“ወልቃይት ጠገዴ የጎበዙን ሀገር ያሳደገኝ እኔ የማውቀው ልናገር”

727

ሁመራ: መስከረም 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሚያውቁትን ጠይቋቸው እውነቱን ይነግሯችኋል፣ የተወለዱበትን ጠይቋቸው ያስረዷችኋል፣ የኖሩበትን ጠይቋቸው ታሪክ ይገልጡላችኋል። ብዙዎች እውነታቸው ሰሚ ስላጣች ስለ እውነት ሞተዋል፣ ብዙዎች ማንነታቸው ስለተደፈረች ስለማንነት በዱር በገደል ተሰቃይተዋል፣ ብዙዎች ታሪካቸው ስለ ተነካች የግፍ መዓት ተሸክመዋል፣ ብዙዎች ክብራቸው ስለተደፈረች ስለ ክብር መሪር ሞትን ታግሰዋል።
ስሚ ስላጣች እውነታቸው፣ ስለ ተከበረች ማንነታቸው፣ ስለ ታፈረች ክብራቸው፣ የጎበዝ መውጫ ስለኾነች ምድራቸው፣ ከአባት ስለ ተቀበሏት ቃላቸው ሲሉ ምቾት ረስተው ነፍጥ አንስተው፣ ጫካ ገብተው ተዋግተዋል፣ አዋግተዋል። ለክብር መሞት ጌጥ በኾነበት በዚያ ምድር አያሌ ጀግኖች ለክብር ተሰውተዋል፣ ታሪክ ለልጅ አውርሰው ምድርን ተሰናብተዋል። ታሪክ የወረሰው ልጅም የአባቱን ቃል እየኖረ፣ የአባቱን መሥመር እያሰመረ እውነት ሰሚ እንድታገኝ ታግሏል።
ቃል በማይሻርበት፣ ጀግኖች በሚፈልቁበት፣ ልበ ሙሉዎች በሚወለዱበት፣ ተኩሶ መሳት ነውር በኾነበት፣ ሀገርና ሠንደቅ ከፍ ከፍ በሚልበት፣ ትጥቅ በማይላላበት፣ ፈሪ በማይሰነብትበት በዚያ ምድር ክብርን የሚነካ ከተነሳ ሁሉም በቁጣ ይነሳል። ትጥቄ ሙሉ ነው፣ ጠመንጃዬ ስሉ ነው፣ ጀግንነቱም የእኔ ነው፣ አልሞ መምታቱም ያደኩበት ነው ብለው የሰው ክብር አይነኩም፣ ከራስ ወሰን አልፈው አይሻገሩም፣ ሰውን በማንነቱ አይጫኑም፣ ሁሉም በሀገሩ ይከበር፣ ሁሉም በቀየው ይኑር ይላሉ እንጂ። ወሰን ተሻግሮ፣ ድንበር ሰብሮ በመጣ ጠላት ላይ ግን ምህረት የላቸውም።
በሀገር ላይ የተነሱትን ጠላቶች ሁሉ እየመቱ መልሰዋቸዋል፣ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በተጠንቀቅ ጠብቀዋል፣ ሠንደቋን ከፍ አድርገው አስከብረዋል። ኢትዮጵያን ለጠላት አያስነኩም፣ ሞተው ያስከብሯታል፣ ደምተው ያፀኗታል፣ አጥንት ከስክሰው ጠላቶቿን ያሳፍሩላታል እንጂ። የበረሃዋ ገነት ፣ የተከዜ ዳር ንግሥት፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ። ጀግኖች በእሳት ተፈትነው ታሪክ ሠርተውባታል፣ ነብሳቸውን አስይዘው ስለ እውነት ተዋድቀውባታል፣ ስለ ማንነት ታግለውባታል።
የደርግ ሥርዓት አልቆ አዲስ ሥርዓት ሲመጣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ የጎንደር ክፍለ ሀገር ነዋሪዎች፣ የጎንደር ክፍለ ሀገር ጀግኖች አይተው የማያውቁትን ወሰን ተሰጥቷቸው፣ ከተከዜ ማዶ ወደ ትግራይ ክልል ተበጅቶላቸው የትግራይ ክልል አንድ አካል ናችሁ ተባሉ። የማይነቃነቅ ድንበር ተከዜ እያለ፣ መናገሻቸው እና ጠቅላይ ግዛታቸው ጎንደር ኾኖ ሳለ በታሪክ ኾኖ የማያውቅ ተከዜን ተሻገሩ፣ ለትግራይ ክልልም ገብሩ ሲባሉ ጀግኖቹ አሻፈረኝ አሉ። ማንነታችን አይነጠቅም፣ ታሪክ አይጠፋም፣ አባት ያወረሰንን እውነት አንጥልም፣ በትግራይ ክልል ሥርም አንተዳደርም ሲሉ ለዓመታት በፅናት ታገሉ። ከዓመታት ትግል በኋላ የተቀሙትን እውነት በደምና በአጥንት ዋጋ ተቀበሉ።
ስለ ወልቃይት ያደጉበት ይናገራሉ፣ የተወለዱበት ይመሰክራሉ። አባታቸው ቀኝ አዝማች ረታ ተኮላ ይባላሉ። የስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት፣ የወልቃይት ባላባት ናቸው። አባታቸው በኢጣሊያ ወረራ ዘመን ከስሜን በጌምድር ጀግኖች እና ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ጋር በመኾን ጠላትን በባሩድ እሳት ቆልተዋል። በጭብጥ ቆሎ እየዋሉ ጠላታቸውን መትተው ሀገራቸውን አስከብረዋል። የእሳቸው ስም ደግሞ ተሰማ ረታ ይባላል። በስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ወልቃይት ብላምባ ሉቃስ በተባለች ሥፍራ ነው የተወለዱት። ዘመኑም በ1940 ዓ.ም ነበር።
በወልቃይት አደጉ። ሀገራቸውን በጀግንነት የጠበቋት ቀኝ አዝማች ረታ ተኮላ ሀገር ሰላም ስትኾን በረሃ ወርደው ማረስ ጀመሩ። ልጃቸው ተሰማ ከአባታቸው ጋር ወደ በረሃ ወረዱ። በሰፊ ማሳ እያረሱ፣ በሰፊ አውድማ እያፈሱ ይኖሩ ጀመር። የዘመኑ ፊታውራሪዎች፣ ደጅ አዝማቾች እና ራሶች ጠረፍ እያስከበሩ፣ በሰፊው መሬታቸው እያረሱ ለጠቅላይ ግዛቱ እየገበሩ ይኖሩ ነበር። በእሳቸው የወጣትነት ዘመን ያን አካባቢ ጀግናው ቢትወደድ አዳነ ያስተዳደሩት ነበር።
በዚያ ዘመን ተከዜን በወሰንነት የሚጋሩት የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት፣ የትግራይ ጠቅላይ ግዛት እና የስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ጎበዛዝት ከታላቁ ወንዝ ላይ እየተገናኙ በጋራ እየዋኙ በፍቅር ጊዜን ያሳልፉ ነበር። ጋሽ ተሰማ ረታም እንዲህ እያሉ ነው ያደጉት። በወጣትነት ጊዜያቸው በዘመነ ኃይለ ሥላሴ ከተከዜ መለስ ያለው ስሜን በጌምድር ይባል ነበር። ንጉሡ አልፈው ደርግ ሲመጣ ደግሞ ጎንደር ክፍለ ሀገር ተባለ ይላሉ ጋሽ ተስማ። እንጂማ ትግራይ የሚባል ክፍለ ሀገር ተከዜን ተሻግሮ አያውቅም። ተከዜ ነኪ የሌለው ደንበር ነው ይላሉ።
በንጉሡ ዘመን ተወልደው ንጉሣዊ ሥርዓቱን አዩ። በዚያም አደጉ። ንጉሡም አለፉ። የደርግን ሥርዓትም አዩ። የደርግ ሥርዓትም አለፈ። በወልቃይት ታይቶ የማይታወቅ ሥርዓት ይዞ የመጣው ሥርዓትም መጣ። ወልቃይት ጠገዴ መላው ኢትዮጵያን በጠረፍ የሚጠብቅ ጀግና ሕዝብ ነው። “ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ማንነቱ አማራ በመኾኑ አንደራደርም፣ ጨርሶ ድርድር የለንም። ተከዜ ነው ድንበራችን” ይላሉ ጋሽ ተሰማ ስለ ወልቃይት ሲናገሩ።
የወልቃይት ጀግኖች የሕወሓትን ቡድን ያለ እረፍት ተዋግተውታል። በፅናት ታግለውታል። ሕወሓት በውሸት ተፈጥሮ በውሸት እንደሚኖር የሚናገሩት ጋሽ ተሰማ በወልቃይት ጠገዴ በመላው አማራ ያልሠራው በደል እንደሌለ ነው የተናገሩት።” ሕዝብ አይኾንም እያለ ክልል ከለሉ፣ እኔን ጠየቁኝ፣ የትግራይ እና የጎንደር ድንበር ተከዜ ነው አልኳቸው። ተቆጥተው ተነሱ። አሰሩኝ። ይሄ አልበቃቸውም አማራ የሚባል የለም ይሉን ነበር። ሂድና አንድን የትግራይ ሰው በኃይለ ሥላሴ ሁመራ ማን ያርስ ነበር ብትለው አይነግርህም። በደርግስ ብትለው አይነግርህም። የት ያውቀዋል። የራሱ ያልኾነን ቦታ። አሁን ተነስተው ነው ወልቃይት የትግራይ ነው ያሉት።” ብለዋል።
የሕወሓት የሽብር ቡድን ወልቃይት ጠገዴ የእኔ ነው ይበል እንጂ ወልቃይትስ ከአማራ ተነጥሎ ታይቶ አይታወቅም። ወልቃይትስ ከተከዜ ማዶ ተካልሎ አያውቅም። እንኳን ሰው ተራራዎች ከስሜን ተራራዎች ጋር የተያያዙ ናቸው። “የልጉዲ ተራራ ከወልቃይት ተራራ ጋር የገጠመ ነው። የወልቃይት ተራራ ከጠለምት ጋር፣ ጠለምት ከስሜን ጋር ይያያዛል። ሰንሰለቱ አንድ ነው” ይላሉ ጋሽ ተሰማ። ተፈጥሮ በራሱ ምስክር ነው። አበው የተወለዱበትን፣ ተወልደው ያደጉበትን ማንነት ሊቀማቸው መሞከሩ ነበር ጀግኖቹን ያስቆጣቸው።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራን ሕዝብ ማንነት ለመቀየር ብዙ ጣሩ አልተሰካላቸውም። ማንነቱን፣ ባሕሉን፣ ጎንደሬነቱን አልጣለላቸውምም ነው ያሉን።” ክረምት ሲመጣ ከትግራይ ለአረም ይመጣሉ። ያን ጊዜ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ ነው በሬ አርዶ ይቀበላቸዋል። ሲያርሙ ይከርማሉ፣ አጭደው ይመለሳሉ። ሲያሳርሙና ሲያሳጭዱ የከረሙት ደግሰው አመሰግነው ተከዜን አሻግረው ይሸኟቸዋል። የእኔ አባትም እንደዚህ ነበር የሚያደርገው። ሠራተኞች ሲመጡ በሬ አርዶ ይቀበላቸዋል። አሁን ግን በሬ አርዶ የተቀበለ የወልቃይት ሰው እጁን ተነከሰ። ” ነው ያሉት።
ጋሽ ተሰማ ታሪኩን ባነሱ ቁጥር ንዴት ይፈታተናቸዋል። የሽብር ቡድኑ ሕወሓት በስልጣን ዘመኑ ታሪክ አዋቂዎችን እየመረጠ ሲገድል፣ ሲያሰቃይ፣ ሲያሳድድ፣ ታሪክ ሲያጠፋና ሲዘርፍ አይተዋልና። የእነ ፊታውራሪ ሰረበ፣ የእነ ፊታውራሪ የሺህወንድም፣ የእነ ቢትወደድ አዳነና የእልፍ ጀግኖች መዳረሻ ወልቃይት መከራ ሲፀናባት ተመልክተዋልና። ወልቃይት የትግራይ ኾኖ አያውቅም፣ አልኾነችምም፣ አትኾንምም የጋሽ ተሰማ ቃል ነው። “እኛ ሀገር የመልቀቅ አመል የለብንም። ለጠላት የመሸሽ አመል የለብንም። እኛ ጠላትን መምታት ነው አመላችን። እኛ ለሀገር መሞት ነው አመላችን። ሀገር እንጠብቃለን። ጀግንነቱ ከእኛ ጋር ነው የትም ንቅንቅ የለም።” ነው የሚሉት።
ጀግና ሀገሩን ጥሎ አይሸሽም። ጀግና ጠላት በረከተ ብሎ አንገቱን አይደፋም። በጀግንነት ተጋድሎ ያስከብራል። ይከበራል እንጂ። ” አንተ የአሁን ዘመን ወጣት ገንዘብ አትውደድ ፣ መጀመሪያ ሀገሬ በል። ሀገሬ ካልክ ጠላት አይነካውም። ወያኔ ሲጋራ ካጨስክለት፣ ጫት ከቃምክለት ይወድሃል። ሀገር ልትጠብቅ ከተነሳህ ግን ይጠላሃል” ነው ያሉት። ጀግኖች በተፈጠሩበት፣ በሞቱበት የተፈጠረ አይፈራም። ጀግኖችን ተከትለህ ካልሄድክ ዘመን ይመሽብሃል፣ ጠላትም ይጫወትብሃል ነው የሚሉት።
የመታለያው ዘመን አብቅቷል። የመዋሸቱ ዘመንም አብቅቷል። ” ሕወሓት ከሃዲ ነው። ከእኛ ጋራ ሠላሳ አምስት ጊዜ ታርቋል። ይታረቃል ያፈርሳል። አሁንም ያን ለማድረግ እያታለለ ነው። አትመኑት። ማታለል፣ መክዳት ሥራው ነው። ምህረት ብሎ አግብቶ አንገት የሚቆርጥ ነው። አሁን ወያኔን የሚያምን ትውልድ ካለ ሞኝ ነው። ሀገራችሁን ጠብቁ። የዋህ እባብ የለም። ጊዜ ጠብቆ በመርዙ ይወጋል። ወያኔም እንደዛ ነው። አደራ እንዳትታለሉ” ብለዋል።
ተከዜ ድንበራችን ማንነታችን አማራ ነው በማለታችን ታሪካችንን እየለቀሙ ለማጥፋት ሠርተዋል። በየአብያተ ክርስቲያናት ያሉ መፃሕፍትን ወስደዋል። የቀሩት ታሪክ አዋቂ ጀግኖችን ለመግደል ጉድጓድ ቆፍረው ለመቅበር ተዘጋጅተው ነበርም ነው ያሉን።
ጋሽ ተሰማ ስለ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ ለጎንደር ጠቅላይ ግዛት ግብር ይገብርበት፣ ደብዳቤ ይፃፃፍበት የነበረውን ማስረጃ ይዘው እውነቷን እየተናገሩ አሉ። አሁን በሑመራ ከተማ የሚኖሩባት ቤታቸው ሳትቀር የታሪክ ምስክር ናት። ቤታቸውን አባታቸው ቀኝ አዝማች ረታ በዘመነ ኃይለ ሥላሴ በ1962 ዓ.ም ያሠሯት ናት። ቤታቸውም አንድ የታሪክ ምሥክር ኾና ዛሬም እርሳቸውን እና ልጆቻቸውን አስጠልላ አለች። እሳቸው እና እንደ እሳቸው ያሉ ታሪክ አዋቂዎች ዛሬም ድረስ ስለ ወልቃይት እውነት እየተናገሩ፣ እየመሰከሩ ተቀምጠዋል።
“ወልቃይት ጠገዴ የጎበዙን ሀገር
ያሳደገኝ እኔ የማውቀው ልናገር” እንደተባለ የጎበዙን ሀገር የተወለዱበት፣ ያደጉበት፣ የሚያውቁት ይናገሩለታል። እውነቱን ይመሰክሩለታል። የሚያውቅ ሲናገር ያምራል። የሚያውቅ ሲናገር እውነት ይገለጣል። የሚያውቅ ሲናገር በውሸት የተከበበው እውነት ይወጣል። አበው ስለ ወልቃይት በእውነት እና በኩራት እየተናገሩ ይናገራሉ። ልጆቻቸውም የአባቶቻቸውን እውነት እና ማንነት ይከተላሉ።
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!

Previous articleአሸባሪው ሕወሃት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ የሚያሳስትበትን የመረጃ ጦርነት በተሟላ የመረጃ ትንተና ማክሸፍ ይገባል።
Next articleየመስቀል ደመራ በዓልና የግሸን ደብረ ከርቤ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡