“ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሎቹ ግን ይጓዛሉ!”

193

ጳጉሜን 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ከአፈመዙ ይልቅ ምላሱ መርዝ ይተፋል። አሸባሪው ሕወሓት ከምሥረታው ጀምሮ እንደ ጦር ስልት ከሚጠቀምባቸው አማራጮች መካከል ጠላት ብሎ የፈረጀውን ሕዝብ እንደ ሕዝብ በጋራ እንዳይቆም የሐሰት ትርክት እየፈጠረ የልዩነት አጀንዳዎችን ማቀበል ቀዳሚው ተልዕኮው ነበር። ይህ የትግል ስልቱ አሁንም ድረስ ሊቀየር ቀርቶ ማሻሻያ እንኳን አልተደረገበትም።
የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ገና በትግል ዘመኑ ማለዳ እርስ በርሱ ተዋልዶ እና ተጋምዶ ለረጅም ዘመናት በአብሮነት የዘለቀውን ኢትዮጵያዊነት ጥርጣሬ ውስጥ ጣለው። አሸባሪው ሕወሓት በትግል ማኒፌስቶው የአማራ ሕዝብ ጠላቴ ነው ብሎ በግልጽ አወጀ። ማኒፌስቶውን የትግራይ ሕዝብ አምኖ እንዲቀበልም የረጅም ዘመን ጥንታዊ ሥልጣኔ እና የሥነ መንግሥት ታሪክ ያላትን ሀገር ከ100 ዓመት ያለፈ ታሪክ የላትም ሲል ተደመጠ። ይህ የታሪክ አረዳድ ስሕተቱ በበርካታ የትግራይ ልሂቃን ዘንድ ተቃውሞ እና ነቀፋ ቢገጥመውም የተወሰኑ ሕጻናትን ኢትዮጵያዊ ብሩህ እይታ ግን አደበዘዘው። ይኽ የተሳሳተ የታሪክ አረዳድ እና አካሄድ ራሱን ሕወሓትን የማታ ማታ ከኢትዮጵያዊነት እሳቤ ነጠለው።

ኢትዮጵያዊያን በቋንቋ፣ በባህል፣ በማንነት እና በብሔር ስብጥር መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ሕዝብ መሆናቸውን ወደ ጎን በመተው የተለየ እና ልዩ ዘር በመምረጥ እርስ በርስ በጥርጣሬ እና በጥላቻ እንዲተያዩ አደረገ። ይኽ አክራሪ የተለየሁ ዘር ነኝ ባይነት (Exceptionalism) አካሄዱ ውሎ ሲያድር የኅልውና አደጋ እስከመሆን ደረሰ። የትግራይ ሕዝብ ነባር እምነት እና እሳቤ በየትኛውም መንገድ ቢለካ ከኢትዮጵያዊነት የራቀ አይደለም።
የሽብር ቡድኑ ከመንበረ ሥልጣኑ ገሸሽ መደረጉን ተከትሎም እኔ የማልመራት፣ እኔ የማላስተዳድራት እና እኔ የበላይ የማልሆንባት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦልም ድረስ እወርዳለሁ ሲል በግልጽ ዛተ።
የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ኢትዮጵያን በአምሳሉ በፈጠራቸው፣ እንደጸባዩ በቀረጻቸው እና እንደ ግብሩ ባደራጃቸው ቡድኖች በአራቱም አቅጣጫ እረፍት ነሳት። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አደባባይ ላይ አውጥቶ እያሰጣ ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር መላላክ እና መገዳደርን የትግል ስልት አድርጎ ተጠቀመበት።
በመጨረሻም የማይነካውን ነክቶ የማይደፈረውን ደፍሮ ኢትዮጵያን ያለብሔራዊ ዘብ ለማስቀረት መከላከያውን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ፈጸመ። ይህ እኩይ ድርጊቱ በርካታ የዓለም ሀገራትን ያስደነገጠ ቢሆንም የእብድ ገላጋዮችን እና ዱላ አቀባዮችን እንዳላሳጣውም በግልጽ አመላከተ። ጦርነቱ በግልጽ ሲጀመር ኢትዮጵያን ለማጽናት እና ኢትዮጽያን ለማጣት የሚሞክሩ ቡድኖች በተቃራኒ ጎራ ተሰለፉ። ሕወሓት በለኮሰው የጦርነት እሳት ክፉኛ ተለብልቦ ከሞት እና ምርኮ ያመለጡት ዳግም ወደ ዋሻ ተሰገሰጉ።
ጦርነቱ ከአሃድ ውጊያ ወርዶ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሰለባዎችን አሰባሰበ። መከላከያም ጥቅም እና ጉዳቱን አስልቶ መቀሌን ለቆ ወጣ። ነገር ግን ከስሕተቱ ፈጽሞ የመማር ፍላጎትም ሆነ ተነሳሽነት የሌለው የሽብር ቡድኑ የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ ወደ ለየለት የሽብር ድርጊት መሸጋገሪያ አድርጎ ተጠቀመበት።
ዳግም ለሁለተኛ ጊዜ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ እና የወረራ መፈክር እያስተጋባ በርካታ የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ወርሮ መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አደረሰ። የወረራው ዓላማ ድፍን ኢትዮጵያ ብትሆንም ሒሳቡ ከአቅሙ ጋር የተገናዘበ ባለመሆኑ ሊጥም ነፍጥም አንጠልጥሎ እየተንጠባጠበ ከወጭ ቀሪ መቀሌ ደረሰ።
ከዚያ አስከፊ የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ በኋላ የሽብር ቡድኑ ዳግም ጦርነትን ምርጫው አያደርግም የሚሉ ቢኖሩም ከጥንታዊ ስሪቱ ተነስተው ሰላምን ምርጫው አያደርግም የሚሉት ግን በርካቶች ነበሩ። ሦስተኛው ዙር የአሸባሪው ሕወሓት የጦርነት ነጋሪት ግን በቀላሉ እሰከቻለው ደርሶ የንጹሐንን ሃብት እና ንብረት አግበስብሶ የሚመለስበት አይመስልም።
በተራዘመ የጦርነት እና የቀውስ ሂደት ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሞክረው የሽብር ቡድኑ ገና ከመጀመሪያው የቆይታ ገመዱን የሚያሳጥረበት ይመስላል። የሽብር ቡድኑን ማዕበል የኢትዮጵያ ጥምር ጦር በሁሉም አውደ ውጊያዎች እየመከተ ይገኛል።
የሽብር ቡድኑን መዳከም ያስተዋሉት የውጭ ረዳቶቹ እና የፕሮፖጋንዳ ጀሌዎቹ በአውሮፖ ጎዳናዎች ላይ መንከባለል ጀምረዋል።
ከሰሞኑ ሾልኮ የወጣው የሽብር ቡድኑ የጦርነት ስልትም አሁን እየሄደበት ያለውን የጥፋት ጉዞ በግልጽ የሚያሳዩ እና የሕወሓት የእጥፋት ዘመን መቃረቡን አመላካቾች ናቸው። ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ በተመሳሳይ የሐሰት ትርክት እና የውሸት ፕሮፖጋንዳ የሚጓዘው ቡድኑ ጥምር ጦሩን ለመከፋፈል እና ለማዳከም ብዙ ቢልም ትናንት አማራን ለማሸማቀቅ ይጠቀምበት የነበረውን አባባል ዛሬ እነርሱ መልሰው እየላኩለት ነው፤ “ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሎቹ ግን ይጓዛሉ!” በማለት።
የሦስተኛው ዙር ወረራ እና ጦርነት ዙሪያ መለስ እውነት ይኽ ሆኖ እያለ ትናንት እንዳደረጉት ሁሉ ዛሬም ጥምር ጦሩን በሐሰት ፕሮፖጋንዳ ለመፍታት እና ለማዳከም በለመዱት መንገድ መጓዝን መርጠዋል። “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል” ይላሉ ኢትዮጵያዊያን በብሂላቸው።
የተደራጀ እና ቀድሞ የነቃ ሕዝብ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ አንደበት ተናጋሪ አንድ ሆኖ በአንድነት የጋራ ጠላቱን በጋራ ይመክታል። የሚደማመጥ፣ የሚከባበር እና የጋራ ፍላጎት ያለው ኃይል ጠላቱ የቱንም ያክል ቢበረታ ከማሸነፍ የሚያቆመው ምድራዊ ኃይል አይኖርም። ምክንያቱም የአንድ ሕዝብ እውነተኛ አሸናፊነት የሚመነጨው ከጠላቱ ድክመት ሳይሆን ከራሱ የውስጥ ጥንካሬ የሚመጣ ነውና። ቻርለስ ዳርዊን እንደሚለው “ጠንካሮች አሸናፊዎች ናቸው፤ አሸናፊዎች ደግሞ የሕልውና ስጋት የለባቸውም።”
በአንጻሩ የተበተነ እና በየመሻቱ የቆመ ሕዝብ ግን ለጠላት ይመቻል። የቱንም ያክል ልዩነቶች እና አለመግባባቶች ቢፈጠሩ እንኳን የጋራ ጠላት እና የኅልውና ስጋት ሲመጣ ልዩነቶችን በይደር ትቶ በጋራ መቆምና የጋራ ጠላትን ማሸነፍ የሰለጠነ ሕዝብ መለያ ባህሪ ነው።
ጥንት ኢትዮጵያዊያን የጋራ የሆነ የኅልውና ስጋት ሲገጥማቸው የውስጥ ልዩነቶቻቸውን በይደር ትተው በጋራ መቆም እና ጠላቶቻቸውን በተባበረ ክንድ መደቆስ ቀድሞም የነበረ እና አሁንም ድረስ የቀጠለ መለያቸው ነው። ዛሬም እንደ ትናንቱ በኢትዮጵያ ኅልውና ስጋቶች ላይ የተበባረ ክንድን አሳርፎ ሀገርን ማጽናት ወቅቱ የሚጠይቀው ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው።
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች‼
በታዘብ አራጋው

Previous article“አንቺ 60 ዓመት ኾኖሻል አትሄጅም ተብዬ ነው እንጂ ውጊያ ልግባ ብዬ ነበር” የማይካድራዋ እናት
Next articleየኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ብሔራዊ አርማ እና ኩራት!