አሸባሪው ሕወሃት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት ማድረሱን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

142
ሰቆጣ፡ መስከረም 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ስቡህ ገበያው ለአሚኮ በሰጡት መግለጫ የሽብር ቡድኑ የሰላም አማራጮችን ወደጎን በመተው ለሦስተኛ ጊዜ በከፈተው ጦርነት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።
የሽብር ቡድኑ በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ፣በጋዝጊብላ ፣በፃግብጂ ፣በዝቋላና በአበርገሌ ወረዳዎች ንጹሃንን በግፍ ገድሏል ፣ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ፈጽሟል ፣ከግለሰብ እስከ መንግሥት ተቋማት ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል ነው ያሉት።
የሽብር ቡድኑ እኩይ ዓላማ አስፈፃሚዎች በሕፃናት ላይ ሳይቀር የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ማድረሳቸውን ነው የተናገሩት።
በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ወለህ ቀበሌ ከአንድ ቤት እስክ አሥር ንጹሃን ሰዎች በግፍ መገደላቸውንም ጠቅሰዋል ዋና አሥተዳዳሪው።
የሽብር ቡድኑ በዝቋላ ወረዳ በተመሳሳይ ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል ነው ያሉት። በሽብር ቡድኑ ወረራ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን የጠቀሱት አቶ ስቡህ፤ የሽብር ቡድኑ ከቀያቸው እስከ ተጠለሉበት የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ እየተከተለ ድጋሜ አፈናቅሏል፣ጥቃትም አድርሶባቸዋል ብለዋል።
በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለማቋቋምና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት አስፈላጊው ርብርብ እንዲደረግም ጥሪ ቀርቧል።
በወለህ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በተፈጸመ ጥቃት የ18 ንጹሃን ሰዎች ህይዎት ማለፉም ይታወቃል።
የሽብር ቡድኑ ሕወሃት በተለይም በወገን ጦር ተመክቶ ሲመለስ በእኩይ ዓላማ አስፈጻሚዎቹ በንጹሃን ላይ እና በተቋማት ላይ ያደረሱት ጥቃትና ውድመት ከፍተኛ ነው ተብሏል።
የሽብር ቡድኑ በሐሙሲት፣ በብርብር፣ በወለህ፣ በቅዳሚት፣ በጸመራ እና በሌሎችም በወረራ በቆየባቸው ጊዜ የጤና ተቋማትን፣ የትምህርት ተቋማትን ፣ የግለሰቦችን ሃብትና ንብረት ፣ ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማትን ዘርፏል፣ አውድሟል ተቋማቱን ከአገልግሎት ውጭ አድርጓል ነው ያሉት።
በዚህም ከ65 ሺህ በላይ ሕዝብ ይገለገልበት የነበረው የጤና ተቋምም መውደሙን ተናግረዋል።
ሕዝብ ጠል የኾነው አሸባሪው ቡድን ሕወሃት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች የግለሰቦችን መኖሪያ ቤት አፍርሷል፣ ለምሽግ ተጠቅሞበታል፣ የእርሻ ቦታዎችን የጦርሜዳ አድርጎ አዝዕርትን አውድሟል፣ የአርሶ አደሮችን እንስሳት ገድሏል ነው ያሉት።
“አሸባሪው ሕወሃት ከሰው ብቻ ሳይኾን ከራሱም፣ ከፈጣሪም ጋር የተጣላ ድርጅት ነው” ያሉት አቶ ስቡህ በደረሰበት ሁሉ ታሪክ ይቅር የማይለው ሰይጣናዊ ድርጊት መፈጸሙን ነው የተናገሩት።
የሽብር ቡድኑ ለሦስተኛ ጊዜ የከፈተው ጦርነት በወገን ጦር እና በደጀኑ ሕዝብ ተመክቶ እንዳሰበው ሳይሳካለት እየሸሸ ነው፣ የሕዝቡ ደጀንነትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ከጠላት ወረራ ነፃ የኾኑ አካባቢዎች ላይ ኅብረተሰቡ መደበኛ እንቅስቃሴውን ተረጋግቶ እየከወነ ነውም ብለዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው ስቡህ ገበያው አያይዘውም በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለማቋቋምና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት አስፈላጊው ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ ቀደም የታየውን መደጋገፍና መተባበር ማስቀጠል ያስፈልጋል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን መልሶ ማቋቋም እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
የክልል መንግሥታት፣ የፌዴራል መንግሥት ፣ ረጂ ድርጅቶች እና ባለሃብቶች በሽብር ቡድኑ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እንተባበር፣ የአገልግሎት ተቋማትን መልሰን በጋራ እንገንባ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ – መስከረም 09/2015 ዓ.ም ዕትም
Next articleአሸባሪው ሕወሃት በአማራና በአፋር ክልሎች 3 ሺህ 598 ንጹሃንን መግደልን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸሙ ተጠቆመ።