“ሀገራችንን እና ሕዝባችን በሕወሓት ከተጋረጠበት የጦርነት አደጋ ለመከላከል የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ማንኛውንም ሕጋዊ እርምጃ እንደግፋለን” የሰሜን አሜሪካ የሲቪክ ማኅበራት ሕብረት ጥምረት

207

ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን አሜሪካ የሲቪክ ማኅበራት ሕብረት ጥምረት በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም “ሀገራችንን እና ሕዝባችን በሕወሓት ከተጋረጠበት የጦርነት አደጋ ለመከላከል የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ማንኛውንም ሕጋዊ እርምጃ እንደግፋለን” ብሏል ጥምረቱ።
ከሰሜን አሜሪካ የሲቪክ ማኅበራት ሕብረት ጥምረት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል:-
የሕወሓት መራሹ መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለ27 ዓመታት የጫነው ኢፍትሐዊነት፤ ኢዴሞክራሲያዊነት፤ የከፋፍለህ ግዛና ወደር የለሽ ዘረፋ ያንግፈግፍው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ከሕግ በላይ መኖርን ድርጅታዊ ባህሉ ያደረገውን የፖለቲካ ቡድን ወደ ማይሸከመው ምዕራፍ በመድረሱ አሽቀንጥሮ መጣሉ ይታወቃል። ይህ አሸባሪ ቡድን የለውጥ ጎዳናውን በማደናቀፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከመረገጥ እና ከመዘረፍ የሚገታውን፣ ለሀገር ክብር አንድነት ቦታ የሚሰጠውን ለውጥ የማይቀበል መኾኑን በተግባር ሲያሳይ መቆየቱን ኹላችን የተረዳነዉ ጉዳይ ነው።
ሕወሓት ከዚህ የ“ለውጥ አልቅበልም ባይነት እና አደናቃፊነት” አልፎ ወደ ቀድሞ የበላይነት እመለሳለሁ በሚል ከንቱ ምኞት ተነሳስቶ ብቸኛ የሀገር እና የሕዝብ ጠባቂ የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ በማጥቃት ሀገሪቱን ለውጭ እና ለውስጥ አደጋ አጋልጧል፤ በአማራና በአፋር ክልሎችና ሕዝብ ላይም የዕብሪት ወረራ በመፈጸም ከባድ የዘር ጭፍጨፋ በማይካድራና አካባቢዋ አድርሷል፤ የትግራይን ክልል የጦር አውድማ በማድረግ ሕዝቡን ታሪክ ይቅር የማይለውን ክህደትና በደል ፈጽሞበታል።
ይህ ሐቅ ግልጽ ኾኖ ባለበት በአኹኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት “ጦርነት ይብቃን፤ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ ተነጋግረን ችግራችንን እንፍታ” በሚል እምነት ለሰላም ካለው ጥልቅ ጉጉት የተነሳ፤
1.ተኩስ ማቆሙን፤
2.የዚኽ ግጭት ጠንሳሾች እና ዋና ተዋናውያን መሪዎችን ከእስር ፈትቶ መልቀቁን፤
3.ሕወሓት ለተጎዳው ሕዝብ ከማደል ይልቅ እርዳታውን ለጦርነት ግብዓትነት እና የለመደውን ዘረፋ እንደሚፈጽምበት እየታውቀም ቢኾን የእርዳታ ምግብ እና ነዳጅ ያለ ችግር በብዛት እንዲገባ መድረጉን፤
4.ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሰየመውን የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሌሴጎን ኦቦሳንጆ በመቀበል ተደራዳሪዎችን መሰየሙን፤
5.የመከላከያ ሠራዊት፤ የአማራ እና የአፋር ክልልሎች የሕወሓትን ብዙ ፈታኝ ትንኮሳዎችን ለሰላም ሲባል እንዲታግሱ ማድረጉን፤ …. ወዘተ ወደጎን በመተው በአሁኑ ጊዜ፤ ሕወሓት ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት ጀምሯል፤ ለትግራይ ሕዝብ ከዓለም የሰላም ድርጅቶች እርዳታ የተላከውን እህል ማመላለሻ መኪናዎችን እዚያው በማስቅረት ለጦርነት ተጠቅሟል፤ የዕርዳታ ምግብ ማመላለሻ ነዳጆችን ዘርፏል፤ የዓለም አቀፍን የሰብዓዊ መብትና የጦርነት ድንጋጌን ሕግ በመጣስ ሕጻናትን ለጦርነት አሰልፏል፤ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሰየመውን የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ኦሌሴጎን ኦቦሳንጆ አልቀበልም በማለት አጠቃላይ የሰላም ሂደቱን ማደናቀፍ ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካ ሕብረት ያለውን ንቀት አሳይቷል፤ የኤርትራን መንግሥት እና ሕዝብ ለመውጋት እየዛተ ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ወንድሙ ከኾነው የአማራና የአፋር ሕዝብ ጋር ደም ለማቃባት የቻለውን ኹሉ እያደረገ ይገኛል።
የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር በሰላም የጋራ ሀገር መስርቶ ለሺህ ዓመታት እንዳልኖረ ኹሉ ትላንት ሀገርን እና ሕዝብን ለማጥፋት የተፈጠረው ይህ ድርጅት ለትግራይ ሕዝብ ብቸኛ የሰላም ዋስትና አድርጎ ራሱን በማቅረብ በድጋሜ ሕዝቡን ለረሃብ እና ለክፉ ጦርነት ዳርጓል።
አኹን ባለንበት ዓለምአቀፋዊ ሀገራዊ ነባራዊ ኹኔታ ሕወሓት ይህን ጦርነት ለሦስተኛ ዙር መጀመር የፈለገበት ምክንያት ቀደም ሲል ከተገለጸው በተጨማሪ “የአሜሪካ ዴሞክራት ፓርቲ መራሹ መንግሥት በውጪ ፖሊሲ ድክመቱ ምክንያት ዓለም አቀፍ ግጭቶች ተበራክቷል” የሚል የሪፐብሊካንን ጫና ለማስተንፈስ ደሃ ሀገር የኾነችው ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ የመጣልም ኾነ ሌላ ጫና የማድረግ ውስጣዊ የፖለቲካ ግፊት እንዲኖር በመፈለግ እንደሆነ ጭምር እናምናለን።
ስለኾነም፤
1.የኢትዮጵያ መንግሥት “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመነጋገር ሰላም የማስፈን” ጽኑ አቋሙ እንደተጠበቀ ኾኖ ሀገራችንን እና ሕዝባችንን በሕወሓት ከተጋረጠበት የጦርነት አደጋ በኃይል ለመከላከል የሚያደርገውን ማንኛውንም ሕጋዊ እርምጃ እንደግፋለን፤
2.የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና የአፋር ልዩ ኃይል ዛሬም እንደትላንቱ የሕወሓትን እኩይ ጦርነት ለመመከት በየግንባሩ እየከፈለ ያለውን መስዋእትነት በማድነቅ፣ በውጭ የምንኖር ዲያስፖራ አካላት ሙሉ ድጋፍ እንስጣለን፤
3.ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ የሰላም ድርድሩን እንዲመሩ በአፍሪካ ሕብረት የተሰየሙት ፕሬዚዳንት ኦሌሴጎን ኦቦሳንጆን እያደረጉ ላሉት ጥረት ሙሉ ድጋፍ እንሰጣለን፤ እኒህን አደራዳሪ ለመቀየር የሚደረግን ማንኛውንም ጫና በጥብቅ እንቃወማለን፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን አንድነቷና ሉዓላዊነቷ ሳይደፈር ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር የተጀመረው ለውጥ እንዲሳካ አኹንም ሙሉ ምኞታችንን እንገልጻለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ተከብራ እና ተፈርታ ለዘላለም ትኑር!!!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

Previous articleʺጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ፣ ወሎ ሙሉ አማራ፣ የጎበዝ ሀገር ነው ሞረሽ ብለህ ጥራ”
Next articleከትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የተሰጠ መግለጫ‼️