
ባሕር ዳር፡ መስከረም 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ”ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማጠልሸት የፖለቲካ ተልዕኮ የተሰጠው አካል ነው” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
የኮሚሽኑ ሪፖርት ቀድሞ የተነሳበትን የፖለቲካ ዓላማ በግልጽ ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ተልዕኮ የሰጡትን አካላት ጊዜያዊ የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት እንደተቋቋመ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።
“የተነሳበትን ውሸት እውነት የማስመሰልና የእኔ ብቻ ነው ትክክል እሳቤ ተቀባይነት እንዲኖረው የማድረግ ዓላማ ያለው ነው” ብለዋል።
የኮሚሽኑ ሪፖርት ቀድሞ የተነሳበትን የፖለቲካ አላማ በግልጽ ያረጋገጠ ነው ያሉት አምባሳደሩ በተፈበረኩ ውሸቶች ሰዎችን የተሳሳተ ድምዳሜና አቋም እንዲይዙ የሚያደርጉ መረጃዎች እንዳካተተ ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ተልዕኮ የአደባባይ ሚስጥር ነው ብለዋል አምባሳደር ሬድዋን ባሰፈሩት መረጃ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ከዚህ ቀደም በኮሚሽኑ ዙሪያ በሰጡት አስተያያት ከምስረታው አንስቶ አወዛጋቢ፣ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለውና ከእናንተ በላይ እኔ አውቅላችኋላሁ የሚል አድሏዊ አቋም እንዳለው ገልጸው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየሠራ ባለበት ወቅት ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን ስም የማጠልሸት ተግባር ላይ ቢጠመድም ከተቋቋመው አካል በትብብር ለመሥራት የሚያችሉ አማራጮችን ለመፈለግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል።
ይሁንና ኮሚሽኑ ጭምብሉን በመግለጥ ኢትዮጵያ ላይ በኃይል ፍላጎቱን ሊጭን ተነስቷል ያሉት አምባሳደሩ ይህን ጣልቃ ገብነት በፍጹም አንቀበልም ሲሉ አምባሳደሩ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J