
አጋር ድርጅቶችን ለማቀፍ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ እራስን በራስ ከማስተዳደር ህገ መንግስታዊ ስርዓት ጋር የማይቃረን፣ አሀዳዊ ስርዓት የመፍጠር ዓላማ የሌለውና ለሀገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ሶዴፓ አስታውቋል፡፡
የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳመላከተው ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ህገ-መንግስቱና የፌዴራል ስርዓቱ በተገቢው መንገድ ሲተገበር እንዳልነበረ፣ ይልቁንም ሶማሌ ክልልን ጨምሮ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሞግዚትነት ሲተዳደሩ እንደነበሩ አስታውቋል፡፡ የሞግዚት አስተዳዳሪዎች ለግል ጥቅማቸው ማስፈፀሚያ የሚመቻቸውን አካል ለይስሙላ ከማስቀመጥ ባሻገር የክልሉን በጀትና መሬት በመቀራመት የክልሉን ሕዝብ ለከፋ ጉዳት እንደዳረጉትም ሶዴፓ በመግለጫው አመላክቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር የዘረፉትን ሀብት አሁንም ድረስ ሀገርን ለማፍረስ እያዋሉት መሆኑ በእጅጉ እንዳዘነ ነው ፓርቲው ያስታወቀው፡፡
በለውጡ ጥቅማቸውን ያጡ አካላት ከዚህ ቀደም በፓርቲው እና በሕዝቦች ላይ ሲያደርሱት በነበረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ በደል ሳይፀፀቱ ዛሬም በእናውቅልሃለን አካሄድ የድሮውን ለመመለስ ተስፋቸውን በተለያየ መንገድ እየገለፁ እንደሚገኙም ሶዴፓ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ እነዚህ አካላት ባለፉት 27 ዓመታት ክልሉን ለችግር ዳርጎ የነበረው አካሄድ ዳግም እንዲመለስ ያላቸውን ምኞት ሶዴፓ መቼም እንደማይፈቅድ ግልፅ ሊሆንላቸው ይገባል ብሏል ፓርቲው በመግለጫው። “ለፓርቲያችንና ለሕዝባችን የሚጠቅመውንም ጠንቅቀን የምናውቅና ቅንነት የጎደለው ምክር የምንሻ አለመሆናችንን ሊገነዘቡት ይገባል” ብሏል ሶዴፓ።
በሌላ በኩል ባለፉት 27 ዓመታት የበላይነት ይዘው የነበሩ የልዩነትና የጥላቻ ትርክቶችን፣ የብሔር ፅንፈኝነትንና አጋር ድርጅቶችን አግላይ አካሄዶችን በሚፈታ መልኩ ኢህአዴግ የጀመራቸውን ለውጦች ሶዴፓ እንደሚደንቅም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡ “አጋር ድርጅቶችንም ለማቀፍ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ እራስን በራስ ከማስተዳደር ህገ መንግስታዊ ስርዓትና ከምንከተለው የፌዴራል ስርዓት ጋር የማይቃረን፣ አሀዳዊ ስርዓት የመፍጠር ዓላማ የሌለውና ለሀገራችን ወቅታዊ ችግሮች ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ሶዴፓ ያምናል” ብሏል መግለጫው።
በሶማሌና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ አከባቢዎች አገራዊውን ለውጥ ለማዳናቀፍ ሌት ተቀን በሚጥሩ አካላት ህቡዕ እንቅስቃሴ የተፈጠረውን ችግር በህገ-መንግስቱ መሠረት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑንም ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ወደ ነበረው በደል፣ ግፍና ትርምስ የሚመልስ ማንኛውም ህልም ሶዴፓ ዘንድ ቦታ የሌለው መሆኑንም አስታውቋል፡፡