
ለመላው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊትና ሲቪል ሠራተኞች በሙሉ እንኳን ለ2015 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሠላም አደረሣችሁ፡፡ አደረሰን!!
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ህዝባዊ ባህሪውንና ጀግንነቱን ጠብቆ የጠላቶቻችንን መሰሪና አፍራሽ ተልዕኮን ተቋቁሞ በመስዋዕትነት አንድነቷን ጠብቃ ህዝቦች በፍቅርና በጋራ የሚኖርባትን ሀገር በመከላከል ህያው ታሪክ የሰራና እየሠራ የሚገኝ ህዝባዊ ኃይል ነው፡፡
በ2014 በጀት ዓመት ያሳለፍነው የሥራ ዘመን የሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን የሠራዊቱን ሁለገብ ዝግጅት ለማጠናከር የሚያስችል የመከላከያ ኢንዱስትሪ እና የመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፎች በአዲሱ አደረጃጀትና የሠው ኃይል አመራር እና አዳዲስ አስተሳሰብ በመምራት አምራች የሚሆኑበትን፣ ኢትዮጵያን የሚመጠንና የሚመስል ሠራዊት ለመገንባት የሚያስችል ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች የተሰሩበት፣ አዳዲስ የውጊያ አቅሞችና አደረጃጀቶች የፈጠርንበት፣ ከተለያዩ ሃገሮች ያለን ዲፕሎማሲያዊና ወተደራዊ ትብብር ሥራዎች ያጠናከርንበት አመት ነው፡፡
በታሪካዊ ጠላቶቻችንና በተላላኪ ባንዳዎች አማካኝነት የተከፈቱ ጥቃቶችንና የሽብር ተልዕኮዎችን በታላቅ ተጋድሎና ጀግንነት በድል ያሳለፍንበት አመትም ነው፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ስራዎችን የተለያዩ የማህበረሰባችን ክፍሎች እንዲያዩትና እንዲጎበኙ ተደርገዋል፡፡ በዚህም ህዝቡ በመከላከያ ላይ ያለውን የባለቤትነት ስሜትና እምነት የሚያጎለብቱ ብቻ ሳይሆኑ ከልብ የመነጩ አወንታዊ አስተያየቶች የቀረቡበትና የሥራ ወኔአችንን ከፍ ያደረጉ በቀጣይም ጠንክረን እንድንሰራ ስንቅ ሆኖ ያገለገለን መርሀ-ግብር መሆኑን ያየንበት ነበር፡፡
በሁሉም ህዝብ ተሳትፎ እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ በ2014 መንግስት ያቀዳቸውን ሶስተኛ የውሃ ሙሌትና ሁለት ተርባይኖች ወደ ኃይል የማስገባት ግቦች እንዳይሳኩ በግንባታ ቦታ የፀጥታ ችግር በመፍጠር የግብአት አቅርቦት ሂደት እንዲስተጓጎል፣ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው ያካሄዱት የተናበበ ሥራ በማክሸፍ የውሃ ሙሌቱም ሆነ ኃይል የማመንጨት ስራዎች እንዲሳኩ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ከፍተኛ ሚና ነበረው፡፡
ውድ የመከላከያ ሠራዊትና የተቋሙ ሲቪል ሠራተኞች!
የዚህ ሁሉ ድል ቁልፍ ሚስጥር በደጀን ህዝባችንና በተቋሙ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ክፍሎች ያላቸው ትስስር የላቀና የሠራዊታችንን ተልዕኮ መሠረት በማድረግ የተገኘ ውጤት መሆኑን በእርግጠኝነት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ለማንም የማይበገርና በእሳት ተፈትኖ ብቃቱና ጀግንነቱ የተረጋገጠ የመከላከያ ሠራዊት ባለቤት ሆናለች፡፡ ይህ ጀግና ሠራዊት እንዲገነባ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የዜግነት ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ ልጆቹን መርቆ ወኔና ጀግንነት አስታጥቆ በመሸኘት ኢትዮጵያን ማንም የጎመጀ ጠላት ሊደፍራት እንደማይችል አስመስክሯል፡፡ ቤት ያፈራውን ስንቅ በማዘጋጀትም የሠራዊቱ አቅም እንዲፈረጥም አድርጓል፡፡ ህዝቡ ጠንካራ ደጀን በመሆንም ሠራዊቱ ጠላቱን እንደ እሳት በሚጋረፍ ሞራልና ስነ-ልቦና እንዲደመስስ የበኩሉን ታሪካዊ አሻራ አሳርፏል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት ከዋናው ተልዕኮ ጎን ለጎን ሠራዊታችን ካበረከታቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች በቋሚነት ችግር ያለባቸው ተማሪዎችና የህብረተሰብ ክፍሎችን በመርዳት፣ አቅመ ደካሞችን የቤት ባለቤት ለማድረግ የህንፃ ግንባታ ማከናወን፣ የሰብል እህል መሰብሰብን፣ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ከህዝቡ ጋር የተደረጉ ተሳትፎዎች በ2015 አዲስ ዓመት የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለመላው ሠራዊታችን እና ለመከላከያ ሲቪል ሠራተኛው፣ የጤና፣ የሠላምና ድል፣ የብልፅግና ዘመን እንዲሆንልን የመልካም ምኞቴን መልዕክት አስተላልፋለሁ፡፡ሁላችንም የሚጠበቅብንን እንወጣ።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J