
ባሕር ዳር፡ መስከረም 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕወሃት ሽብር ቡድን በአፋር ክልል ንጹሃንን በግፍ ከመጨፍጨፉም ባለፈ የእምነት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችንም የህዝብ መገልገያ ንብረቶችን በማውደም የፈጸመው ጥፋት ሰይጣናዊ ተግባር መሆኑን የክልሉ የሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኑ በሕዝብና ሀገር ላይ ያደረሰውን ግፍና በደል በግልጽ እየታወቀ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአንዳንድ ምዕራባዊያን ፍላጎት ለማስጠበቅ በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ እያራመደ የሚገኘውን አድሏዊ አካሄድ ተገቢ እንዳልሆነ ነው የሃይማኖት አባቶቹ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያመለከቱት።
ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ችግር በራሳችን እንድንፈታ ሁኔታዎችን ሊያመቻቹልን ይገባል ብለዋል።
ከክልሉ የሃይማኖት አባቶች መካከል ሼክ ሃቢብ ሙስጠፋ ፤ የህወሃት ሽብር ቡድን ባለፈው ዓመት በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ንጹሃንን ሆን ብሎ ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን መፈጸሙን አውስተዋል።
በዚህም ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም አረጋውያን ጭምር በሽብር ቡድኑ ሰይጣናዊ ጥቃት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መገደላቸውን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው ብለዋል።
በተለይ በ”ጋሊኮማ ” ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የነበሩ በርካታ ዜጎች በሽብር ቡድኑ የከባድ መሳሪያ ጥቃት እንደተገደሉ ጠቅሰው፤ በበራህሌ፣ እዋና ሌሎችም አካባቢዎች የፈጸመው ጭፍጨፋ አመላክተዋል።
ይህም ትውልድ ሲያወሳው የሚኖር አረመኒያዊ ተግባር መሆኑን ሼክ ሃቢብ ገልጸዋል።
በድኑ ካደረሰው ዘግናኝ የሆነ ሰብአዊ ጉዳት ባለፈ የእምነት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችንም የህዝብ መገልገያ ንብረቶችን ማውደሙ በግልጽ እየታወቀ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአንዳንድ ምዕራባዊያን ፍላጎት ለመጠበቅ በዝምታ ማለፉ አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የሽብር ቡድኑ በሀገራችንና ህዝባችን ላይ ተጨማሪ መከራ እልቂት እንዲፈጽም እድል የሰጠ መሆኑን በማመልከት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ተመድ ይህንን በፍጥነት አርሞ ጥፋተኛውን በግልጽ በመለየት ሀገሪቱ ለጀመረችው የሰላም ጥረት የበኩሉን ገንቢ ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ሌላው የሃይማኖት አባት ወንጌላዊ አበራ ከበደ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ በየደረሰበት ንጹሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመግደልና በሴቶች አስገድዶ ከመድፈር ባሻገር በእምነት ተቋማቶችን ላይ ጥቃት በመፈጸም በታሪካችን አይተን የማናውቀውን ጸያፍ ወንጀል ፈጽሟል ብለዋል።
ለዚህም በጭፍራና አደአር (ካሳጊታ ቀበሌ) እንዲሁም ሰሙሮቢ ወረዳ የእምነት ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት ጠቅሰዋል።
በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን ጾታዊ ጥቃትና የግፍ ግድያ አለም የሚያውቀው ሃቅ ነው መሆኑን የገለጹት ወንጌላዊ አበራ ፤ ቡድኑ ተስፋ በመቁረጥ የፈጸመው አጥፍቶ የመጥፋት ሰይጣናዊ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ሕዝብም እንደባህሉ በሽብር ቡድኑ የግፍ ጥቃት ለተገደሉ ወገኖቹ በየአካባቢው “ዋይደል”የሚባል ባህላዊ መታሰቢያ ሰርቶ እየዘከራቸው ብቻም ሳይሆን ለመጪ ትውልድም ታሪኩን እንዲያውቅ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ በሕዝብና ሀገር ላይ ያደረሰውን ግፍና በደል በግልጽ እየታወቀ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወንጀሎቹን በመሸፋፈን ኢትዮጵያን ለማዳከም መሞከሩ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
ይህ ሚዛን የሳተ አመለካከትና ግልጽ ወገንተኝነት ለችግሩ መፍትሄ የሚያመጣ ሳይሆን የበለጠ የሚያወሳስብ በመሆኑ ከመሰል አድላዊ ተግባራቸው በመታቀብ ከእውነት ጎን እንዲቆምም ጠይቀዋል።
ባለፈው ዓመታት የሽብር ቡድኑ የክልላችን ህዝብ ላይ ያደረሳቸው ዘርፈ ብዙ ግፍና በደሎች ለመግለጽ የሚዘገንን ፤ ከአንድ ሰብአዊ ፍጡር የማይጠበቅ የአውሬነት ተግባር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሀጂ መሐመድ ደርሳ ናቸው።
ከዚህም ውስጥ የሽብር ቡድኑ በጋሊኮማ ፣ በያሎና በራህሌ አካባቢዎች ሴቶችንና ህጻናትን ሳይቀር በግፍ በመጨፍጨፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን አለም መስክሯል ብለዋል።
ይሁንና አንዳንድ ምዕራባዊያን የቡድኑ ወንጀል በዝምታ በማለፍ የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማስፈጸም ሽፋን መሆኑን ተገቢነት እንደሌለው ገልጸዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው፤ የሽብር ቡድኑ በሕዝብና ሀገር ላይ ያደረሰውን ግፍና በደል በግልጽና በተጨባጭ መረጃ እየታወቀ በተለይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአንዳንድ ምዕራባዊያን ፍላጎት ለማስጠበቅ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እያራመደ ያለውን አድሏዊ አካሄድ በመተው የራሳችንን ችግር በራሳችን እንድንፈታ ሁኔታዎችን ሊያመቻችልን ይገባል ብለዋል የሃይማኖት አባቶቹ።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር
