
ባሕር ዳር: መስከረም 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከእስራኤል፣ ከጣልያንና ከሶሪያ ሀገራት የተውጣጡ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ባሕል እና አማርኛ ቋንቋ ለመማርና ለመመራመር የሚያስችላቸውን ሥልጠና በባሕር ዳር እየወሰዱ ይገኛሉ።
ሥልጠናውን ያዘጋጁት በሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ሥነልሳንና የኢትዮጵያ ጥናት የአማርኛ ቋንቋ መምህርና የአፍሪካ/ኢትዮጵያ ፎክሎር መምህርና ተመራማሪ ጌቴ ገላዬ (ዶ.ር) የሀገራትንና የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከር በቋንቋ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የውጭ ሀገራት ገንዘብ መድበው፣ መዝገበ ቃላት አዘጋጅተው ቋንቋቸውን ለልጆቻቸው ያስተምራሉ ያሉት ዶክተር ጌቴ በተለይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋን ለማስተማርና ለማሳደግ የልህቀት ማዕከል መገንባት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ተመራማሪው እንዳሉት የውጭ ሀገራት በዕቅዳቸው አካትተው የአማርኛ ቋንቋን ለልጆቻቸው ሲያስተምሩ በኢትዮጵያ ግን ለአማርኛ ቋንቋ ተገቢውን ትኩረት አልተሰጠውም።
ከውጭ ሀገራት የመጡ ሠልጣኞች ከመጡበት ሀገር ሲመለሱ የአማርኛ ቋንቋና የኢትዮጵያ ባሕልን እንደሚያስተዋውቁም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያን ለቋንቋቸውና ለባሕላቸው ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተመራማሪው ገልጸዋል። ሠልጣኞቹ ከሥልጠናው በኋላ የቋንቋም ኾነ የታሪክ መሠረት የኾኑ ገዳማትን እንዲጎበኙም ጋብዘዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ.ር) “በተገቢው መንገድ እንድንግባባ አንዳችን የአንዳችንን ቋንቋ መማር ይጠበቅብናል” ብለዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በግዕዝ ቋንቋ ላይ የተመሰረቱ ጥናቶችን እያካሄዱ መሆኑን ዶክተር ፍሬው አመላክተዋል። በጥናቱ ላይ መሳተፍ የሚፈልግ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ መካተት እንደሚችል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
ለጥናቱ ስኬታማነት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ቁርጠኛ ነውም ብለዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሂዩማኒቲ ፋኩልቲ ዲን ዋልተንጉሥ መኮንን (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ የስብጥር ማንነት የልዩ ልዩ አየር ንብረት መገኛ፣ የረዥም ዘመን ሀገረ መንግሥትን መስርታ ሥርዓትን ያቆመች የራሷ የኾነ ፊደል የቀረጸችና የራሷ ጽሑፍ፣ ባሕል ያላት፣ ነጻነቷን እስከብራ የኖረች ታላቅ ሀገር ነች ብለዋል።
ዶክተር ዋልተንጉሥ እንዳሉት አማርኛ በአፍሮ ኤዥያ ዐብይ የቋንቋ ቤተሰብ ሥር በኢትዮሴማዊ ንዑስ የቋንቋ ቤተሰብ ከሚመደቡ ቋንቋዎች መካከል ተጠቃሽ ነው።
የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሒር ሙሐመድ በበኩላቸው ሠልጣኞች የአማራንም ኾነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ታላቅነት ለሌሎች እንዲያስተዋውቁ ጠይቀዋል።
ሠልጣኞች በሚኖራቸው ቆይታም ቢሯቸው አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግላቸውም ገልጸዋል።
ከሠልጣኞቹ መካከል ጣሊያናዊቷ ኢላሪያ ዞርዛን በቆይታዋ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ባሕል እንደምታጠና ተናግራለች። ከቆይታዋ በኋላም የሁለቱን ሀገራት ቋንቋና ባሕል በተለይ ለምዕራቡ ዓለም ለማስተዋወቅ ጥረት እንደምታደርግም ገልጻለች።
ጀርመናዊው ቶቢያስ ፔልሽን በበኩሉ ሥልጠናው ጀርመንንና ኢትዮጵያን የበለጠ ለማስተሳሰር እንደሚጠቅምም ተናግሯል። በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ዓለም የማይገኝ ባሕል፣ ወግና ትውፊት እንዳለም ሠልጣኙ ባደረገው ቅኝት መገንዘቡን መስክሯል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J