
ሁመራ: መስከረም 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የገፏቸው ወድቀዋል፣ የገጠሟቸው ተሸንፈዋል፣ የተኮሱባቸው ተቀድመዋል። በረሃው አይበግራቸውም፣ ውኃ ጥሙ አያስቆማቸውም፣ ረሃብ አያሰናክላቸውም። ጥሙን ረስተው፣ ረሃቡን ትተው ለተከበረች ሀገራቸው፣ ለተወደደች ሠንደቃቸው፣ ለድርድር ለማትቀርብ ማንነታቸው ሲሉ መዋያቸውን በዱር፣ ማደሪያቸውን በምሽግ አድርገዋል።
ከአያት ቅድመ አያት ሲወርድ በመጣ ጀግንነታቸው፣ ተመልክታ በማትሥት አፈሙዛቸው፣ ምድር ላይ በማትወድቅ ጥይታቸው ሀገር አስከብረዋል፣ ሠንደቅ ከፍ አድርገዋል። በሀገር ላይ በክፋት የተነሱትን መትተዋቸዋል፣ ክብር እንድፈር ያሉትን በአሻገር አስቀርተዋቸዋል። የጦር መምጫውን፣ የድል መንሻውን፣ የአተኳኮስ ዘዴውን ያውቁበታል። ተኩሶ መምታት ፣ ድል አድርጎ መምጣት መገለጫቸው ነው።
በዚያ ምድር እልፍ ጠላቶች እየመጡ ተመትተዋል፣ ከወንዝ ማዶ ከወሰን ባሻገር እንዳልነበር ኾነው ቀርተዋል፣ ለኢትዮጵያ ክብር ሠግደው እጅ ነስተዋል፣ ለጥፋታቸው ጉልበት ስመው ይቅርታ ጠይቀዋል። ምቱ ሲጠነክርባቸው፣ ውሽንፍሩ አላላውስ ሲላቸው፣ መውጫ መግቢያው ሲጠፋባቸው እጅ እየነሱ ምኅረት ለምነዋል። ልባቸውን ያመኑ ጀግኖች፣ ጀግንነትን ከዘመን ዘመን ያስቀጠሉ ደፋሮችም ጠላትን እንዳመጣጡ ሲመልሱት ኖረዋል። ስለ እነርሱ ጀግንነት የተመላለሱባቸው ሸለቆዎች፣ ውለው ያደሩባቸው ምሽጎች፣ ጠላትን የቀጡባቸው ሸንተረሮች ይመሰክራሉ።
ለዓመታት ሥርዓት የገፋቸው ጀግኖች፣ በመከራ ዘመን በፅናት የታገሉና የተዋደቁ ነበልባሎች፣ በእሳት የተፈተኑ ልበ ሙሉዎች፣ ዛሬም በሀገራቸው፣ በሠንደቃቸው፣፣ በማንነታቸው፣ በክብራቸውና በሕልውናቸው የመጣውን ጠላት ነፍጥ አንስተው እየመከቱት፣ አንድ እርምጃ ወደፊት እንዳይጓዝ አድርገው እየመቱት ነው። የወልቃይት ትንታጎች፣ የበረሃ መብረቆች እምብኝ ለማንነት፣ እምብኝ ለክብር፣ እምብኝ ለፍቅር ብለው በረሃ ከወረዱ ሰነባብተዋል። ያለ ድል አንመለስም፣ ጠላታችንን አደብ ሳናስይዝ ፊታችን አንመልስም ብለዋል።
ለዓመታት በማንነታቸው የመጣባቸውን፣ ለዓመታት የበደል ጥግ የፈፀመባቸውን፣ ለዓመታት የገደላቸውን፣ ለዓመታት ያሳደዳቸውን፣ ለዓመታት ከቤት ንብረት ውጭ ያደረጋቸውን ጠላት እየተፋለሙት ነው። ማንነታቸውን ተቀብለው፣ ጠላታቸውን አሸቀንጥረው ጥለው ለዳግም ወረራ ሲመኝ እረፍ ብለው እየተከላከሉት፣ ተቆጥተው እየመቱት ነው።
እነዚህ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ጀግኖች ለዓመታት በደል ካደረሰብን ጠላት ጋር ሜዳው ላይ ተገናኝተናል። ጀግንነት ተያይተናል እያሉት ነው። ያውቀናል እናውቀዋለን፣ ያለፈው ዘመን አይደገምም፣ ጠላትም በጀግኖች ምድር አንድ እርምጃ አይራመድም ብለዋል።
በወልቃት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን የቃፍታ ሑመራ ሰላም አስከባሪና ሚሊሾች የሕወሃት የሽብር ቡድን ወልቃይትን አያስባትም፣ የጀግኖችን ምድር ፈፅሞ አይረግጣትም ብለዋል። አካባቢያቸውን በተጠንቀቅ እየጠበቁ ያገኘናቸው ሰላም አስከባሪዎች እና ሚሊሻዎች ጠላትን እንደ አመጣጡ እንመልሰዋለን። ክንዳችንን እናሳርፍበታለን ነው ያሉት።
የብርጌድ ምክትል አዛዥ አምሳ አለቃ ሊላይ ገረፍኤል ሰላም አስከባሪዎች እና ሚሊሻዎች የሽብር ቡድኑን ወረራ ለመመከት ቆርጠው መነሳታቸውን ተናግረዋል። ሚሊሻው የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ በቁጣ ተነስቷል ነው ያሉት። የሕዝቡ ደጀንነት የተዋጊው ቁርጠኝነት እና ቁጣ የሚገርም ነውም ብለዋል።
በወልቃይት ምድር ለማንነታቸው የታገሉ ቀብር እንኳን ሳይፈቀድላቸው ይኖሩ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል አዛዡ በማንነቱ ተሰቃይቶ የኖረ ሕዝብ እንደኾነም አስታውቀዋል። የሽብር ቡድኑን ፈፅሞ ለማጥፋት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁጣና በእልህ መነሳታቸውንም ተናግረዋል። የጠላትን ሥራ አስቀድመን ስለምናውቅ አስቀድመን ተዘጋጅተናል፣ ጠላት የትም አያልፍም ነው ያሉት።
የሻለቃ ምክትል አዛዥ መቶ አለቃ ታደለ ግዛው በመከላከያ ሠራዊት እንደነበሩ ነግረውናል። እሳቸው በሠራዊቱ ውስጥ በነበሩበት ዘመን የአማራ ተወላጆች በሕወሃት መሪዎች ግፍ ሲደርሳባቸው እንደነበር ነው የተናገሩት። ያሰቃዩን ሰዎች ጥሩ ሜዳ ላይ ተገናኝተናል፤ ወንድነታችንን አሁን እያዩት ነው፣ ወደፊትም ያዩታል ብለዋል። በሁሉም አቅጣጫ እሾህ ኾነን እየጠበቅን ነው፣ እንኳን ለአሸባሪው ሕወሓት ለሌላ ጠላት ዝግጁ ነን ነው ያሉት። ሕዝባችን አብሮን ነው። የሕወሓት ቡድን በየደረሰበት እየተመታ ነው። ጠላታችንን ሳንመክት እረፍት የለንም ወደፊትም እንመክተዋለን ብለዋል።
የጀግኖቹ አባል ቸሬ አዳነ ሚሊሻው እና ሰላም አስከባሪው በቁርጠኝነት መነሳቱን ተናግረዋል። ጠላትን እንደምንመክተው ጥርጥር የለንም ብለዋል። ያሳለፍነው ጭቆና ጠላትን በቁርጠኝነት እንድንዋጋ አድርጎናል ነው ያሉት።
ሌላኛው አባል ማሙዬ አየናይ የሽብር ቡድኑ በስልጣን ዘመኑ ሲያታልል እና ሕዝብን ሲያጭበረብር እንደነበር ነው የተናገሩት። አሁን ጠላት በቆፈረው ጉድጓድ እየተቀበረ ነው፣ በጫረው እሳት እየነደደ ነው፣ ሁሉም በወኔና በእልህ ኾ ብሎ ዘምቷል፤ የወልቃይት ጠገዴን ምድር ድጋሜ አይረግጣትም ብለዋል።
የቃፍታ ሑመራ ወረዳ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊና የብርጌድ አዛዥ አምሳ አለቃ ስማቸው ገብሩ በከፍተኛ ዝግጅት ጠላትን እየተከላከልን ነው ብለዋል። ጠላት ለእኛ አዲሳችን አይደለም፣ የሚመጣውን እያስቀረን አካባቢውን እያስጠበቅን ነውም ብለዋል። ባለሀብቶች እና መላው ማኅበረሰብ ከተዋጊው ኀይል ጋር በወኔና በአስተማማኝ ደጀንነት እንዳለም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል። ሚሊሻው አኩሪ ጀግንነት እየፈፀመ መኾኑንም አስታውቀዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ማንነቱን ተነፍጎ የኖረ ነው ያሉት አዛዡ አባቶች በጀግንነት ለማንነት ሲዋጉ ኖረዋል፣ እኛም የተሰውትን ጀግኖች እያሰብን በጀግንነት እየታገልን ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ የጠላትን ግፍ በሚገባ ሰለሚያውቅ ጠላት መጣ ሲባል ኾ ብሎ እንደሚነሳም ተናግረዋል። የወልቃይት ሕዝብ እሴቱን፣ ባሕሉን እና ማንነቱን ተነጥቆ እንደኖረም ገልጸዋል። ጠላቱን በጥንቃቄ የሚያውቀው ማኅበረሰብ አሳምሮ እንደሚቀጣውም ተናግረዋል።
የቃፍታ ሑመራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አብዱልዋስ አቡበከር የሽብር ቡድኑ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን ሲያደርግ እንደነበር አስታውቀዋል። ጠላት አካባቢውን በልዩ ትኩረት እንደሚመለከተውና ለጥቃት እንደሚመርጠው ገልጸዋል። የፀጥታ ኀይሉ በተቀናጀ አግባብ ባንዳን፣ ሠርጎ ገብን በመጠበቅና ምሽግ ኾኖ በመከላከል ከፍተኛ ሥራ እየሠራ መኾኑን ነው ያነሱት።
የአካባቢው ማኅበረሰብ አሁን ሳይኾን ከዓመታት በፊት ፀረ ሕወሃት ትግል ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውሰዋል። የሽብር ቡድኑ የአካባቢውን ወግና ባሕል ለማጥፋት ሲሠራ እንደቆየም አስታውቀዋል። ማኅበረሰቡ የጠላትን ሥራ ስለሚያውቅ ለትግል ወደ ኋላ እንደማይል ነው የተናገሩት። ጠላትን እየተከላከልን ልማቱን እያፋጠንን ነውም ብለዋል። የሥራ ኀላፊዎችም ከሕዝቡ ጋር በመኾን በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት። ሕዝቡ በጠላት የደረሰበትን ግፍና በደል ከማንም በላይ ስለሚያውቀው በራሱ ተነሳሽነት የሚነሳ መኾኑንም ተናግረዋል።
የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል እንዲሰበሰብ የሚያደርግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። የዘማች ቤተሰቦችን ብቻ ሳይኾን የአቅመ ደካሞችን ሰብል እንደሚሰበስቡ ነው የተናገሩት። የአካባቢው ማኅበረሰብ ከጠላት እንቅስቃሴ ለአንዴና ለመጨረሻ እንዲገላገል የጀመረው የጀግንነት ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J