
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 9/2012 ዓ.ም (አብመድ)በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመራ ቡድን በሸዋ ሮቢት ከተማ ስለአካባቢው ሰላም ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ከሁለቱም አጎራባች አካባቢዎች የኅብረተሰብ ክፍሎችና በየደረጃው ያሉ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው፡፡
የውይይቱ ዓላማ በሰሜን ሸዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳድር አጎራባች አካባቢዎች እየተፈጠረ ላለው የሰላም እጦት መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦች እርስ በርስ የሚጋጩ ሳይሆኑ ለዘመናት ተቻችለውና በጋራ ሰርተዉ የኖሩ ናቸው ብለዋል፡፡
የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ መሪዎቹ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ገዱ በተለይም የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ለሰላም ታላቅ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያዬት ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ሕዝቦችን ለመነጣጠል ጥረት የሚያደርጉ ጥፋተኞችን አጋልጦ በመስጠት በኩል ኅብረተሰቡ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡
በሕዝቦች መካከል ጥላቻ የለም ያሉት ተሳታፊዎቹ የፖለቲካ ጥማቸውን ለመወጣት ሕዝቡን በማጋጨት ማትረፍ የሚፈልጉ አካላት ከድርጊታቸዉ ሊቆጠቡ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ
ፎቶ፦ የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳድር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት