
ባሕር ዳር፡ መስከረም 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ሕወሃት የተቃርኖ ሃሳብ የሚያራምድን ሁሉ ማጥፋት ከምስረታው ጀምሮ የሚከተለው ስልት ነው ሲሉ የትግራይ ዴሞክራስያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
አሸባሪው ሕወሃት ከምስረታው ጀምሮ በአሻጥር ሲሰራ የኖረ ቡድን እንጂ ለሰላምና አብሮነት ደንታ የማይሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የትዴፓ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሸባሪው ሕወሃት ከጥንት እስካሁን ለራሱ ጥቅም ብቻ እየሰራ ህዝብን በማሰቃየት ቀጥሎበታል ብለዋል።
የሕዝብን ችግርና ስቃይ ለራሱ መጠቀሚያነት በማዋል በጦርነት ሁሌም ዓላማየን አሳካለሁ ብሎ የሚያምን የጥፋት ስብስብ መሆኑን ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኑ በቅርቡ ያዘጋጀውና አፈትልኮ የወጣው የጥፋት ሰነዱ ”ነፃነታችን በክንዳችን” በሚል ባሰፈረው ጽንሰ ሐሳብም አሁንም ሕዝብን ለጦርነትና ለእልቂት ለመማገድ የሚሰራ መሆኑን ያረጋገጠበት ነው ብለዋል።
በሕወሃት የትግል ዘመን በማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሰብአዊ መብት ዙሪያ የተለየ ጥያቄ ማንሳት በጠላትነት ያስፈርጅ እንደነበር አስታውሰው ለዚህ በርካታ ማሳያዎች ነበሩ ብለዋል።
በትግል ወቅት ለእውነት ቆመው ይታገሉ የነበሩ በርካታ ጓዶች በአደባባይ የተረሸኑና ሚስጢራዊ ግድያ የተፈፀመባቸው እንዳሉ አስታውሰዋል።
በመሆኑም አሸባሪው ሕወሃት የተቃርኖ ሃሳብ የሚያራምድን ሁሉ ማጥፋት ከምስረታው ጀምሮ የሚከተለው የፖለቲካ ስልት ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ከሕወሃት የትጥቅ ትግል መስራቾች መካከል አንዱ የነበሩት ዶክተር አረጋዊ በዴሞክራሲ፣ በድርድርና በሰላም የማያምን የጨካኞች ስብስብ በመበራከቱ እሳቸውና ሌሎች ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ታጋዮች ድርጅቱን ቀደም ብለው ለመልቀቅ መገደዳቸውን አስታውሰዋል።
ድርጅቱ ኢትዮጵያን የማስተዳደር እድሉን ባገኘባቸው ዓመታት የዘረፋና የአፈና ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠሉ በሕዝብ ግፊት ከስልጣን መወገዱንም ጠቅሰዋል።
አሸባሪው ሕወሃት በጥፋት አብረውት ሚራመዱ፣ ዓላማውን ከሚደግፉለትና በዘረፋ ሰንሰለት አብረውት ከሚሰሩ አካላት በስተቀር ለሕዝብ ጥቅምና ለልማት መስራት የማይሻ ጥቅመኛ ቡድን መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ ይህንን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከላዩ ላይ እንዲወርድለት መታገል አለበት ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ።
አሸባሪው ሕወሃት በኢትዮጵያ ሰላም ከሰፈነ ለበርካታ ዓመታት በፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን ስለሚያውቅ በጦርነት፣ ሁከትና ትርምስ እድሜውን ለማራዘም እየጣረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው፤ የሽብር ቡድኑን የጦርነት አባዜና ሀገር የማፍረስ እቅድ በጋራ ሆነን ልንመክት ይገባል ብለዋል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር