
ጳጉሜን 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ወታደር የሚለው መጠሪያ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ከተመሠረተ ጀምሮ ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል። ቀድሞ በነበረችው ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት የሚያስከብሩ እና ለሕዝባቸው ደኅንነት ዘብ የሚቆሙ ሁሉ መጠሪያቸው በየዘመኑ የተለያየ ነበር። በዱር በገደሉ ወጥተው፣ ወርደው እና ቀርተው የሀገራቸውን ነጻነት የሕዝባቸውን ደኅንነት ያረጋገጡ ሁሉ የጦር ጭፍራ፣ የጦር ሠራዊት፣ ወጥቶ አደር፣ ዘማች፣ ጦረኛ እና ተዋጊ በሚል መጠሪያ ሲጠሩ ቆይተዋል።
የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን የባርነት ሸማ የቀደዱ፣ የአፍሪካ አህጉርን የቅኝ ግዛት ዘመን ወረራን ያወራረዱ እና ቅኝ ገዥዎችን በዓድዋ ተራሮች ያንበረከኩ የሀገር ባለውለታዎች ደግሞ መጠሪያቸው አርበኛ የሚል ሆነ።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ዛሬ ካለችበት ደረጃ እንድትደርስ የግል ምቾታቸውን ትተው፣ ሕይዎታቸውን አወራርደው እና ቤተሰቦቻቸውን ረስተው ያሻገሯት ወታደሮች ባለውለታ ናት።
ለሀገር ወታደር ሆኖ መቆም በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ዘንድ የተለየ ክብር ነበረው። ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል ዘብ ሆኖ መሰለፍ የራሱ የሆነ ዘውድ እና ሞገስ አለው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙር በሚሰማበት ሁሉ የወታደር ትውስታ የጎላ ነው።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ በተውለበለበበት ከፍታ ሁሉ ወታደር ከቀለማቷ ጋር ደምቆ ይታያል። ኢትዮጵያ በተጠራችበት የከፍታ አውድ ሁሉ ወታደር አሻራው ጉልህ ነው።
ወታደር ኢትዮጵያን በአጥንቱ ያቆማት፣ በስጋው የሠራት እና በደሙ ያቀለማት ምድር ነች። በየዘመኑ የነበሩ እና በተለያየ ስያሜ የተጠሩ የሀገር ዘቦች በኢትዮጵያ የዘመናት አኩሪ ታሪክ ውስጥ ድርሻቸው ላቅ ያለ ነው።
ወታደር የኢትዮጵያን ክፉ ዘመን ሁሉ ድልድይ ሆኖ አሸጋግሯል። ወታደር መጥፎ የተባሉትን የኢትዮጵያዊያን የእርስ በርስ ግጭቶች ሳይቀር አብርዶ ወደ ሰላም ቀይሯል።
ወታደር ከኮሪያ እስከ ሊቢያ፤ ከኮንጎ እስከ መቋዲሾ ዘምቶ ለዓለም ሰላም መስፈን ሳይቀር የድርሻውን ተወጥቷል፤ ሀገሩንም በዓለም አደባባይ አስጠርቷል።
በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር ሁሉ ደሙን ያፈሰሰው፣ አጥንቱን የከሰከሰው እና ስጋውን የቆረሰው ወታደር ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የታሪክ እጥፋቱ ዘመን ሆነ። ወታደር የሚለው ሙያ እና መጠሪያ ደርግ ከሚባል ሥርዓት ጋር ብቻ ተቆራኝቶ የደርግ ወታደር የሚል ያልተገባ እና የተዛባ ትርጓሜ ያዘ። ይህ በዘመነ ኢህአዴግ የወታደርነትን ክብር አደብዝዞ ለአንድ ብሔር መሰባሰቢያ ጓዳ ለማድረግ ታስቦ የተሰራ ሴራ ነበር።
የእኛ ዘመን ትውልድ ውትድርናን በተዛባ አውድ ሆን ተብሎ እንዲረዳው ተደረገ። ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ሲገባ እና ማታ ከትምህርት ቤት ሲወጣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙር እንዳይዘምር የተደረገ ትውልድ በውትድርና ሙያ ላይ ብዥታ ቢፈጠርበት ምን ይገርማል። ይኽ ብዥታ ኢትዮጵያን ምን ያክል እንደጎዳት እና ለአሁናዊዎቹ የኅልውና ፈተናዎች እንደዳረጋት መገንዘብ አያዳግትም።
ወታደር ማለት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ብሔራዊ ዓርማ እና ኩራት ነው። ኢትዮጵያ ዋጋዋ ስንት ነው ቢባል በደሙ መዝኖ፣ በአጥንቱ ተምኖ እና በሕይዎቱ ተሸክሞ ትክክለኛ ዋጋዋን የሚያውቀው ወታደር ብቻ ነው።
ወታደር ለዓላማ እና ለአቋም የሚፋለም፤ ለመርህ እና ለእውነት የሚታገል ነው። ወታደር የሀገር ፍቅሩን እስከ ሞት በዘለቀ መስዋእትነት የሚገልጽ እና የሀገር መኖር በወታደር መኖር የሚጸና ነው።
ኅልውናዋ ከውስጥም ከውጭም ለሚፈተነው አሁናዊቷ ኢትዮጵያ ወታደር ሆኖ ከማገልገል የተሻለ የሀገር ፍቅር መገለጫ የለም።
በየአካባቢው ለሚሳደደው ወገን ወታደር ከመሆን የተሻለ ክብር አይኖርም። ተስፋ ከፊቷ ለሚታይ፤ ፈተና ከጉያዋ ለተጣባት ኢትዮጵያ ወታደር ከመሆን የተሻለ ውለታ አይገኝም።
በታዘብ አራጋው
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼