
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲል የድሬዳዋ አስተዳደር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
አስተዳደሩ ያወጣው መግለጫ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለ27 ዓመታት የሀገሪቱን ማዕከላዊ ስልጣን ተቆጣጥሮ በነበረበት ጊዜ ከፈጸማቸው ኢሰብአዊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዋነኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የድሬዳዋ አስተዳደር ህዝብ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ቡድኑ የሀገሪቱ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ በነበረበት ዘመን የፍቅር፣ የመቻቻል እና የብሄር ብሔረሰቦች የአብሮነት መኖሪያ ትንሿ ኢትዮጵያ የሆነውን የድሬዳዋ አስተዳደር ህዝብ እርስ በእርስ እንዲጠራጠር እና እንዲጋጭ በማድረግ በማኅበረሰቡ መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በፍቅር መሀል ጥላቻን በመተማመን መሀል መጠራጠርን በአንድነት መሀል መከፋፈልን በበጎነት መሀል ክፋትን በሰላም መሀል ጦርነትን የሚዘራ ባጠቃላይ ከሰው ልጆች መሰረታዊ እና ሰዋዊ ባህሪ ያፈነገጠ ፀረ -ሰው ድርጊት የሚፈፅም መሰሪ ስብስብ ነው።
ከዚህም አልፎ ለርካሽ ፖለቲካ እና ለስልጣኑ ቀጣይነት ሲል ሴራ በመጎንጎን የስልጣኔ በር የፍቅር እና አብሮ መኖር ተምሳሌት የሆነችውን ድሬዳዋን ስምና ዝናዋን በማይመጥን ደረጃ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ማሽቆልቆል እዲፈጠርና አስተዳደሩ በልማት ወደ ኋላ እንዲቀር አድርጓል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እየተጋለበ በከፈተው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች የሚኖሩ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን ህይወት አጥፍቷል፤ በእድሜ ልክ ድካም የተከማቸ የሚሊዮኖችን ሀብትና ንብረትም በከንቱ አውድሟል።
የዚህ ባንዳ ቡድን ዋነኛ ሀሳብ ኢትዮጵያን እኔ ወይም የኔ ተላላኪ የሆነ ሀይል ካልመራት አፈርሳታለሁ የሚል ሲሆን ይህን በጤነኛ አዕምሮ ሊታሰብ የማይችል ከክፋት ሁሉ የከፋ ሀሳቡን ለማስፈፀምም ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት በመክፈት ምስኪን የደሀ ልጆችን በአደንዛዥ እፅ እያደነዘዘ ወደ እሳት እየማገደ ይገኛል።
ቡድኑ የያዘው እኩይ አላማ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ሰላም እና ልማት ፀር መሆኑን የሚገነዘበው የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት እና ህዝብ በምስራቅ በኩል የህወሓት አጋሮች በሆኑት እንደ አልሸባብ እና ሸኔ ባሉ የሽብር ቡድኖች የሚሞከሩ ሙከራዎችን በማክሸፍ እና በህወሓት ላይ በሚወሰደው እርምጃ እንደሁልጊዜው ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በአፅንኦት እየገለፀ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ያረጋግጣል፡፡
በመጨረሻም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ የጀመረውን ጦርነት አቁሞ በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል ተገቢውን ጫና እንዲያሳድር የድሬዳዋ አስተዳደት ጥሪውን ያቀርባል።
የድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር
ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም
ድሬዳዋ