
ሑመራ፡ ጳጉሜን 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “በማይካድራው ጭፍጨፋ ወቅት በዓይኔ ያየሁት የአማራ ሕዝብ ብዙ ተገድሏል” ሲል ለወገን ጦር እጁን የሰጠ የአሸባሪው ሕወሃት ታጣቂ ምርኮኛ ተናገረ።
ምርኮኛው ፍስሃ ገብረ ሚካኤል ይባላል። በማይካድራ ከተማ ነበር ነዋሪነቱ። በማይካድራ በግብርና ሥራ ይተዳደር እንደነበርም ይናገራል። ወደ ትግራይ ከሄደ በኋላ ደግሞ የሽብር ቡድኑን ተቀላቅሏል። ለሽብር ቡድኑ ሲዋጋ ሀገሩን ከወረራው እየተከላከለ ላለው ሠራዊት እጁን ሰጥቷል። እጁን የሰጠው በወልቃት ጠገዴ ለሚገኘው ሠራዊት ነው። የሽብር ቡድኑ ማይካድራን ለቆ ሲወጣ ባዘጋጃቸው ገዳዮች አማራዎችን እየመረጠ ገድሏል ነው ያለው።
“በከተማዋ የሳምሪ ቡድን በርካታ አማራዎችን እየመረጠ ገድሏል፣ ማይካድራ ላይ ስለ ወደቀው አስከሬን የምንናገርበት አንደበት የለንም ብሏል። የግድያ እቅዱን ያወጣው ሕወሓት እንደኾነም ገልጿል። ገዳይ ቡድኑ ከበረሃ ሳሉጎች እና ከታጠቁ ፖሊሶች የተውጣጣ ነበር” ሲል ተናግሯል ።
“የገደሉትን ሰው እሳት እያነደዱ ሲያቃጥሉ ነበር” ብሏል ።
የመከላከያ ምት ከአቅማችን በላይ ነው ያለው ፍስሃ፤ ሕይወቱን ለማትረፍ ለመከላከያ ሠራዊት እጁን መስጠቱንም ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ ከመከላከያ ጋር ኾኖ መጣብን፣ ኢትዮጵያ በሙሉ ልትበላን ነው፣ አሁን ትግራይ ከገቡ አይደለም ሰው ቅጠል አይቀርም፣ ተነስ እያሉ በኀይል ያስነሱታል፣ በኀይል ተጎትቶ ይገባል ብዙው ወዲያው ይከዳል” ብሏል።
ከራያ ጫፍ፣ እስከ ጠለምት ጫፍ ከዚያም እስከ መተማ ጫፍ የትግራይ መሬት ነው እናስመልሳለን ይላሉም ብሏል። መሣሪያ ከጠላት ወይም ከተሰዋ ጓደኛህ አንሳ እንባላለንም ነው ያለው።
“በማይካድራ የአማራ ሕዝብ ተጨፍጭፏል፣ ከአንድ ቤት ቆፍቁፈው ሲያወጡት ስድስት አለያም ሰባት ይገኛል ያኔ ይገደላል፣ አንድም የሚያመልጥ የለም፣ ሰው በጊዜ ከቤቱ ገብቶ ስለነበር፣ በዓይኔ ያየሁት የአማራ ሕዝብ ብዙ ሞቷል” ብሏል።
“አንዲት ኢትዮጵያን እመኛለሁ፣ ጎጠኝነት ይብቃን ፣ ውጊያው በቃን ብሏል። ኢትዮጵያ አንድ ኾና ወደፊት እንድትራመድ እፈልጋለሁም” ሲል ገልጿል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
