የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አቶ ደመቀ መኮንን ከተመድ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በኒውዮርክ ባደረጉት ውይይት አስገነዘቡ።

141
ባሕር ዳር፡ መስከረም 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ጋር በኒውዮርክ ተወያይተዋል።
ውይይታቸው ኢትዮጵያ እያካሄደችው ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር እና በታዳሽ ኃይል ልማት ዙሪያ ያተኮረ ነበር።
በውይይቱ አቶ ደመቀ አትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራች መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ረገድ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግር ተጠቃሽ መሆኑን ያነሱት አቶ ደመቀ፤ መርሃግብሩ ከሃገሪቱ ባሻገር ፋይዳው ለአጎራባች ሃገራት ጭምር መሆኑን አብራርተውላቸዋል።
ኢትዮጵያ እምቅ የታደሽ ኃይል ሃብቶቿን በማልማት ምጣኔሃብታዊ እና ማህበራዊ እድገትን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች በማከናወን ላይ እንደምትገኝ በውይይቱ ተነስቷል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከታዳሽ የልማት ኘሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ደመቀ፤ ኘሮጀክቱ ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት በንግግር ብቻ የሚፈታ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ደመቀ፤ ኢትዮጵያ ሁሌም ለንግግር እና ውይይት ዝግጁ መሆኗን አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማትን እውን ለማድረግ እያከናወነችው ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ታዳሽ ኃይል ልማትን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት የመንግስታቱ ድርጅት የአካባቢ ኘሮግራም እንደሚደግፍ የገለፁ ሲሆን የህዳሴ ግድብ አለመግባባት በውይይት የሚቋጭበት ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 77ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እየተሳተፉ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ ጋርም ውይይት አድርገዋል።
ኮሚሽኑ በድርቅ እና ግጭት የተፈናቀሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ለመርዳት እያከናወናቸው ላሉ ተግባራት አቶ ደመቀ ምስጋና አቅርበው፤ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፓ ግራንዴ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት መስራቱን እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
Previous article“የሕወሃት ሽብር ቡድን በአፋር ክልል በንጹሃን ላይ የፈጸመው ግፍ ሰይጣናዊ ተግባር ነው” የሃይማኖት አባቶች
Next articleዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ምርመራ የባለሙያዎች ኮሚሽን ያቀረበውን ሪፖርት በርካታ ሀገራት እንደማይቀበሉት አስታወቁ።