
ጳጉሜን 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግና ሕዝብ ለጀግኖቹ ክብር ይሰጣል። ሀገሩንም በጀግንነት ይጠብቃል።
ጀግንነት በእርግጥ ወደ ጦር ግንባር ስለመዝመትና ስለመዋጋት ብቻ አይደለም። በቀደመው ዘመን እንደዛ መኾኑ ትክክል አልነበረም ማለት ግን አንችልም። ያኔ በትምሕርት አዋቂ ሆኖ አራት ዓይና ከመባል በላይ በጦር ደርጅቶ ግዛትን ማስከበር ነበር ጀግንነት። ይህም ደግሞ ለኢትዮጵያ ትርፍ እንጂ ብዙ ኪሳራን አላመጣም፡፡ ጀግና ከየት ይምጣ? እያልክ ለምንስ ትብሰለሰላለኅ፣ ጀግንነነት ከየትም በምንም ሊሆን ይችላል፡፡
በየዘመኑ እልፍ ጀግኖች ጀግንነታቸዉን በዉል ገልጠዉ ሁሌም የሚታወሱበትን ሥራ አስቀምጠዉ ያልፋሉ፡፡ ዛሬ ላይ ጀግንነትን በብዙ መንገድ መተርጎም ይቻላል፡፡ አሁን ባለዉ ነባራዊ ሁኔታ ግን ሀገር ካለባት ችግር እንድትገላገል ከማድረግና ከማገዝ የበለጠ ጀግንነት ከየት ሊመጣ ይችላል?
አዎ ከየት ሊመጣ ችላል? ጀግናህን ታከብራለህ፡፡ ግን ደግሞ አንተም ጀግና ኾነህ የምትከበርበትና የምትዘከርበት እድል ከፊት ለፊትህ ነዉ ያለዉ፡፡ ሀገር በሽብር ቡድኑ ትህነግ ታምሳ እየተቆላች ባለችበት በዚህ ወቅት እልፍ ጀግኖች በግምባር ተሰልፈዉ ለሀገር መክፈል ከሚገባቸዉ በላይ ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ አሁን ላይ ሁሉም ጀግኖችን እያወደሰ ይገኛል፡፡ ማመስገኑ ማወደሱ አንደኛዉ ጉዳይ ቢኾንም ከጎናቸዉ ተሰልፎ ከጀግኖች አወዳሽ ወደ ጀግኖች ጎራ ለመቀላቀል ምንም የሚያግድ ነገር የለም፡፡
ከጀግና ጋር መዋል ከጀግና ጎን መሰለፍ ወደ ጀግንነት መንደርደሪዉ መንገድ ነዉ፡፡ እናም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ጠላትን በግንባር ድባቅ እየመቱ ሀገርን ለማጽናት በዱር በገደሉ ሲዋትቱ አለሁላችሁ የምንልበት ወቅት ጊዜዉ አሁን ነዉ፡፡
አሜሪካዊዉ ታዋቂ የስነ ልቦና ምሁሩ ፕሮፌሰር በርናርድ ዌይነር ስለ ፍቅር ሲናገሩ “የፍቅር መስፈሪያዉ ስፍር አልባዉ ፍቅር ብቻ ነዉ” ይላሉ፡፡ አንደኛ ህይወቱን ሳይሳሳ ለሀገሩ ፍቅር መገለጫ እየሰጠ ላለዉ የወገን ጦር ፍቅርን እና ደጀንነትን ማሳየት ደግሞ በዚህ ወቅት መሠራት ካለባቸው ጀብዱ ውስጥ አንዱ ነዉ፡፡
ሀገርን በደሙ ለማጽናት ደሙን እያፈሰሰ ላለዉ ፍቅርን እየሰጠ ሞትን ለሚጎነጭ ትክክለኛ ሀገርና ወገን አፍቃሪ ዉለታዉን የምንመልሰዉ ለሰጠን ፍቅር ተስተካካይ እንኳን ባይኾን የቻልነዉን አጋርነት ማሳየት ግድ የሚልበት ወቅት አሁን ነው፡፡
የወገን ጦር ደጀንነት ከግንባር እስከ መንደር ይዘረጋል፡፡ ግንባር ላይ ፊት ለፊት የጠላትን አንገት ሲቀላ አለሁልህ ማለት ሲቆስል ማንሳት፣ ሲራብ ማብላት፣ ሲጠማ ማጠጣት እና ከግንባር በተጨማሪ የአካባቢን ሰላም መጠበቅ ስፍር አልባ ፍቅር እየሰጠን ላለዉ ጦር ቢያንስ እንጅ የሚበዛ አይደለም፡፡ የሽብር ቡድኑ ህወሓት የከፈተዉን ወረራ ለመመከት ከሊቅ እስከ ደቂቅ የደጀንነቱ እና የሀገር መዉደዱ ጉዳይ በተግባር እየተገለጠ እየታየ ነዉ፡፡ የዛሬ ታጋዮች የነገ ባለታሪክ እና ጀግኖች ለመኾንም ስማቸዉን በደማቅ ታሪክ ጽፈዉ ለማለፍ ሚሊዮኖች ስለአንዲት ሀገር በጋራ ቆመዋል፡፡
ለሀገር ክብር በኩራት የሚከፈል ዋጋ የነገ ደማቅ ታሪክ ነዉና ለጀግኖች ክብር በመስጠት አንተም ጀግና ሁን! አንቺም ጀግና ሁኚ!
በኤልያስ ፈጠነ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J