስለሚችል ወደ አማራ ክልል አይሄዱም” ማለቱን ቢሰሙም በሕዝቡ ሙሉ እምነት ስላላቸው ለመማር መምጣታቸውን ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ያወጣው መግለጫ የተማሪዎችን በሀገራቸው የትኛውም ክፍል ተንቀሳቅሰው የመማር መብት የሚገድብ፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያንም የሚነጥል በመሆኑ ወደ አማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች መጥተው እየተማሩ እንደሚገኙ አብመድ አረጋግጧል፡፡
መሐሪ ተስፋይ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ነው፡፡ ከትግራይ ክልል የመጣው ተማሪው ደብረ ታቦር ከደረሰ በኋላ አንድ ዕውነት ላይ ደርሷል፤ ስለአማራ ክልል ሕዝብ የተነገረው መረጃ የፈጠራ ወሬ መሆኑንም በሩቁ ሆኖ ሳይሆን ከሕዝቡ ውስጥ ሆኖ አረጋግጧል፡፡
“በነበርኩበት አካባቢ ወደ አማራ ክልል መጥቼ እንዳልማር ያስፈራሩኝ ነበር፤ አሁን ሁሉም የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ላይ በፍቅር ሆነን መማር ጀምረናል፤ ሁሉም ፍላጎቱ ተምሮ መለወጥ እንጂ ሌላ ጉዳይ የለውም፤ ስለሆነም እኛ ተማሪዎች ከአሉቧልታ መራቅ አለብን›› ብሏል፡፡ ስለአማራ ሕዝብ መጥፎነት ሲነገረው እንደቆየ የተናገረው ተማሪ መሐሪ “የአማራ ሕዝብ በመጥፎ እሴት እና በጥላቻ ሳይሆን ሀገር ወዳድ መሆኑን በማወቃችን በክልሉ ለመማር መጥተናል” በማለት ስለ ዕውነታው መስክሯል፡፡
ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገችው ሌላኛዋ ከትግራይ ክልል የመጣችው የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ከምዝገባ ጀምሮ ያለው ሂደት ፍጹም ሰላማዊ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ወደ አማራ ክልል እንዳትመጣ ስጋት ተፈጥሮባት እንደነበር፣ ከቦታው ተገኝታ እንዳረጋገጠችው ግን የሰማችው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ለአብመድ አስተያዬት ሰጥታለች፡፡
ከትግራይ ክልል የመጡ 31 የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ትምህርታቸውን አየተከታተሉ እንደሚገኙ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ባለው ባዬ (ዶክተር) ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ተማሪዎች የኢትዮጵያ ልጆች እንደመሆናቸው ያለመድሎ እንደሚስተናገዱም አረጋግጠዋል፡፡ “እንኳን የሀገሪቱን ዜጎች ቀርቶ ከደቡብ ሱዳን ተማሪዎችን ተቀብለን እያስተማርን ነው” ያሉት ዶክተር ባለው ተማሪዎቹ ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን እየተማሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
“አንድ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ዓላማው የፖለቲካ እና የኃይማኖት አጀንዳ በማራመድ ብጥብጥ መፍጠር ሳይሆን በሰላም ተምሮ ሀገሩን እና ራሱን መጥቀም መሆን እንዳለበት የማስገንዘቢያ እና የስነ ልቦና ግንባታ ስልጠና ሰጥተናል” ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ