
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም “ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከጥምር ጦሩ ጎን በመቆም የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብር መጠበቅ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው” ብለዋል።
አቶ ግዛቸው ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-
ሀገራችን ኢትዮጵያን ክብርና ታሪኳን ለማሳነስና ለማፍረስ በአሸባሪው ህወሓትና ግብረ አበሮቹ በአራቱም የሀገራችን ማዕዘን ጦርነት ከተከፈተብን ቆይቷል።
እንደ ሀገር በአንድነት ፀንተን፤ እንደ ሕዝብ በክብር በርትተን ለመኖር ብቸኛው መፍትሔ የጠላትን እቅድና ፍላጎት በስሜት ሳይሆን በስክነት አስቦ በአንድነት በመመከት ነው።
በጠላት አሉቧልታ መደናገርና መከፋፈል ሳያስፈልግ በአንድነት፣ በመተጋገዝ ለጋራ ሀገር በጋራ መቆም ወቅቱ የሚጠይቀው ታሪካዊና ሞራላዊ ኃላፊነት ነው።
በመሆኑም የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት እና የትኩረት ማዕከል የሆነች ኢትዮጵያን ትናንት በነበራት ከፍታ ልክ አይነኬ ሁና የገጠማትን አሁናዊ ፈተና በድል እንድትሻገር፣ በአሸባሪው ህወሓት የተቃጣብንን ወረራ በብቃት እየመከተ የሚገኘውን፣ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ጋሻና ጦር ሆኖ መከታ የኾነንን የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ጥምር ጦሩን መደገፍ ኃላፊነታችንን ከመወጣታችንም በላይ የግድ የሚለን ወቅት ላይ ነን።
ስለሆነም ላቡን እና ደሙን እያፈሰሰ፤ ለሀገር እና ለወገኑ በበጋ ፀሐይ፤ በክረምት ዝናብ እየተፈራረቀበት አቀበት ቁልቁለቱ ሳይበግረዉ ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት እየተናነቀ ውድ ሕይወቱን አስይዞ የሀገር ሉዓላዊነትን እየጠበቀ ለሚገኘው የኢትዮጵያዊ ጠባቂ ሠራዊታችን ድጋፍ ማድረግ እና ትክክለኛ ደጀን መሆን የዜግነት ትንሹ ግዴታ መሆኑን በውል በመረዳት ከሠራዊታችን ጎን በፅናት መቆም ይገባናል።
ከሠራዊታችን ጎን ደጀን ሆኖ መቆም ያልቻለ ኢትዮጵያዊ ሀገራችንን ሊያፈርሱ ዘወትር ነጋ ጠባ ከሚታትሩ ሀገር አፍራሽ የጠላት ኃይሎች ጋር ተባባሪ ከመሆን ተለይቶ አይታይም።
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J