“አንቺ 60 ዓመት ኾኖሻል አትሄጅም ተብዬ ነው እንጂ ውጊያ ልግባ ብዬ ነበር” የማይካድራዋ እናት

199

ሁመራ: ጳጉሜን 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እናት ልዋጋ ካለች የመረረ ነገር ገጥሟታል፣ ከፍቷታል፣ ግፍ በዝቶባታል ማለት ነው። እናት ካልመረራት፣ እንስፍስፍ አንጀቷን የሚያስቆርጥ ነገር ካልገጠማት፣ ነፍጥ አንሱ፣ ሂዱና ተታኮሱ አትልም። ሀገር ስትደፈር፣ ልጆቿ መከራ ሲበዛባቸው፣ ችግርና ስቃይ ሲጠናባቸው የተመለከተች ቀን ትቆጣለች፣ ሂድ እና ተዋጋ፣ ለሀገር ፍቅር፣ ለሠንደቅህ ክብር ሙት ትላለች።

በሀገሯ ካልመጡባት፣ በማንነትና በክብሯ ካልተነሱባት፣ እርስትና እትብት እናሳጣሽ፣ ሀገር አልባ እናድርግሽ ካላሏት ተነሱ ተዋጉ አትልም። እርሷ የምትቆጣው የመረረ ነገር ሲገጥማት፣ ሠንደቋን ሲደፍሩባት፣ መከራውን ሲያበዙባት ነው።

ሮጠው ያልጠገቡ ልጆች፣ ነገን መኖር የሚናፍቁ ባለ ተስፋዎች ዘር እየተመረጠ መከራ ሲበዛባቸው፣ ደማቸው ሲፈስ፣ ምድሯ በስቃይ ስትመላ ተመልክተዋልና አብዝቶ ከፋቸው፣ የግፍ ብዛት አስመረራቸው። የማይካድራ ጎዳናዎች ደም ሲፈስስባቸው፣ አስከሬን በአስከሬን ሲጫጫንባቸው፣ የስቃይና የጣረሞት ድምፅ ሲበዛባቸው በእናት አንጀት ተመልክተዋልና ሀዘኑ ኃያል ኾነባቸው።

በደል ሳይገኝባቸው የሞቱት፣ በጅምላ የተቀበሩት፣ በወጉ ያላረፉት፣ ሩጫቸውን ያልጨረሱት፣ ነፃነት እና መልካም ዘመን ያላዩት ሰዎችን ሞት አይረሱትም፣ በደል የበዛባት፣ ስቃይ የበረከተባት፣ የስቃይ ድምፅ በየጎዳናው የተሰማባትን ቀን አይዘነጓትም። እናት መከራው ሲበዛባት፣ አክብራ ያስቀመጠችው ሲነካባት፣ ከበደል ላይ በደል ሲደራረብባት ያን ጊዜ ትቆርጣለች፣ ያን ጊዜ ትጨክናለች፣ የምትጨክነው ታዲያ የተቀደሰች ሀገሯን ለማስከበር፣ የተከበረች ሠንደቋን ላለማስደፈር፣ ልጆቿን በወግ ማዕረግ አሳምሮ ለማኖር ነው።

ሀገር በእናት ትመሰላለች፣ እናትም በሀገር ትከበራለች፣ እናት እውነት ናት፣ እናት መከበሪያ ፣ እናት መመኪያ፣ እናት መድመቂያ፣ እናት መዋቢያና ማበቢያ ናት። እናት ፈገግ ስትል የከበደው ቀን ይቀላል፣ የጨለመው ዘመን ይፈካል፣ አስቸጋሪው ቀን ይረሳል። እናትም ልጆቿ ፈገግ ሲሉ ትደሰታለች፣ ፈጣሪዋን ሳታቋርጥ ልጆቼን ባርክልኝ፣ ቀድስልኝ፣ ከፍ ከፍም አድርግልኝ እያለች ትማፀነዋለች፣ ኖሮ የሚያስከብራት፣ ስትደክም ምርኩዝ የሚኾናት፣ ሲከፋት የሚያፅናናት፣ ባረጀች ጊዜ የሚጠውራት፣ በሞትችም ጊዜ አልቅሶ የሚቀብራት ነውና ለልጇ ትሳሳለች፣ መልካም ነገር ሁሉ ይገጥመው ዘንድ ያለ ማቋረጥ ትፀልያለች፣ ያለ እረፍት ትማፀናለች።

ታዲያ ምርኩዝና ደጋፊዋን፣ ጧሪና ቀባሪዋን ግፈኞች ሲነኩባት፣ በግፍ ሲያሳጧት አብዝታ ታዝናለች፣ አብዝታ ትጨነቃለች። የሕወሓት የሽብር ቡድን በማይካድራ ከተማ ከበደል ላይ በደል ሲደራርብ ኖሯል፣ ከማይካድራ ለቅቆ ሲወጣ ደግሞ የበደሉን ሁሉ ጫፍ ፈፅሟል። ሰዎችን በገጀራ አንገታቸውን እየቆረጠ ገድሏል፣ በጅምላ ቀብሯል፣ ሕፃናትን ያለአሳዳጊ አስቀርቷል።

ይህ የሽብር ቡድን በኢትዮጵያ የትናንቱ ጠባሳ ሳይረሳ ለዳግም ወረራ ተነስቷል። በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣውን ወረራ የኢትዮጵያ ጀግንኖች በብቃት እየመከቱት ነው። ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንም ለሠራዊቱ አስተማማኝ ደጀን ኾነውታል።

የማይካድራ እናቶችም ለሠራዊቱ ደጀን ኾነውታል። በሽብር ቡድኑ ግፍ የተፈፀመባቸው የማይካድራ እናቶች ከዚህ በኋላ ዳግም ለመታረድ ቆሞ የሚጠብቅ የለም ነው ያሉት። ዳግም ማይካድራን የሚያያት የለም። ከሞት የተረፍን ሰዎች ነን። ለጠላት እጅ የሚሰጥ የለም። ጠላቶቻችን ቀብረን ብቻ ነው የምንተማመነው፣ በአንድነት ተነሰተናል ማንም አይነካንም። አካቢያችን አይረግጣትም ነው ያሉት። እናቶቹ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ለተሠማራው የጥምር ጦር አስተማማኝ ደጀን ኾነዋል። አይዟችሁ ልጆቻችን እያሉ ያበረታቷቸዋል።

ወይዘሮ አበባ ገዳሙ የማይካድራ ከተማ ነዋሪ ናቸው። እኒህ እናት ሀገራቸውን ለመታደግ ለሚዋደቁ ጀግኖች ሥንቅ እያዘጋጁ ያቀብላሉ። ለጀግናው ጥምር ጦር አይዟችሁ እያልን ስንቅ እናቀብላቸዋለን፣ የአሸባሪው ቡድን ሳምሪ ያደረገውን አንረሳም። ልጆቼን አይዟችሁ እላቸዋለሁ፣ አይደለም ንብረቴን ሕይወቴን ለመስጠት ወደኋላ አልልም ነው ያሉን። የአባቶቻችንን ታሪክ እናንተ ድገሙት፣ አደራ ልጆቼ እላቸዋለሁ ነው ያሉት።

የውጭ ወራሪ ሲመጣ ኢትዮጵያ ደቁሳ ነው የመለሰችው፣ አሁንም የመጣ ቢመጣ ትደቁሰዋለች፣ ጠላት በልጆቻችን ይደቆሳል ብለዋል። የሳምሪን ክፉ ሥራ ያየ ለዳግም ባርነት ወደኋላ አይልም። እኛ ለሞት ቀጠሮ ተይዞልን የነበርን ሰዎች ነን፣ ነገር ግን ጀግና ልጆቻችን ደርሰው ነው ያተረፉን፣ እነዚህን ሰዎች ልንረሳ አንችልም ነው ያሉን ወይዘሮ አበባ።

እንኳን አንገት እየተቆረጠ ሲጣል ያየን እኛ በቴሌቪዥን ያየው እንኳን አይረሳውም። እንዳይደገም ጀግኖቻችን አይዟችሁ እያልናቸው ነው፣ እስከመጨረሻው እንዋጋቸዋለን፣ አንቺ 60 ዓመት ኾኖሻል አትሄጅም ተብዬ ነው እንጂ ውጊያ ልግባ ብዬ ነበር። የእነሱ ግፍ አያስተኛም። ያለንን ሁሉ እንሰጣለን፣ የምንሰስተው ነገር የለም ብለውናል።

ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ እንዳወቅ ውለታው ጠላት እስኪጠፋ ድረስ ከጀግኖቻችን ጋር አንለያይም ነው ያሉት። ልጆቻችን በሀገራችን ላይ የተነሳውን ሲመክቱ እኛ እንከተላችኋለን ነው ያሏቸው። ለዓመታት በደል አድርሰውብናል፣ ማይካድራን ለቅቀው ሲወጡ፣ እናት ልጇን እያጠባች አርደዋል፣ ልጅ ከእናቱ ነጥለው ገለዋል፣ የሮጠውን በጥይት፣ የቆመውን በገጀራ አሰቃይተው ገድለዋል ነው ያሉት ወይዘሮ እንዳወቅ።

በጨለማ አሰቃይተውናል፣ አማራ መኾን ብቻ ለሞት ዳርጎናል፣ መታወቂያው እየታየ የአማራ ልጅ ተገድሏል፣ ዘሩ ተመርጦ ተሠቃይቷል ነው ያሉት። ይህን ያደረገን ቡድን እስከመጨረሻው እንታገላለን፣ መቼም ቢኾን አናስደርሰውም ብለውናል።

አሸባሪው ሕወሓት ይሄን ስቃይ ባደረሰበት ሕዝብ ላይ ነው ዳግም ለወረራ የተነሳው፣ ዳግም ለበደል ጠመንጃውን ያነሳው። ዳግም ለመውረር የሚቋምጠው። ኩሩ ሕዝብ ለጠላት እጁን አይሰጥም፣ ጀግና ሕዝብ ሀገሩን አያስደፍርም፣ ሠንደቁን አያስነካም፣ በቁጣ ይነሳል፣ በጀግንነት ጠላቱን ይመልሳል፣ በወኔ ተጉዞ በድል ይመለሳል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleዳያስፖራዎች አሸባሪው ህወሐትን የማውገዝ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያጠናክሩ አምባሳደሩ ጥሪ አቀረቡ።
Next article“ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሎቹ ግን ይጓዛሉ!”