
ወልድያ፡ ጳጉሜን 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዶክተር ዶናልድ ሊቨን “የአሁኒቷን ኢትዮጵያ የሠሯት ወሎየዎች ናቸውና ምስጋና ይገባቸዋል” ሲሉ ከሚያሞካሿቸው የወሎ ግዛቶች አንዱ የጁ ነው።
“የጁ የእግዜር መሐል እጁ” እንዳለ ባለቅኔው የጥንታዊው የጁ ግዛት መናገሻ ወልድያ በጦርም በንግድም ስሟ ገናና ነው። ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ የሚመጡ ሲራራ ነጋዴዎች መገናኛቸው ወልድያ ናት።
ወልድያ እንደ ከተማ ከተቆረቆረች ከ235 ዓመታት በላይ ማስቆጠሯን ታሪክ ይነግረናል። ጎንደርን ከወሎ አስማምተው እና አስተባብረው እንዳሥተዳደሩ የሚነገርላቸው ታላቁ ራስ አሊ ደግሞ የወልድያ ከተማ መሥራች ናቸው ይባላል።
በ1777 ዓ.ም ገደማ ታላቁ ራስ አሊ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከሚገኘው ታላቁ ቤተ መንግሥታቸው ላይ ሆነው ወደ ታች ይመለከታሉ። የታላቁን ራስ አሊ ዕይታ የሳበው አካባቢ ደግሞ በቀድሞ መጠሪያው አዋጅ መንገሪያ በአሁኑ መጠሪያው ማክሰኞ ገበያ የሚባለው አካባቢ ነበር።
ታላቁ ራስ አሊ በጥቅጥቅ ጫካ ወደተከበበችው ማክሰኞ ገበያ እየተመለከቱ የሚያስተውሉትን ነጭ ነገር አጣርቶ እንዲመጣ አገልጋያቸውን ይልኩታል። የተላከው ግለሰብም በአካባቢው እንደደረሰ የአንዲት ወላድ ልብስ ተሰጥቶ ይመለከታል። ሲመለስም ነጩ ነገር ምን ነበር ተብሎ በንጉሡ የተጠየቀው ግለሰብ “ወልዳ” ብሎ መመለሱን ተከትሎ ከተማዋ ወልድያ ተባለች የሚሉ አሉ። በሌላ በኩል በአራቱም አቅጣጫ የመጡ ሲራራ ነጋዴዎች መገናኛ በመሆኗ ወልድያ ተባለች የሚሉም አልታጡ።
ወልድያ ከአፋር እስከ ትግራይ፣ ከጅቡቲ እስከ ሀረር ወደ ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚመጡ ነጋዴዎች መገናኛቸው ናት።
ጥንታዊው ማክሰኞ ገበያ ደግሞ ከጥንት እስከ ዛሬ ከአሞሌ እስከ ጠገራ ብር፤ ከፈረንካ እስከ ወረቀት ብር ለሻጭ ለዋጮች ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። ዛሬም ከሳንቃ እስከ አዳጎ፣ ከወልድያ እስከ ሲሪንቃ፣ ከመርሳ እስከ ውርጌሳ፣ ከዶሮ ግብር እስከ ሃራ፣ ከዋጃ እስከ ተኩለሽ፣ ከቆቦ እስከ አዘቦ፣ ከራያ እስከ ጊራና ሲራራዎችን እያገናኘ የንግድ፣ የባሕል እና የሕዝብ ለሕዝብ መረጃ ልውውጥ ይደረግበታል።
ተራሮችን ተንተርሳ የተመሠረተችው ወልድያ ከተማ በጦር ሜዳ አውደ ውሎም በርካታ ታሪክ ተሠርቶባታል። የአሸናፊ ተሸናፊ እጣ ፋንታን የቀየሩ፣ ለሀገር የተከፈለ መስዋዕትነትን የዘከሩ እና ታሪክን ለትውልድ ያሻገሩ ጀብዱዎች ተፈጽሞባታል።
ላስታን ከዛጉየ፤ ራያን ከወሎ በጋራ የምትቀኘው የየጁዎች መናገሻ በኢትዮጵያ ታሪክ አያሌ ውጣ ውረዶችን በድል ተሻግራለች። ከእነዚህ መካከል የታላቁ ራስ አሊ መናገሻ ወደ ደብረ ታቦር ማቅናቱን ተከትሎ ሽፍቶች ለሲራራ ነጋዴዎች እንቅፋት መሆናቸው ይጠቀሳል። ይህን ተከትሎም የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲህ ተቀኙ፦
“ማማው ደብረ ታቦር ደጋሌቱ የጁ፣
ወንጭፍ አጠረና ወፎች እህል ፈጁ።”
ዛሬም ጥንታዊዋን የየጁ መናገሻ ለመረበሽ ግሪሳ ወፎች ቢዞሯትም ማክሰኞ ገበያ ከአራቱም አቅጣጫ የመጡ ሲራራዎችን ከማስተናገድ አላገዱትም። ግሪሳው በወንጭፍ እየተለቀመ ጎን ለጎን ከፍ ያለ የሥነ ልቦና ባለቤቱ የአካባቢው ሲራራ ነጋዴ በማክሰኞ ገበያ “አማን ናችሁ?” እየተባባለ ይገበያያል። አይፈሩም፤ አይኮሩም ሲራራ ብቻ ሳይሆን ልበሙሉ ጀግናም ማክሰኞ ገበያ ሞልቷላ።
በታዘብ አራጋው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J