
ባሕር ዳር፡ መስከረም 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከውኃና ኢነርጅ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ስድስተኛውን የውኃ፣ ውኃ ዲፕሎማሲ እና ኮሙኒኬሽን ፎረም አካሂዷል።
የኢፌዴሪ ውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ኢትዮጵያ እምቅ የውኃ ሀብት እንዳላት ገልጸዋል። 75 በመቶ የሚኾነው የሀገሪቱ የውኃ ሀብት ድንበር አቋርጦ የሚሻገርና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚጋራ እንደኾነ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ድንበርና ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብቶቿን ለመስኖ ማስፋፊያ፣ ለኀይል ማመንጫነት፣ ለዓሳ ሀብት፣ ለቱሪዝምና ለሌሎች አገልግሎቶች ፍጆታ በሚፈለገው መጠንና አግባብ ለማልማት እንድትችል ድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም የትኩረት መስክ እንዲኾን ተደርጓል ብለዋል።
ድንበር አቋርጠው ለሚፈሱ የውኃ ሀብቶች ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረጉ የትብብርና የድርድር ተግባራት ላይ የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ በጥንቃቄ እየተተገበረ ይገኛል ነው ያሉት።
ሀገሪቱ ያሏትን ሀብቶች አልምታ እንድትጠቀምና እንድታድግ እንዲኹም ወደፊት የሚሰነዘረባትን አፍራሽና ከእውነት የራቁ ፕሮፓጋንዳዎች ለመመከት እና ለሌሎች ለማስረዳት ሚዲያውን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አምባሳደሩ አስገንዝበዋል።
በፎረሙ ላይ የውኃና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ ሀገር አቋራጭ ወንዞችና የሚዲያ ሚና፣ የግብጽ የናይል ፖሊሲና ሌሎችንም ጉዳዮች የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበዋል። ጥናታዊ ጽሑፎችን ካቀረቡት መካከል የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ውሂበእግዜር ፈረደ (ዶ.ር) የግብጽ የናይል መዋቅራዊ ፖሊሲ ኢትዮጵያን በተለያየ ቴክኒኮች ማዳከም እንደኾነ አስረድተዋል። በተለያዩ ጊዜያት የግብጽ መንግሥታት ሕዝባቸውን ለመግዛት በተሳሳተ የውኃ ትርክት ላይ የተመሰረተ አካሄድ መከተላቸውን ጠቁመዋል። በመኾኑም ኢትዮጵያ የግብጽን የተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ ለመቀልበስ ጠንካራና ትክክለኛ ዲፕሎማሲን ማመንጨት እንዳለባት አስገንዝበዋል።
ዶክተር ውሂበእግዜር ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ የዓለምን የውኃ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ መገንዘብ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ መነሻ በመኾኗ ወንዙን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባት ገልጸዋል።
ዶክተር ውሂበእግዜር እንዳሉት የሕዳሴ ግድቡን የብሔራዊ ማንነት መገለጫ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የአሁኑ ትውልድ አሻራ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
የግብጽን ሴራ ለመቀልበስ ከውኃ ፖሊሲ ብቻ ሳይኾን ጠቅላላ አካባቢያዊ ሁኔታን መረዳትና ለዚያም ዝግጁ መኾን ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በፎረሙ ከተሳተፉት መካከል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና የዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር እምቢያለ በየነ ኢትዮጵያ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምክንያት የዲፕሎማሲም ኾነ የተግባር ፈተናዎች እንዳጋጠማት ተናግረዋል።
የግብጽን አጀንዳ በመከተል ምላሽ መስጠት ብቻ ሳይኾን ያለውን እውነታ ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J