አሸባሪው ሕወሃት በአማራና በአፋር ክልሎች 3 ሺህ 598 ንጹሃንን መግደልን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸሙ ተጠቆመ።

615
ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ሕወሃት በአማራና በአፋር ክልሎች ከህግ ውጪ 3 ሺህ 598 ንጹሃን ሰዎችን መግደልን ጨምሮ በጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸሙ ተጠቆመ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት የጋራ ምርመራ ዉጤቶችን ተከትሎ በኢትዮጵያ መንግስት የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኅይል የምርመራና ክስ ኮሚቴ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲያጣራ መቆየቱ ይታወቃል።
የግብረ ኀይሉ የምርመራና ክስ ኮሚቴ በአፋርና አማራ ክልሎች በሚገኙ ዘጠኝ አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥፋቶችን የምርመራ ውጤት የመጀመሪያ ምዕራፍ ሪፖርቱን ረቂቅ አውጥቷል።
በዚህም በአማራ ክልል፦በወልዲያ፣ ላሊበላ፣ ሰቆጣ፣ ጃማ ወረኢሉ፣ ደሴና ኮምቦልቻ አካባቢዎች እንዲሁም፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በአፋር ክልል እ.አ.አ ከመስከረም 15 እስከ ጥር 31 2021ድረስ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አጣርቷል።
የምርመራና ክስ ኮሚቴው ባደረገው ማጣራት ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ ህግ የጣሱ በጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ በርካታ ጥፋቶችን አሸባሪዎቹ ሕወሃትና ሸኔ መፈጸማቸውን ማረጋገጡን ገልጿል።
በዚህም ከህግ ውጪ 3 ሺህ 598 ሰዎች ተገለዋል፣ 1 ሺህ 315 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ 2 ሺህ 212 ሰዎች የአስገድዶ መድፈርና ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል እንዲሁም 452 ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተነክቷል ሲል ሪፖርቱ አመላክቷል።
ይህ አሰቃቂ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአሸባሪዎቹ ሕወሃት እና ሸኔ አማካኝነት መፈጸማቸውን ገልጿል።
ከህግ ውጪ የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ ሪፖርቱ እንዳመለከተው በወልዲያና አካባቢው ብቻ 1 ሺህ 181 ሰዎች በአሸባሪው ህወሃት ግድያ የተፈጸመባቸው መሆኑን ገልጿል።
በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች አሸባሪዎቹ ሕወሃትና ሸኔ በፈጸሙት ግድያ በሰሜን ሸዋ ዞን 257 ሰዎች እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ 162 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በአፋር ክልል ከፍተኛ ጥፋት ያደረሰው አሸባሪው ሕወሃት የ263 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉንም ሪፖርቱ ጠቁሟል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር
Previous articleአሸባሪው ሕወሃት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት ማድረሱን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next article“ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማጠልሸት የፖለቲካ ተልዕኮ የተሰጠው አካል ነው” አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን