
ህወሐት ከማዕከላዊው መንግስት ስልጣኑ በህዝብ ዓመፅ ተወግዶ ወደ ትግራይ ከሸሸ በኃላ እንደገና በኃይል ወደ ስልጣን ለመመለስ ያልቆፈረው ጉድጓድ ያልገለበጠው ድንጋይ የለም፡፡ የሃሰት ትርክቶችን በመፍጠር የትግራይን ህዝብ ከአጎራባች ክልል ወንድምና እህት ህዝቦችና ከመንግስት ጋር ቅራኔ ውስጥ ለማስገባት የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም ኖረዋል፡፡
ልዩ ሃይልን በከፍተኛ ቁጥር በማሰልጠንና የእብሪት ወታደራዊ ትርክቶችን በማሳየት ጦርነትን አበክሮ ቀስቅሰዋል፡፡ ብሎም በመንግስት ይቀርብለት የነበረውን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በመግፋትና የአገራችንን መከላከያ ሃይል ከጀርባ በመውጋት ፀረ ሰላምነቱን ብቻ ሳይሆን የአገር ከሃዲነቱንም ጭምር ለመላው ዓለም ግልፅ በሆነ ሁኔታ አሳይተዋል፡፡
ትዴፓ ህወሐት ይሰብከው የነበረን ጦርነት እንዲያቆም፣ ጦርነት ሊያስከትለው የሚችለውን ቀውስና እልቂት እየጠቆመ ሲያስጠነቅቀው ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ይህ እብሪተኛ ቡድን በተለይም የሰሜኑን እዛችን ወግቶ ከፍተኛ መጠን ያለው ትጥቅ ከታጠቀ በኃላ በከፍተኛ ትዕቢት ተሞልቶ ከመላው የአገር መከላከያ ሃይላችን፣ ከአማራና መላው የአገራችን ልዩ ሃይሎች ጋር ውጊያውን ቀጥሎበታል፡፡
ሆኖም ይህ ራሱ የለኮሰው እሳት ራሱን በላውና ከ17 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ እንዲንኮታኮት ሆነ፡፡ ነገር ግን
ስናስጠነቅቅ እንደነበርነው የመጀመሪያው የጦርነቱ ሰለባ የትግራይ ህዝብ ሆነ፡፡ ህወሐት የትግራይን ህዝብ የበቀል ድግስ ሲያዘጋጅለት ማይካድራ ላይ ዘር የለየ ጭፍጨፋ ፈፀመ፡፡ቀጥሎም በተለመደው የጦርነት ባህርይ ለሆነው የሰው እልቂት፣የመሰረተ ልማት ውድመት መፈናቀል፣የሴቶች መደፈርና ለሃብት ዝርፍያ ዳረገው፡፡
መንግስት ለስድስት ወራት ያክል ትግራይን ለማሰተዳደርና ለማረጋጋት ቢሞክርም ጦርነቱ ግን ሊቆም ባለመቻሉ ለፅሞና ጊዜ ብሎ ሰኔ 21,2013 ለቆ በመውጣት ተከታታይ የሰላም ጥሪዎችን ለህወሐት አቀረበ፡፡ በዚህ ወቅት ትዴፓ ዳግም የተገኘው የሰላም ጥሪና ከመንግስት በኩል የቀረበውን ዕድል ህወሐት ይቀበል ዘንድ አበክሮ አሳስበዋል፡፡
ጦርነቱን ወደ ክልሎች ለማሰፋት ያደርገው የነበረን ሙከራ ሁሉ ከጅምሩ አውግዘዋል፡፡ህወሐት ከሰላም ጋር ያለው ግንኙነት ሆድና ጀርባ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን በተለይም በጦርነቱ የበላይነት አግኝቻለሁ በሚል ስሜታዊነት ለሰላም ጥሪዎች ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ለ2ኛ ጊዜ አዲስ አበባን የመቆጣጠር ክተት አወጀ፡፡ ስልጣኑን ማስመለስ ካልቻለ ደግሞ አገራችንን ለመበታተን አልሞ የ13ና የ14 ዓመት ዕድሜ ህፃናትን ሳይቀር እያፈሰ አዘመተ፡፡
ይህ ከኃላው እየተገደለ የሚገፋው ታጣቂም ከፍተኛ የእውር ድንብር ጥፋቶችን እያደረሰ ደብረ ሲና ቢደርስም በደረሰበት አፀፋዊ እርምጃ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ለሞት አስረክቦ ተመልሶ በትግራይ የክልል አጥር እንዲኮራመት ተደረገ፡፡በየሜዳው ወድቆ የአሞራ ሲሳይ ከሆነው ወጣትና ህፃን በላይ አካላ ጎዶሎ ሆኖ የገባው ቁጥር ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ቁስሉ ሳይታከም በመቅረቱ ካለቀው ውጪ ድኖም የተረፈውን ሸሽቶ ማምለጥ የቻለውም ለከፍተኛ የሞራል ውድቀት ተዳርጎ አንገቱ የተሰበረ ሞራለ ቢስ ወጣት ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም እጅ ግን በደቀቀው የህወሐት አቅም ፊትም አልታጠፈም፡፡ከህወሐት አንፃር ግን አሁንም ከ500,000 በላይ ወጣት ጨርሶ፤ የቀረው ተዳክሞ ተስዶ ባለበት ሁኔታ፤ ህዝቡ በረሃብ፣ በመድሃኒት እጦት
እያለቀ እያለ የሰላም ጥሪዎችን ገፍቶ በፀላኤ ሰላምነቱ በመቀጠል ለ3ኛ ዙር ጦርነት በስፋት ሲዘጋጅ መቆየቱን አይተናል፡፡
ህወሐት የትግራይን ህዘብ አሁንም በከፍተኛ የማሰገደድ ጫና እንዲዘምት፣ እንዲዋጋ ለማድረግ በሚተጋበት ጊዜ መንግስት ግን ለህዝቡ የተገኘውን ያህል ሰላም በመመኘት ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር እንደሚፈልግ ለመላው
ዓለም ግልፅ በሆነበት መልኩ ገልፀዋል፡፡ ብዙ ርቀትም ተጉዞ ከድርሻው በላይ ቀርበዋል፡፡ ህወሐት ግን የሰላም ጥሪዎችን ከደካማነት ቁጥር በመቁጠር የሰላም ጥሪውን በጉልበታችን ያመጣነው ነው ብሎ ሲያጣጥለው ተስተውለዋል። ተቀባይነት የማይኖራቸው ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደርም ሰላም እንዳይሳካ ከማድረጉ በላይ ጦርነትን በመለኮስም የሰላምን በር ፈፅሞ እንዲዘጋ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡
ህወሐት ፀረ ሰላም መሆኑንና ለህዝብም ደንታ እንደሌለው፣ዘራፊና አሸባሪ ስለመሆኑም መላው ዓለም ተገንዝቦታል፡፡ስለዚህ ከህዝብና ከመላው የዓለም ማህበረሰብ እየተነጠለ መምጣቱ በግልፅ የሚታይ እውነት ነው፡፡
ጦርነቱን በጀመረ ዋዜማ በረሃብ ምክንያት በሞት አፋፍ ላይ ያሉትን ረሃብተኞች ላይ ለመድረስ ከዓለም ማህበረሰብ የተሰጠውን ከ570,000 ሊትር በላይ የሆነ ነዳጅ ከሚያጣጥሩት ረሃብተኞች አፍ መንጠቁ ከፍተኛ ውግዘት
ደርሶበታል።
ከዚህ በመነሳት ድርጅታችን የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(ትዴፓ)
👉 ህወሐት በህዝብና አገር ላይ የጀመረውን የሶስተኛ ጊዜ ጦርነት እጅግ ያወግዛል፣
👉 በዚህ ጦርነት ለሚደርሰው ጥፋት ሁሉ ተጠያቂው ህወሐት እንደሆነ ያምናል፣
👉 መንግስት አገርንና የህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚወስደውን እረምጃ ሁሉ ይደግፋል፣
👉 የአገራችንን ሰላም ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ ዳግም ያረጋግጣል፣
👉 መላው ኢትዮጵያዊ ህዝብ በዚህ አገርን የማስከበርና የህዝብን ደህንነት የማረጋገጥ እርምጃ ከመንግስት ጎን እንዲሰለፍ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
👉 በተለይም የትግራይ ህዝብ ህወሐት ጦርነትን እንዲያቆምና የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ ከመንግስት ጋር እንዲደራደር ለማድረግ፣ የልጆቹን ደም ይገታ ዘንድ በህወሐት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ እምቢታ እንዲቀሰቅስ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
👉 እንዲታጠቅ የተገደደውና ለግለሰቦች የስልጣንና የጥቅም ፍላጎት በማለቅ ላይ ያለው ወጣት ለወላጆቹ ሰላም፣ ለራሱም ነፃነት ጥቅምና እድገት በማሰብ በተመቸው መንገድ አፈሙዙን ወደ ጨቋኞቹ የህወሐት አመራሮች እንዲያዞር ወይም በሰላም እጁን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል እንዲሰጥ ጥሪያችንን እናቀርበለን እንመክራለን፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋእትነት ፀንታ ትኖራለች!!
ነሐሴ 27/2014 ዓ.ም