“የኢትዮጵያን ጠላቶች አንድ ኾነን እንመክታለን፤ አዲሱን ዓመት በፍቅርና በተስፋ እንቀበላለን” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው

188

ሁመራ: ጳጉሜን 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የ2015 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ለዓመታት ስቃይ በበዛበት፣ መከራ በፀናበት፣ ሞትና መሰደድ በጠነከረበት የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ አልፏል። ዛሬ ላይ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ተጥሎበት የነበረውን የመከራ ቀንበር በትግሉ አሸንፎ አዲስ ዓመትን በደስታ እየተቀበለ ይገኛል። ነፃነቱን አስመልሷል፣ በማንነቱ ተውቧል፣ በባሕሉ አጊጧል። መላው የአማራ ሕዝብም “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” በማለት በአንድነት ታግሎ የትግሉን ፍሬ አይቷልም ብለዋል።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ መስፈሪያ የሌለውና ታሪክ ፈጽሞ የማይረሳው በደል ፈጽሟል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ዛሬም እንደ ትናንቱ ሁሉ ግፍ እያደረሰ ነው። ኹለት ጊዜ ጦርነት ከፍቶ በሽንፈት የቋጨው የሽብር ቡድኑ ሦስተኛ ወረራና ጦርነት ከፍቷል። አሸባሪው ቡድን የከፈተው ጦርነት በጀግና የኢትዮጵያ ልጆች እየተመከተ ነው። አሁንም በኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ ይመከታል ብለዋል።

አቶ አሸተ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ በአንድ እጁ ጠላቱን በሌላኛው እጁ ደግሞ ልማቱን እያለማ እንደሚገኝ ገልጸው የዞኑ አስተዳደር እና ሕዝቡ በቅንጅት እየሠራው ባለው ሥራ በተደጋጋሚ የወረራ ሙከራ ያደረገውን የሽብር ቡድን ጥቃት ሲመክት ቆይቷል። ወደፊትም በአንድነት እየመከተ ሰላሙን ያስጠብቃል። ማንነቱን ያስከብራል ብለዋል።

በአዲሱ ዓመት የዞኑን ሕዝብ ጥያቄ ለማስመለስ አበክረው እንደሚሠሩ የገለጹት አሥተዳዳሪው ሰላሙን እያስጠበቀ በአዲሱ ዓመት ልማቱን እያስቀጠለ ወደ እድገት እና ብልጽግና ያመራል ብለዋል።

ዋና አሥተዳዳሪው ወልቃይት ጠገዴ ለአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የሚያቃጥል እሳት ኾና ትኖራለች ነው ያሉት። የመከራው፣ የስቃዩ፣ የመገደሉና የመሣደዱ ዘመን አክትሟል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በአንድነቱ ማንነቱን አስከብሮ እንደሚኖር አስገንዝበዋል።

አዲስ ዓመትን ስንቀበል በተስፋና ለልማት በተነሳ ልቦና መኾን እንደሚገባው አቶ አሸተ ገልጸዋል። በዓሉ ሲከበር ለሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት መስዋእት እየከፈለ ለሚገኘው የጥምር ጦር ድጋፍ በማድረግና ጧሪ የሌላቸውን የተቸገሩትን በመርዳት ሊኾን እንደሚገባም ተናግረዋል።

አንድነት ምን ያክል የድል ምስጢር እንደኾነ አይተናልና አሁንም የበዙትን ጠላቶች ለመመከት እና ክልሉን ሰላማዊ በማድረግ በልማት ለማሳደግ አንድነትን ማጠንከር ያስፈልጋል ብለዋል።

አዲስ ዓመት ሲከበር አካባቢን በንቃት እየጠበቁ መኾን እንዳለበት ያነሱት አሥተዳዳሪው ኹሉም ኢትዮጵያዊ ከከፋፋይ ሴራ ራሱን አላቆ አንድነትን፣ ፍቅርን መተባበርን በአዲሱ ዓመት ሊያስቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleእንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ፣ አደረሰን! ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአዲስ አመት እንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
Next article“በአዲሱ ዓመት ለሀገራችሁ እያደረጋችሁ ያላችሁትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እጠይቃለሁ” አምባሳደር ስለሺ በቀለ