መንግሥት በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ላይ ፈጣን እና የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ተፈናቃዮች ጠየቁ።

175

ወልድያ: መስከረም 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሽብር ቡድኑ ሕወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ በከፈተው ሦስተኛ ዙር ወረራ በንጹሃን ወገኖች ላይ ጥቃት ፈጽሟል። ጥቃቱን በመፍራት ከመኖሪያ ቀያቸው በሸሹ ንጹሃን ወገኖች ሃብትና ንብረት ላይም ቡድኑ ዘረፋ እና ውድመት እየፈጸመ መሆኑን የዐይን እማኞች ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ሕወሃት በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በንጹሃን ወገኖች ላይ የግፍ ግድያ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ዘረፋ እየፈጸመ መሆኑን ከጥቃቱ አምልጠው በመርሳ ከተማ አስተዳደር ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የተጠለሉ ወገኖች ገልጸዋል። ተፈናቃዮቹ መንግሥት በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ላይ ፈጣን እና የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸውም ጠይቀዋል።

ወይዘሮ አንሻ ሙሐመድ በራያ ቀቦ ወረዳ የ023 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ላለፉት ሁለት ዓመታት በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በተፈጸመብን ወረራ ከመኖሪያ ቀያችን እየተፈናቀልን ለከፋ ሰብዓዊ ጉዳት ተጋልጠናል ብለዋል። ወይዘሮ አንሻ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በድንገት ስለመጡ ለእለት ጉርስ እና ልብስ ሳይዙ ነፍሳቸውን ለማዳን ብቻ እንደወጡም ነግረውናል።

ባለፈው ዓመት ወረራ የሞቱት ሞተው የቀሩት ሃብት እና ንብረታቸው ተዘርፎ በእርዳታ ማሳለፋቸውንም ገልጸዋል። ዘንድሮም በተመሳሳይ ወቅት የሽብር ቡድኑ ወረራ በመፈጸሙ የነበራቸው የዕለት ጥሪት ሳይቀር መዘረፉን ጠቅሰዋል።

መንግሥት ችግራችን አይቶ የማያዳግም እርምጃ ይውሰድልን ሲሉም ተማጽነዋል።

የሽብር ቡድኑን ድንገተኛ ወረራ ለማምለጥ ቀያቸውን እንደለቀቁ የነገሩን ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሽሽግ ከበደ በሽሽት ላይ ህጻናት በጥይት እና ውኃ ሙላት ሕይዎታቸውን እንዳጡ ነግረውናል። ያልሸሹት ሴቶችም ባለቤትሽ ያለበትን ተናገሪ፣ የተደበቀ ሃብት እና ንብረት አሳይ እያሉ አስገድዶ መድፈር እና ድብደባ እየተፈጸመባቸው ነው ብለዋል።

በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ዘረፋ፣ ግድያ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን በመርሳ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ያገኘናቸው አቶ አህመድ ሽኩር ነግረውናል። በቅርቡ በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በተፈጸመው ወረራ የቁም ከብት ተነድቷል፤ ፍየሎቻችንም ታርደው እየተበሉ ነው ብለውናል። በበርሃ ከብት ይዘው ያሉ እረኞች መውጫ አጥተው መታገታቸውን የነገሩን አቶ አህመድ መሸሽ ባልቻሉ ንጽሃን ላይም ድብደባ እና ግድያ እየተፈጸመ ነው ብለዋል። መንግሥት በአስቸኳይ በታጣቂዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።

በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ምክንያት በመርሳ ከተማ አስተዳደር እና ውርጌሳ በሚገኙ 12 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ከ13 ሺህ 200 በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleየአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ሐሙሲት ቀበሌ የሚገኘውን ታጋይ ሰርክዓለም ትዛዙ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤትን አወደመ።
Next article“የኢትዮጵያም ሆነ የቀጣናው ሰላም በዘላቂነት የሚረጋገጠው አሸባሪው ሕወሓት ሲጠፋ ብቻ ነው” ዶክተር አስራት አጸደወይን