“ከወልቃይት ሠማይ ሥር፣ ከተከዜ ወንዝ ዳር”

312

ሁመራ: መስከረም 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አንዳንድ ወንዞች አሉ እውነት የሚናገሩ፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ታሪክ የሚመሰክሩ፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ታሪክ የሚዘክሩ፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ከትውልድ ትውልድ የሚዘከሩ፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ታሪክ ያገነናቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ምስጢር የመላባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ መንፈስ ቅዱስ የጎበኛቸው፣ እንዳንድ ወንዞች አሉ ቃል ኪዳን ያረፈባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ጥበብ የሚፈስስባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ስልጣኔ የሚጓዝባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ትውልድ ከትውልድ ጋር የሚተሳሰርባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ሕዝብ ሁሉ የሚከባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ብርሃን የሚገለጥባቸው፣ እንዳንድ ወንዞች አሉ የጥፋት ደብዳቤ የሚፋቅባቸው፣ እንዳንድ ወንዞች አሉ የመዳን ነገር የሚነገርባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ የዕዳ ውል የሚሰረዝባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ የምስራች የሚነገርባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ምስጢር የሚመሴጠርባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ታዕምር የሚደረግባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ትውልድ ሁሉ የሚናፍቃቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ትንቢት የሚነገርባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ትንቢት የሚፈፀምባቸው፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ የትህትና ትምህርት የሚሰጥባቸው። አንዳንድ ወንዞች አሉ ስማቸው በዓለሙ ሁሉ የሚነሳ፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ዝናቸው በብራና የሚወሳ።
አንዳንድ ወንዞች አሉ የተቀደሱትን ለማጠጣት የተመረጡ፣ ወይን፣ ወተት፣ ማርና ውኃ ኾነው መልካሟን ዓለም የሚያጠጡ፣ አንዳንድ ወንዞች አሉ ከወንዝነት የበለጡ፣ ታላቅ ነገር የተሰጡ።
የግሪክ ፈላስፎች ሳይነሱ፣ የሮም ጠቢባን ጥበብን ሳያስሱ፣ ዛሬ ኀያላን የሚባሉ ሀገራት ሰው ሳይደርስባቸው፣ ስልጣኔ ሳይታሰብባቸው፣ ዘመናዊነት ሳይሞከርባቸው አስቀድማ የሰው ልጅ መገኛ የኾነች፣ ልሳነ ሰብን የተሰጠች፣ በቃል ኪዳን የከበረች፣ ለምስክርነት የተቀመጠች፣ በታሪክ ከፍ ከፍ ያለች ሀገር ነበረች። ኢትዮጵያ የተሰኘች። ከስጦታዎች ሁሉ በላቀ፣ ከስሞች ሁሉ በረቀቀ ስያሜ የተሰየመች። በቀስተ ደመና፣ በተስፋዋ ምልክት የተከበበች፣ አምራ የተዋበች። የግሪክ ፈላስፎች ከተነሱ፣ የሮም ጠቢባን ጥበብን ካሰሱም በኃላ፣ ተከትለዋት ለመጡት ታሪክ እየነገረች፣ ለስልጣኔ እንግዳ ለኾኑት ስልጣኔ እያስተማረች፣ በጥበብ ላልተራቀቁት በጥበብ እያራቀቀች ዛሬም አለች። የቀደመችው ሀገር ነገም በጥበብና በሞገስ ትኖራለች።
ከመፍጠር በፊት የነበረውን፣ የት እንደነበር፣ ፍጥረታትን አሳልፎ የት እንደሚኖር የማይመረመረውን፣ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረውን፣ ዘመንን የሚገዛውን፣ ከዚህ እስከዚህ የሚባል ዘመን የሌለውን፣ ዘመኑ የማይቆጠረውን፣ ወሰኑ የማይለካውን፣ ሰማይና ምድርን የሚያሳልፈውን፣ የትም፣ መቼም የሚገኘውን፣ ሁሉን የሚያውቀውን ፈጣሪ ታከብራለች። ስሙን እየጠራች፣ ለምስጋና እጆቿን እየዘረጋች በረከትና ረድኤት ትቀበላለች።
ፈጣሪም ወንዞቿን ባርኮላታል፣ ዋሻዎቿን ቀድሶላታል፣ ተራራዎቿን በመንፈስ ቅዱስ ሞልቶላታል። የለመነችውን ሁሉ ይሰጣታል። የጠየቀችውን ሁሉ ያደርግላታል። በተባረኩት ወንዞቿ፣ በተቀደሰቱት ዋሻዎቿ፣ በመንፈስ ቅዱስ በተመሉት ተራራዎቿ ሁሉ ትውልድ ሁሉ የሚፈልጋቸው፣ ያያቸው ዘንድ የሚመኛቸው፣ ሳያቋርጥ የሚጓዝባቸው፣ ደጅ የሚጠናባቸው መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ሀብቶች ሞልተዋል። እድል ከእርሱ ጋር የኾነች የተራራዎቹን ምስጢሮች፣ የወንዝ ዳሩን ጥበቦች፣ የዋሻዎቹን ረቂቅ ስጦታዎች፣ የሐይቅ ውስጡን መልካም ነገሮች ያያል። አይቶም ይደነቃል።
በኢትዮጵያ ምድር ከሚፈስሱት፣ እየፈሰሱ ምድርን ከሚያረሰርሱት፣ የደረቀውን ከሚያለመልሙት፣ በታሪክ በተደጋጋሚ ከሚነሱት፣ ብዙዎች ስሙን በተደጋጋሚ ከሚያነሱት፣ አፍላጋት መካከል ከወልቃይት ሠማይ ሥር፣ ከታላቁ ተከዜ ወንዝ ዳር ጊዜ አድርሶኛል። ተከዜ ስመ ገናና፣ ተከዜ የበረሃ ውስጥ ተጓዥ፣ ተከዜ የዘመናት እግረኛ። ጀንበር ዘልቃ በጠለቀች ቁጥር ተከዜ ያለማቋረጥ ይፈስሳል። ክረምት ግም ሲል፣ ተራራዎች በጉም ሲሸፈኑ፣ ፈጣሪ ለምድር ዝናብን ሲፈቅድ የጠራው ተከዜ ይደፈርሳል፣ ደፍርሶና አጎልብቶ ከዳር ዳር እያማታ ይገሰግሳል።
በታላቁ ወንዝ ነግደው የሚያተርፉ ነጋዴዎች፣ አርሰው የሚያጎርሱ ገበሬዎች፣ ተዋግተው ሀገር የሚጠብቁ ጀግኖች ሲመላለሱበት ኖረዋል። ሞልቶ በተቆጣ ጊዜ አላሻግርም ሲላቸው፣ ኩልል ብሎ በጠራ ዘመን ሲፈቅድላቸው ነው የኖረው። ነጋዴዎች ከእነ ግመሎቻቸው፣ ገበሬዎች ከእነ በሬዎቻቸው፣ ጀግኖች ከእነ ፈረስና በቅሎዎቻቸው ዝቅ ብለው ሲጠጡት ኖረዋል። የጠማቸው ጠጥተውበታል፣ የሞቃቸው ቀዝቅዘውበታል፣ የተከዙት ተዝናንተውበታል።
ተከዜ ሲጠማ የሚጠጡት፣ ሲሞቅ የሚቀዘቅዙበት፣ ሲከፋ የሚዝናኑበት ብቻ አይደለም። በዳሩ ኾነው ትናንትን የሚያዩበት፣ የዘመናትን እርቀት፣ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመረምሩበት፣ ታሪክ የሚጠይቁበት፣ ጠይቀው የሚረዱበት፣ ጥበብ የሚፈልጉበት፣ እውነት የሚያዩበት ነው እንጂ። ተከዜ ተነግሮ የማያልቅ ታሪክ በጉዞው ውስጥ ይናገራል። የማይታበል እውነት ይመሰክራል። ትናንትን ለዛሬ፣ ዛሬን ለነገ ያቀብላል። በተከዜ ዳር ሲቆሙ ለንግድ የተሻገሩበት ነጋዴዎች፣ በሬዎቻቸውን ያጠጡበት ገበሬዎች፣ ሀገር ለማስከበር ያለፉበት ጀግኖች ውል ይላሉ።
ታላቁ ወንዝ እየተገማሸረ ይጓዛል። ያገኘውን እየያዘ ወደ መዳረሻው ያመራል። ከዳሩ ቆሜ ከተፈጠረበት አሁን እስካለበት ዘመን ያለውን የዘመናት ጉዞውን አንሰላሰልኩ። ለአንድ ቀን ሳያርፉ ሁል ጊዜም መጓዝ። ለዘመናት መንገሥ፣ ያለ ድካም መገስገስ። ተከዜ ከዳጋ እስከ በረሃ ድረስ ሠፍረው ያሉ ኢትዮጵያውያን በዜማ እያጀቡት፣ በትዝብት እየተመለከቱት ይሸኙታል። እርሱም ያገኘውን እየተሸከመ ሀገሩን ተሰናብቶ ልምላሜ ወደ ሌላቸው ሀገራት ይጓዛል። ትናንት መጓዝ፣ ዛሬም መጓዝ፣ ነገም መጓዝ።
“እውነት እና ታሪክ በጠየቁት ጊዜ
የዘመኑን ሁሉ ይሰጣል ተከዜ” ተከዜ ሲጠይቁት የማይሰጠው እውነት፣ የማይገልጠው ታሪክ የለውም። የዘመናቱን ታሪክ ይሠጣል። የዘመናቱን እውነት ይገልጣል። የተለያዩ ሀገራት ሕዝቦች ማዶና ማዶ ኾነው ጠጥተውታል። ጠጥተው ረክተውበታል። ደስታን አግኝተውበታል። ተከዜ ሰዎች የሚገናኙበት፣ የጋራ ደስታ የሚያዩበት፣ ፍቅርና አንድነታቸውን የሚያሳዩበት ነው።
ከወልቃይት ሠማይ ሥር፣ ከታላቁ ወንዝ ተከዜ ዳር ቆሞ በኩራት የሚገማሸረውን እየተገማሸረ የሚጓዘውን ወንዝ ታዘብኩት። እፁብ የሚያሰኝ ግርማ ተላብሷል። ልብን የሚያርድ ኀይል ተሰጥቶታል። በዚያ ወንዝ ስንት ነገር ታይቶበታል። በረሃ ሳይበግራቸው፣ ወበቅ የበዛበት ምድር ሳያማርራቸው ሀገራቸውን በጀግንነት የሚጠብቁ ጀግኖች ከተከዜ ወንዝ እየጠጡ ይኖራሉ። ልጆች ወደ ወንዙ ወርደው በውኃ እየተራጩ ወደር የለሽ ደስታ ያያሉ። በፍቅር የተሳሰሩ ጥንዶች በተከዜ ዳር ተቀምጠው ፍቅራቸውን ያጣጥማሉ፣ እንደ ወንዙ የረዘመ ዘመን ይሰጣቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን ይማፀናሉ። በወንዙ ዳር እየተመላለሱ የፍቅርን ጥግ ያያሉ።
ተከዜ ወንዝ ብቻ አይደለም ውኃ ብቻ የሚፈስስበት፣ ተከዜ ፍቅር ነው ሰዎች የፍቅርን ጥግ የሚያዩበት፣ ተከዜ የሐዘን መርሻ ነው። ያዘኑት ሐዘናቸውን የሚረሱበት፣ ተከዜ እውነት ነው የፈለጉትን የሚያዩበት፣ ተከዜ ታሪክ ነው የኋላውን የሚያስታውሱበት፣ ተከዜ ተስፋ ነው ነገን ለማየት የሚጓጉበት። ሞልቶ የሚገማሸረው ወንዝ አስቀናኝ። ዓይኔን እያንከራተትኩ ተመለከትኩት የማይጠገብ ውበት ተችሮታል። የማይሰለች መወደድ ተሰጥቶታል። በውበቱ ተማረኩ፣ ከግርማው ተሸነፍኩ።
ከአማረው ውበቱ ላይ በዙሪያው የቆሙ አረንጓዴ ካባ የተጎናፀፉ ዛፎች ተጨምረው ሌላ ግርማ ሰጥተውታል። ሌላ ውበት አላብሰውታል። እፁብ የሚያሰኝ ውበቱን ሲመለከቱት ከአጠገቡ አትራቅ፣ ከወንዙ ዳርቻ አትልቀቅ ያሰኛል። ውበቱ ቢገርመኝ፣ ግርማው ቢደንቀኝ ከዳሩ ቁሜ ኢትዮጵያን አደነኳት። በአንደበቴም አመሰገንኳት። ኢትዮጵያ ኾይ በሁሉ ታድለሻል። ኢትዮጵያ ኾይ ውበት ሁሉ ተሰጥቶሻል። ኢትዮጵያ ኾይ ረቂቅ ነሽና ምስጋና ይገባሻል፣ ኢትዮጵያ ኾይ ከከበሩት የከበርሽ ነሽና ክብር ይገባሻል። ኢትዮጵያ ኾይ በምድርሽ የተፈጠሩት የታደሉ ናቸው። ምድርሽን በፍቅር የረገጡትም የተመረጡ ናቸው። ስለ አንቺ የቆሙትም የተከበሩ ናቸው። ስለ አንቺ የሚሞቱትም ብሩካን ናቸው።
በወልቃይት ሠማይ ሥር፣ በተከዜ ወንዝ ዳር አየሁ፣ አደነቅኩ ብዙ ምስጢር። በማይጠገበው ምድር የረቀቁ ነገሮችን ተመለከትኩ።
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!

Previous articleበአንዳንድ ምዕራባውያን ዒላማ ውስጥ የገቡ ቀደምት ልዕለ ኃያላን ሀገራት!
Next articleአግራ በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ችግርን ለመዋጋት የ550 ሚሊዮን ዶላር ፈንድ ይፋ አደረገ።