የኢህአዴግ እህት እና አጋር ድርጅቶች ውህደት ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ምሁራን ተናገሩ፡፡

225

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) የወሰን እና የማንነት እንዲሁም በፍትሃዊነት የመልማት ጥያቄዎች ያሏቸው ክልሎች ጉዳይ በምን መልኩ ሊፈታ እንደሚችል ኢህአዴግ ግልጽ አቋም ሊይዝ እንደሚገባ ምሁራን ተናግረዋል፡፡

የአራት ብሔራዊ እህት ደርጅቶች ማለትም የአዴፓ፣ የህወሃት፣ የኦዴፓ እና የደኢህዴን ግንባር በመሆን ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ኢህአዴግ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ የመሆን ሀሰብ ከጠነሰሰ ዓመታት እንደተቆጠሩ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሲመክር እንደቆየም ነው ያስታወቀው፡፡ ይህንን በተመለከተ ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሙያ እየሰሩ ያሉት ሲሳይ ምስጋናው (ዶክተር) እና ጀምበሩ አረጋ (ረዳት ፕሮፌሰር) የኢህአዴግ ውህደት እውን ሆኖ ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ የሚመሠረት ከሆነ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝምን ለመፍጠር እንደሚያስችል ነው የተናገሩት፡፡ ይህም እኩልነት የነገሰባት፣ ፍትሕ የበለጸገባት እንዲሁም የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መብት የተከበረባትን ሀገር ለመገንባት ተስፋ እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡

ለዘመናት ከፓርቲው ጋር አብሮ የመጣውን የተደራረበ ችግር ለመፍታት መልካም አጋጣሚ መሆኑን በመግለጽም ክልሎች ለዘመናት ተነፍጓቸው የነበረውን እኩልነትና ፍትሃዊነት እንደሚያጎናጽፋቸው ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡ እንደ ምሁራኑ አስተያዬት ውህደቱ ዕውን ከሆነ የድርጅቱን ጥንካሬ ከማሳደግም ባለፈ በሕዝብ ላይ የተፈጠረውን ጥርጣሬ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ይሁን እንጂ ውህደቱን የሚገዳደሩ ምልክቶች እየታዩ መሆኑንም ምሁራኑ አንስተዋል፡፡

ፓርቲው ስለጉዳዩ ባለፉት ዓመታት እና በ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ እየገለጸ ቢሆንም ህወሃት “ጠንካራ ፓርቲ የመመስረት ሂደቱን አሃዳዊ ስርዓት ተመልሶ ሊመጣ ነው” በማለት ለመዋሃድ ፍላጎት እንደሌለው መግለጹ የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ የመነጣጠል አደጋ መሆኑን በስጋት አንስተዋል፡፡ ውህደት እና አሃዳዊነት የማይገናኙ ሀሳቦች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡ ይልቁንም የህወሃት አቅጣጫ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለለውጡ የከፈለውን መስዋዕትነት አሳንሶ ከማየት የመጣ መሆኑን ነው ምሁራኑ የተናገሩት፡፡

ኢህአዴግ የጀመረውን ጥናት በፍጥነት አጠናቅቆ ቶሎ ወደ ተግባር መግባት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በተለይም በውህደቱ የሕዝብን መሠረታዊ ፍላጎት ባማከለ መልኩ ውይይት ማድረግ እና ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚገባ፣ በግንባሩ ድርጅቶች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትም በውይይት ለመፍታት ኢህአዴግ ቁርጠኛ ሆኖ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ውይይቱ ውጤታማ እንዳይሆን ግትር ሃሳብ ይዘው የሚቀርቡ አካላት ካሉ ደግሞ አስተማሪ ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰድን እንደ አማራጭ መጠቀም ተገቢ መሆኑን ነው ምሁራኑ ያመለከቱት፡፡

የወሰን እና የማንነት እንዲሁም በፍትሃዊነት የመልማት ጥያቄዎች ያሏቸው ክልሎች ጉዳይ በቀጣይ በምን መልኩ ሊፈታ እንደሚችል ግልጽ አቋም ሊይዙበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
እንደ ምሁራኑ ማብራሪያ ትክክለኛ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ በፍረጃ ላይ የተመሠረተውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም መቀየር፣ የፓርቲውን አደረጃጀት በአዲስ ማዋቀር፣ የፖሊሲ እና ስትራቴጂ እንዲሁም የትግበራ ለውጥ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ ይህ ካልሆነ ሕዝቡም ለውጡን በጥርጣሬ መመልከቱን ይቀጥላል፤ የፓርቲ ውህደቱም ውጤታማ ላይሆን ይችላል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous article“አማራ ክልልን እንደሚወራው ሳይሆን በተቃራኒው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡” የተማሪ ወላጆች
Next articleባለፉት 27 ዓመታት ክልሉን ለችግር ዳርጎ የነበረው የሞግዚት አስተዳዳሪዎች አካሄድ ዳግም እንዲመለስ ያላቸውን ምኞት መቼም እንደማይፈቅድ ሶዴፓ አስታወቀ፡፡