
ሁመራ: መስከረም 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጀግና ልጅ ሀገሩን ያስከብራል፣ የጀግና ልጅ ዳር ድንበሩን ይጠብቃል፣ የጀግና ልጅ ሠንደቁን ከፍ ያደርጋል፣ የጀግና ልጅ ለቃል ኪዳን ይኖራል። በመከራ ዘመን ፀንተዋል፣ በእሳት ተፈትነው ድል አድርገው ወጥተዋል፣ ድል መለያቸው፣ አሸናፊነት መገለጫቸው ነው። ከዘመን ዘመን ያለ መሰልቸት ጠረፍ ጠብቀዋል፣ ሀገር አጽንተዋል፣ ባንዳና ሰላቶን ቀጥተዋል፣ ኮርተው ወገናቸውን አኩርተዋል።
በዚያ በረሃው እንደ እሳት በሚናደፍበት፣ ጠላት ዓይኑን በማያነሳበት፣ ሀገር ለመድፈር በሚሞክርበት እና በሚቋምጥበት ምድር እልፍ ጀግኖች አሉና ጠላት አንገቱን ደፍቶ ይኖራል። ተመኝቶ ይቀራል። እንደ እሳት የሚያቃጥሉትን፣ እንደ አንበሳ የሚያደቅቁትን፣ እንደ ነብር የሚቆጡትን፣ ተኩሰው መሳት የማያውቁትን፣ አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት የሚሰጡትን ጀግኖች አልፎ ሀገር መውረር ወሰን መድፈር አይቻለውም። በማይስተው አፈሙዛቸው፣ በማያብለው ጠመንጃቸው ተመልከት እያሉ እየመቱት ይኖራሉ። በጀግንነታቸው ይከበራሉ ። በጀግንነታቸው ያስከብራሉ።
በጦርነት ጊዜ ከእነርሱ በላይ አተኳኮስ፣ በሰላም ጊዜ ከእነርሱ በላይ አስተራረስ የት ተገኝቶ። ጠረፍ እየጠበቁ ያርሳሉ፣ ነጭና ጥቁሩን ያመርታሉ፣ በወተትና ማር ይቀማጠላሉ። እያረሱ ጠረፍ ይጠብቃሉ፣ ሀገራቸውን የተመኘውን በአሻገር ይመልሳሉ፣ ግንባር መትተው ይጥላሉ። ጠላታቸውን አሳምረው ይቀጣሉ። ለሀገር መሞት ክብራቸው፣ ለሀገር መቁሰል ጌጣቸው ነው። ጠመንጃቸውን ወልውለው፣ ሳንጃቸውን ስለው፣ ትጥቃቸውን አሳምረው፣ የማይሻር ቃል ኪዳን አሥረው አትንኩን ይላሉ። በፍቅር እንጂ በጦር የሚነካቸው አይወዱም። በጥል ለነካቸው ጦር ላዘመተባቸው ጠላት ወዮለት በሚያነድደው ክንዳቸው ያነድዱታል፣ በሚያቃጥለው ክንዳቸው ያቃጥሉታል።
በፍቅር ለመጣ በፍቅር ይቀበሉታል፣ በጠጅና ማር ያቀማጥሉታል፣ ጮማውን እየቆረጡ ያስተናግዱታል፣ ስሞት አፈር ስኾን እያሉ ያጎርሱታል። የጀግኖች ሥፍራ በጠላት አይሞከርም። ምሽጋቸው አይደፈርም፣ ጠላት እነርሱ ባሉበት አይቀርብም።
“ምን ያበደ ነው ምን የሰከረ
የጀግናን ምሽግ የሠረሠረ
የክላሽ ጥይት ጠጥቶ አደረ” እንደተባለ የእነርሱን ምሽግ የሠረሠረ ጥይት ይጎነጫል፣ እርሳስ ይጎርሳል፣ ዳግም ላይመለስ ያሸልባል፣ እሳት ያለበትን ምሽግ መሠርሠር አይታሰብም አይሞከርም።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ጀግኖች ሀገር በጠላት እንዳትደፈር በተጠንቀቅ ሲጠብቁ ኖረዋል፣ በደምና በአጥንታቸው የሀገራቸውን ሠንደቅ ከፍ አድርገዋል፣ ባንዳና ሰላቶን ሲቀጡ ኖረዋል። እነዚህ የጀግና ልጆች፣ የጠረፍ አጥሮች ዛሬም ከአባቶቻቸው በወረሱት ጀግንነት ጠረፍ እየጠበቁ፣ ሀገራቸውን እያስከበሩ ነው። ጀግኖቹ ከውጭና ከውስጥ የሚነሳን ጠላት እየቀጡ ይኖራሉ። ለሀገራቸው ክብር ውሎና አደራቸው በበረሃ ኾኗል።
ጀግኖቹ በሀገር ላይ ጦርነት የከፈተውን የሕወሓት የሽብር ቡድን በጀግንነት እየመከቱት ነው። ቀደም ሲል በማይካድራ ንፁሐንን ጨፍጭፎ የሸሸው የሽብር ቡድኑ ታጣቂ የሳምሪ ቡድን ከሡዳን በኩል ሠርጎ እንዳይገባ፣ በሀገር ውስጥም የሽብር ቡድኑ ወረራ እንዳይፈጽም ጀግኖቹ በየአቅጣጫው በተጠንቀቅ አካባቢያቸውን እየጠበቁ ነው። ከትግራይ ክልል የሚነሳውም ኾነ ከሱዳን የሚመጣው የሽብር ቡድን ወልቃይት ጠገዴን መርገጥ እንደማይቻለው ይናገራሉ። ለምን ካሉ ጀግኖቹ አሳምረው ይቀጡታልና።
በእልህና በቁጣ ጠላትን በጀግንነት እየመከቱ ያሉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሰላም አስከባሪዎችና ሚሊሻዎች የሽብር ቡድኑ በአካባቢው ዝር ማለት እንደማይቻለው ነው የሚናገሩት።
የጀግኖቹ አባል አየነው መንግሥቱ ሚሊሻው በሙሉ ልብ ሀገሬን አላስደፍርም ብሎ ተነስቷል ብለዋል። ድጋሜ ግፍ እንድናይ አንፈቅድም፣ ቀስቃሽ ሳይኖረው በእልህና በወኔ ነው የተነሳው ነው ያሉት። ለግዳጅ ዝግጁ የኾነና ጠላት ዝር እንዳይል እየጠበቀ መኾኑንም አንስተዋል። ስለ ሕወሓት ባሕሪ ለወልቃይት ሕዝብ አይነገርም፣ በደንብ ያውቀዋል፣ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የሕወሓትን ባሕሪ ስለሚያውቅ ተነስ እስኪባል አልጠበቀም፣ ቀድሞ መጥቶ በር ዘግቶ ነው የተቀመጠው ነው ያሉት። ገና በራያ ጦርነት ከፈተ ሲባል ነው በጀግንነት የተነሳው፣ አሁንም በተጠንቀቅ እየጠበቀ ነው፣ ጠላት አንድ እርምጃ ወደፊት አይራመድምም ብለዋል።
የብርጌድ መሪው ቃኘው መኮንን ሚሊሻው በሰላም ጊዜ ገበሬ፣ ሀገር ሲወረር ደግሞ ወታደር ኾኖ የሚኖር መኾኑን ነው የተናገሩት። በሱዳን ጠረፍ ድንበር ለማስከፈት ሞክሮ የነበረውን ጠላት በጀግንነት እንደመከቱትም ገልጸዋል። የሕወሓት የሽብር ቡድን በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን አንረሳውም፣ አጥፊ ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመመከት ተነስተናል ብለዋል። ከሱዳን በኩል እገባለሁ ያለን ጠላት እንደሚቀጡትም ገልጸዋል።
የሻለቃ አዛዡ ሻምበል ፋንታሁን ሐጎስ ለ22 ዓመታት በመከላከያ ሠራዊት ማገልገላቸውን ነው የተናገሩት። የሕወሓት የሽብር ቡድን የአማራ ተወላጆች በመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን እንዳይኾኑ ሲያደርግ እንደነበር ነው ያስታወሱት። የአማራ ተወላጆች ከፍተኛ መኮንን ከኾኑ ምስጢሮቻቸውን ስለሚያውቁባቸው ከፍተኛ መኮንን እንዲደርሱ አይፈልጉም ነበር ነው ያሉት። በሕወሓት የሽብር ቡድን መከላከያ ሠራዊት ሲወጋ ኢትዮጵያ እንደደማች፣ ኢትዮጵያን እንደገደሏት ነው የቆጠርኩት ብለውናል። በሙያዬ ይሄን ኩሩ ሕዝብ እያገለገልኩ ነው፣ ወልቃይት ጠገዴን እንዳይደፍሯት እያደረግን ነው፣ ወልቃይት መቼም አትደፈርም ነው ያሉት።
ዛሬ ላይ ሕወሓትን ለመመከት በመዋጋቴ እንደኔ እድለኛ የለም፣ የእኔ መንከራተት ለሀገር ስለኾነ ደስተኛ ነኝ ብለዋል። ለሕወሓት የሽብር ቡድን ምንም አይነት ርህራሄ እንደሌላቸውም ገልጸዋል። ሕወሓት ለሰላም ዝግጁ አይደለም፣ ማታለያ ነው፣ ክፋታቸውን አይተውም፣ ሰላም ሰላም የሚሉት ጊዜ ሲያጡ ጊዜ መግዣ ነው፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሕወሓትን መመከት ብቻ ነው አማራጩ ብለዋል።
ሌላኛው የሻለቃ አዛዥ አምሳ አለቃ አስተዋለ ዱባለ ሚሊሻው በእዝ ሰንሰለት እየተመራ በጀግንነት ጠላቱን እየመከተ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት። በትጥቅ እና በሥነልቦና ዝግጁ መሆኑን እና አሁን ላይ በሱዳን ድንበር ሊገባ የሚችለውን ጠላት በተጠንቀቅ እየጠበቀ መኾኑን ነው የገለጹት። የዘር ጭፍጨፋ ያደረገን የሽብር ቡድን በሚገባው መንገድ እንቀጠዋለንም ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮማንደር እዘዘው አስናቀው ከአሁን በፊት በሱዳን አምዳይት አድርጎ ሰርጎ ለመግባት ሲሞክር ከርሞ ድባቅ ተመትቶ እንደተመለሰ ነው ያስታወሱት። ለሦስተኛ ዙር የጀመረውን ጦርነትም በጀግንነት እየመከቱት መኾኑን ነው የተናገሩት። በዞኑ ለጠላት የማይደፈር የታጠቀ ኀይል መኖሩንም አስታውቀዋል። የሕዝቡ ደጀንነት የሚደነቅ መኾኑንም አንስተዋል። ሕዝቡ እጅግ የሚያኮራ እንደኾነም ተናግረዋል።
ሠርጎ ገቦችን በቁጥጥር ስር በማድረግ ትግላቸውን በጀግንነት እየመሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። በየትኛውም አቅጣጫ ሊመጣ የሚችልን ጠላት ለመመከት የሚያስችል ቁመና ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል። መዘናጋት ካለ ሀገርና ወገንን እናስደፍራለን ያሉት ኮማንደሩ በተጠንቀቅ ሁሉንም በሮች በመዝጋት ጠላታቸውን እየመከቱ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ሁሉም ሰው ዝግጁ መኾን እንዳለበትም አሳስበዋል።
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J