የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ሐሙሲት ቀበሌ የሚገኘውን ታጋይ ሰርክዓለም ትዛዙ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤትን አወደመ።

210

ሰቆጣ: መስከረም 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ሐሙሲት ቀበሌ ታጋይ ሠርክዓለም ትዛዙ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤትን አውድሟል። የትምህርት ቤቱ ተወካይ ርእሰ መምህር አበርሃም አበበ ለአሚኮ እንደተናገሩት ትምህርት ቤቱ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል።

የሽብር ቡድኑ ትምህርት ቤቱ ከተመሠረተበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ያሉ ሰነዶችን ሁሉ ሙሉ በሙሉ አውድሟል ብለዋል። የተማሪዎችን ቤተ-መጽሐፍት፣ ቤተ-ሙከራ፣ መማሪያ መጽሐፍት፣ ኮምፒተሮች፣ ፕላዝማዎች፣ የተማሪዎችን መቀመጫ ወንበሮች፣ ጠረጴዛና ሌሎችም የትምሀርት ቁሳቁስ ሁሉ ዘርፏል፣ አውድሟልም ነው ያሉት መምህር አብርሃም።

ትምህርት ቤቱ ከ9ኛ ከፍል እስከ 12ኛ ክፍል ከ900 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነበር ያሉት መምህር አብርሃም በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ደግሞ ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር እቅድ ነበረው ብለዋል።

የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በወረራ በቆየባቸው ሁሉ ህዝብን አንገት ለማስደፋ፣ የጥፋት አሻራውን አሳርፏል ያሉት ደግሞ የትምህርት ቤቱ የወላጅ መምህር ኅብረት አባል ሃምሳ አለቃ አበራ ደምሴ ናቸው።
በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተገነባውና የልጆቻችን ፍሬ ያየንበት ትምህርት ቤት በዚህ ሁኔታ ወድሞ መቅረት የለበትም፣ በትብብር መልሰን ልንገነባው ይገባል ነው ያሉት።

የቀረው የትምህርት ቤቱ ሕንጻ ነው ያሉት የትመህርት ቤቱ ተወካይ ርእሰ መምህር አብርሃም አሁን በአለበት ሁኔታ እንደሀገር በተያዘው የትምህርት ማስጀመሪያ መርኃግብር መሰረት ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን መጀመር እንደማይችል ተናግረዋል።

አሁን ላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ መመዝገብና ትምህርት ማስጀመር የሚያስችል ሁኔታ የለም የሚሉት ርዕሰ መምህሩ የተማሪዎች ሰነድና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ሁሉ በሽብር ቡድኑ ወድመዋል ነው ያሉት።

ትምህርት ቤቱን ወደ ነበረበት የመማር ማስተማር ሥራው ለመመለስ መንግሥትም ኾነ ለጋሽ ድርጅቶች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ

ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleጣና ፎረም በመጭው ጥቅምት ወር አጋማሽ በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል።
Next articleመንግሥት በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ላይ ፈጣን እና የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ተፈናቃዮች ጠየቁ።