“2014 ዓ.ም የአሸባሪው ሕወሃት ወረራን በመመከት የኢኮኖሚ ጫናውን ለመቋቋም ጥረት የተደረገበት ነበር” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

147

ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በ2014 በጀት ዓመት ለመልሶ ግንባታና ለልማት ሥራዎች ትኩረት በመስጠት ጦርነቱ ጫና ያሳደረበትን ኢኮኖሚ ለማቋቋም ውጤታማ ሥራዎች የተከናወኑበት መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ባሳለፍነው ዓመት አሸባሪው ሕወሃት በሰላም ወዳዱ የክልላችን ሕዝብ ላይ ወረራ በማድረግ መላው ዓለም ያዘነበትን ሰቆቃ፣ የዘር ፍጅት፣ መፈናቀል፣ የሀብት ውድመት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽሞብናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ታጋሹና ጀግናው ሕዝባችን ግን ከጸጥታ ኃይላችንና ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ አኩሪ ገድል ፈጽሟል ብለዋል።
በአሸባሪው ሕወሃት የተፈናቀለውን የክልሉን ሕዝብ መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ ሀብቶችን ለመገንባት መላው የክልሉ ሕዝብና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ላሳየው ርብርብም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሁለተኛው ዙር ወረራ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ከተቀለበሰ በኋላ የመልሶ ግንባታና የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት በመደረጉም የበጋ ስንዴ ልማታችን፣ የክረምት ግብርናችን፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እጥረትን ለመፍታት ያደረግነው ንቅናቄ፣ የአረንጓዴ ልማት ሥራችን፣ የኢንቨስትመንት እድገታችን በእጅጉ አበረታችና ሀገራዊ የብልጽግና ተስፋችንን ያሳደገ ነበር ብለዋል።
የሀገራችንን ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ብሔራዊ የሰላም የውይይት መድረክ የአማራ ክልል ሕዝብና መንግሥት ጽኑ እምነት ያለው ቢሆንም ለሰላም አማራጭ በሩን የማይከፈተው አሸባሪው ሕወሃት በተደጋጋሚ ሕዝባችን ላይ ወረራ እየፈጸመ ይገኛልም ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ለደቂቃም ቢሆን አሸባሪው ሕወሃትንና የትግራይን ሕዝብ አንድ አድርገን አንመለከትም ያሉ ሲሆን፤ መንግሥታቸውም የትግራይና የአማራ ሕዝብ ወንድማማችነት በአሸባሪው ቡድን የጠላትነት እንቅስቃሴ እንዳይገታ አበክሮ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የክልላችን ሕዝብ ለሰላም ዝግጁ የመሆኑን ያክል ክብርና ማንነቱን ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ አንድነት ጠላት የሆነውን ኃይል ከሚፋለመው ጥምር ኃይል ጎን ተሰልፎ ባሳየውና እያሳየ ባለው አኩሪ ደጀንነቱ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል።
በመጪው የ2015 አዲስ ዓመት የተጋረጠብንን ወረራ በመቀልበስ፣ የሕዝባችንን ውስጣዊ አንድነት አስጠብቀን ለሰላምና ለልማት በጽናት በመረባረብ፣ የገጠመንን የኑሮ ውድነት ፍትሃዊ የገበያ ሥርዓት በማስፈንና የተጀመረውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ እድገት ማሻሻያ በስኬት በመተግበር ዓመቱ ለመላው ሕዝብ የድል፣ የሰላምና የልማት ዓመት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleግንባር ድረስ የዘለቀው ደጀንነት!!
Next article“አሸባሪው ሕወሃት ሥሪቱ እና ፍጥረቱ በተቃርኖ የተሞላ ነው” በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጥናት መምህር