“ወታደር መሆን ከራስ በፊት ለሕዝብ ጥቅም እና ለሀገር ክብር መቆም ነው” መቶ አለቃ እውነቱ ማዘንጊያ

302

ወልድያ፡ መስከረም 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብዙዎች ለሀገራቸው ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በእናታቸው ይመስሏታል። እልፎች ለክብሯ ዘብ አድረዋል፤ ለሉዓላዊነቷ በዱር በገደል ተዋድቀዋል። ዘመናትን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ የነጻነት ታሪክ ውስጥ ዘመን አይሽሬ ታሪክ የጻፉ የሀገር ባለውለታ ወታደሮች በርካታ ናቸው።
ዛሬም እንደትናንቱ ምቾታቸውን ንቀው ከቤተሰቦቻቸው ተራርቀው፤ ሀገራቸውን አስቀድመው ወገናቸውን አስደምመው በየቀኑ ጀብድ የሚሠሩ ወታደሮች በየምሽጉ አሉ። ኢትዮጵያ ጠላት በድንበሯ ጀግና በማሕጸኗ ነጥፎባት አታቅም። ሰትደክም የሚያበረቱ፣ ስታዝን የሚያጽናኑ፣ ስትወጋ የሚጠግኑ እና ወደ ኋላ ስትቀር የሚያዘምኑ ወታደሮች ባለቤት ናት፤ ኢትዮጵያ።
ወራሪዎች ዐይናቸውን በሚጥሉባት ኢትዮጽያ፣ ቀኝ ገዥዎች አብዝተው በሚመኟት ኢትዮጵያ፣ ጎረቤቶቿ በስጋት እና በፍርሃት በሚመለከቷት ኢትዮጰያ ዘንድ ወታደር ሆኖ መመረጥ መታደል ነው። ወታደር ስትሆን ሀገር አብዝታ ታምንሃለች ወገን ይመካብሃል። ወታደር ስትሆን ዘብ የቆምክለት ሕዝብ ከፈጣሪ በታች ሀገሩን በአደራ የሚሰጥ ላንተ ነው። ወታደር ስትሆን አባቶች ሀገራቸውን፣ እናቶች ክብራቸውን እና ታዳጊዎች ተስፋቸውን በአንተ ላይ ይጥላሉ። ወታደር ስትሆን አምነህ ትታመናለህ።
“ወታደር መሆን ከራስ በፊት ለሕዝብ ጥቅም እና ለሀገር ክብር መቆም ነው” ያሉን የአንድ ክፍለ ጦር የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ የሆኑት መቶ አለቃ እውነቱ ማዘንጊያ ናቸው፡፡ አሁናዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ወታደር መሆንን ይጠይቃል ይላሉ። የውስጥ ባንዳዎች እና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች እረፍት የሚነሷትን ሀገር ከመጠበቅ የተሻለ ኅላፊነት የለም የሚሉት መቶ አለቃ እውነቱ የድል ወታደር መሆን ደግሞ ክብሩ ልዩ ነው ብለውናል።
መቶ አለቃ እውነቱ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ወታደሮች በነበራቸው ብቃት፣ ጀግንነት፣ የሀገር ፍቅር እና ጽናት ይታወቁ እንደነበር አንስተዋል፡፡ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ወታደሮች ከቀደሙት በተጨማሪ ብቁ ሥልጠና እና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቀዋል ሲሉም ገልጸዋል። የድል ሠራዊት ነው ሲባልም ውስብስቡን የሀገር ውስጥ ባንዳዎች ሴራ እና የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ተላላኪዎች ሽፍጥ በአጭር ጊዜ ራሱን አደራጅቶ ማሸነፍ በመቻሉ ነው ይላሉ።
መቶ አለቃ እንደሚሉት ባንዳዎች ያፈረሱትን እና የበተኑትን ወታደር በአጭር ጊዜ አደራጅቶ እና አቀናጅቶ ከውስጥም ከውጭም የመጣን ጠላት የተቋቋመ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙም አልተስተዋለም። በዚህ ወቅት የዚህ ሠራዊት አባል ከመሆን የተሻለ የሀገር ፍቅር መገለጫ የለምና ወጣቶች መከላከያን መቀላቀል ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
በቀደመው ሥርዓት ከወታደራዊ ሳይንስ እና እሳቤ በተዛነፈ መንገድ በመመራቱ በተዛባ መንገድ እንዲታይ የተደረገውን የውትድርና ሙያ ኢትዮጵያ ቁመና እንዲኖረው ለማድረግ የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼

Previous article“የወልቃይት ትንታጎች፣ የበረሃ መብረቆች”
Next article“ተቆርቋሪ ትግራዊያን እልህ አሰጨራሽ ትግል አድረገዉ ሕዝባቸዉን ከአሸባሪው ሕወሃት ነጻ ማዉጣት ይገባቸዋል” የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ሸዋፈራዉ ሽታሁን