
ባሕር ዳር: መስከረም 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያም ሆነ የቀጣናው ሰላም በዘላቂነት የሚረጋገጠው የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ሲጠፋ ብቻ መሆኑን የጐንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተናገሩ። የትግራይ ሕዝብ አሸባሪውን ሕወሓት ቢታገልና ቢያጠፋ ከሌላው ሕዝብ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆንም ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል።
ፕሬዚዳንቱ ዶክተር አስራት አጸደወይን እንደገለጹት የሽብር ቡድኑ ጥቅምት 24 /2013 በሰሜን እዝ ላይ ክህደት በመፈጸም፣ በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት የፈጸመ ሲሆን፤ ከሰሞኑ የጀመረው ጦርነት ሶስተኛ ወረራ ደግሞ ሌላኛው የቀጠለ ጥፋቱ ነው።
ይህ ተግባሩ መቼም ቢሆን ለሰላም ፍላጎት የሌለው፣ የማይሰለጥን ቡድን መሆኑን ያሳየ ነው ያሉት ዶክተር አስራት፤ አሸባሪው ሕወሓት የሰላማዊ ድርድሩን ወደጎን በመተው ለሶስተኛ ጊዜ ወደጦርነት መግባቱ ከስህተቱ የማይማር የአጥፊ ቡድን መሆኑን በተግባር ያሳያል ብለዋል።
ዶክተር አስራት እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ሕወሓት ከስህተቱ ባለመማሩ በርካታ ወገኖች ህይወታቸውን እንዲያጡ፣ የትግራይ እህቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ አባቶቻችንና ወንድሞቻችን የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንዲሆኑ አድርጓል።
ከሠራቸው ሁለት ስህተቶች ሳይማር ሶስተኛ ስህተት ለመፈጸም መነሳቱ በሰላም መኖር የማይችል የጥፋት ቡድን መሆኑን በግልጽ ያሳየ ነው ብለዋል።
“የሚያሳዝነው የትግራይ ሕዝብ ይህን አስከፊና አረመኔ የሆነ ቡድን ማውገዝ አለመቻሉ ነው፤ ትግራይ ውስጥ ያሉት ታፍነውና ተገደው እንደሆነ ይታወቃል፤ አንዳንድ የትግራይ ወገኖቻችን እኩይ ተግባሩን እያጋለጡ በግልጽ የሚታገሉ አሉ” ነው ያሉት ዶክተር አስራት። ይሁን እንጂ ከትግራይ ውጪ በሀገር ውስጥ ያሉና በውጭ ሀገር ያሉት የትግራይ ወንድሞቻችን የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባር ሊያወግዙትና በቃ ሊሉት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ኢፕድ እንደዘገበው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!