
ወልድያ፡ ጳጉሜን 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ሰላማዊ አማራጮችን ሁሉ ጥሶ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ ግልጽ ጦርነት ካወጀ ሳምንታት እየተቆጠሩ ነው።
በእያንዳንዷ የሽብር ቡድኑ ፀረ-ኢትዮጵያዊ እንቅስቃሴው ሁሉ የሰላም እጆች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ባይታጠፍበትም የሰላም አማራጭ እድሎቹን ሊጠቀምባቸው ግን አልፈለገም።
የሽብር ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ወረራ እና ጦርነት የያዛቸውን አካባቢዎች በሰላም ለቆ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ተጠይቋል። በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከሚያደርሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ይባስ ብሎ ለሦስተኛ ዙር ኢትዮጵያን በመውረር የለየለት የሽብር ቡድን መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በድጋሚ አሳይቷል።
ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሽብር ቡድኑን ሦስተኛ ዙር ወረራ እና ትንኮሳ ማውገዛቸውን ተከትሎ እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ሃሳቦችን ሲሰነዝር መደመጥ የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
የጦርነት አቅም የፈጠረ በመሰለው ጊዜ “ከአማራ ሕዝብ የማወራርደው ሒሳብ አለኝ” ሲል የሚደመጠው የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ መውጫ መግቢያ ሲያሳጣው ደግሞ ብሔር እየለየ እና ቡድን እየነጠለ ጠብ የለኝም የሚል የተማጽኖ ምልጃ ይልካል።
በትግሪኛ መፎከር፣ በእንግሊዝኛ መለመን እና በአማርኛ መሳደብ የሽብር ቡድኑ የተለመደ ቅጥፈት ቢሆንም አሁን ደግሞ በማኒፌስቶ ጠላት ያለውን እና ሒሳብ አወራርድበታለሁ፤ አንገቱንም አስደፋዋለሁ ያለውን የአማራ ሕዝብ የፀጥታ መዋቅር ለማታለል ሲሞክር ተደምጧል።
የሰሞኑ የሽብር ቡድኑ ሕወሓት አዲስ የጦርነት እና የፕሮፖጋንዳ ስትራቴጂ ምን እንድምታ ይዟል ሲል የወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) አነጋግሯል።
አሸባሪው ሕወሃት ለተከታታይ ሦስት ዙር ጦርነት እና ወረራ ከፍቶ ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ጉዳት ያደረሰበትን ማኅበረሰብ “ጠብ የለኝም” ማለት የለየለት ተቃርኖ ነው ያሉን በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጥናት መምህር ሙሉነህ ደምሴ ናቸው። በሁለተኛው ዙር ወረራ የወልድያ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ በርካታ ማኅበራዊ ተቋማትን አውድሟል ያሉት መምህር ሙሉነህ ከአንድ ማኅበረሰብ ጋር “ጠብ የለኝም” ለማለት ከዚህ የበለጠ ምን ግፍ ሊፈጽም ፈልጎ ነበር ሲል ይጠይቃሉ።
“የሽብር ቡድኑ ሕወሃት ሥሪቱ እና ፍጥረቱ በተቃርኖ የተሞላ ነው” ብለዋል መምህር ሙሉነህ፡፡

አሸባሪው ሕወሃት የተለያዩ አካባቢዎችን በኀይል በወረረ ማግስት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወረራ እና ጦርነት እንደተከፈተበት ያስመስላል። ለሰላም አማራጮች ፈቃደኛ ነኝ እያለ የሚያታልለው የሽብር ቡድኑ በሌላ በኩል የኮንክሪት ምሽጎችን ገንብቶ በንጹሃን ላይ የጦርነት ማዕበል ይፈጽማል፤ ይኽም የሽብር ቡድኑን የለየለት ጠብ አጫሪነት ያሳያል ነው ያሉት መምህር ሙሉነህ።
በሦስተኛው ዙር ወረራ እና ጦርነት በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከመኖሪያ ቀየው መፈናቀሉን የጠቀሱት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ መምህር ኤፍሬም ይላቅ ናቸው። ይህን ያህል ሕዝብ ከመደበኛ መኖሪያ ቀየው በተፈናቀለበት፣ ሃብት ንብረቱ በተዘረፈበት እና ንጹሃን ሕይዎታቸውን ባጡበት ጦርነት “ከአማራ ሕዝብ ጋር ጠብ የለኝም” ማለት የለየለት ተቃርኖ ነው ብለዋል መምህር ይላቅ።
መምህር ኤፍሬም የሽብር ቡድኑ ሕወሃት የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ለመሳብ እና የውስጥ አንድነትን ለመሸርሸር የተለየ አካሄዶችን እያሳየ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ጦርነቱ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ብቻ ሳይሆን በስንቅ እና በትጥቅ ከሚደግፉት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል። ወረራውን በማያዳግም ደረጃ በመቀልበስ በወረራው የተጎዳውን ሕዝብ ማኅበረሰባዊ መረጋጋት ማምጣት ግድ እንደሚልም ገልጸዋል።
አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮጵያ የኅልውና ስጋት በመሆኑ በጋራ መቆምን እና መተባበርን ይጠይቃል ብለዋል። የሽብር ቡድኑ ሕወሓት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለውጭ አጋልጦ እየሰጠም ስለሆነ ከተራዘመ ጦርነት ወጥቶ ብሔራዊ ጥቅምን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ ትብብር ያሻል ነው ያሉት። በፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ በደጀንነት እና በግንባር በመዝመት ኢትዮጵያን መታደግ ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ ነው ብለዋል ምሁራኑ።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው -ከወልድያ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
