የምዋጋው ኢትዮጵያ ሰላም ስለሚያስፈልጋት ነው!

173

ባሕር ዳር: ነሐሤ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ውጣ ውረዱ፣ መከራውና ፈተናው፣ ጽናቱና ታማኝነቱ ሁለነገሩ ኢትዮጵያን ይመስላል፡፡ በብዙ ይፈተናል፤ በማይታመን ብቃት አሸንፎ ብቅ ይላል፡፡ የኢትዮጵያን ጠላቶች በብርቱ ክንዱ ይደቁሳል፡፡ ፈተናዎቹን ሁሉ በእምነት እና በጽናት ይሻገራል፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፡፡
ወቅቱ ኅዳር ወር መጨረሻ አካባቢ 2012 ዓ.ም ቦታው ደግሞ የትግራይ ክልል ርእሰ መዲና መቀሌ፡፡ በወቅቱ መቀሌ መሽገው ሀገር እና ሕዝብ ሲያምሱ የነበሩት ጉምቱዎቹ የትህነግ ባለስልጣናት መቀሌን ለቀው እግሬ አውጭኝ ብለዋል፡፡ በምትኩ ከጀርባው ከተወጋ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጉዳቱን እና ውጋቱን ተቋቁሞና አገግሞ ጀብድ የሠራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መቀሌን በማይታመን ገድል ተቆጣጥሯል፡፡ መቀሌ በቀይ መለዮ ለባሾቹ መዳፍ ውስጥ ገብታ ጽሞና ይስተዋልባታል፡፡
ጥቅምት 24 እና በተከታታይ ባሉት ቀናት ትግራይን ከየትኛውም መገናኛ አውታሮች ለይቶ ግፍ እና በደል ሲፈጽም የነበረው ቡድን ሽንፈቱ የማይታመን ሆኖበታል፡፡ መከዳት የሚፈጥረው የአካል እና የሞራል ስብራት ጠሊቅ ቢሆንም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸውና ከዚያ ፈተና ወጥተው ለዳግም ግዳጅ የተዘጋጁት በርካቶች ነበሩ፡፡
በወቅቱ ከደረሰባቸው አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት በማገገም ላይ የሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ያሳለፉት ጊዜ ከባድ ቢሆንም ጽናታቸው ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ነገሮችን ቀለል አድርገው የሚመለከቱ አድርጓቸዋል፡፡ ምንም እንኳን አካባቢው የጦርነት ቀጣና ቢሆንም በቀድሞው ሰሜን ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ውስጥ ነገሮች እንደቀድሞው የአዘቦት ሆነው ቀጥለዋል፡፡
ፀሐይ ውሎዋን አገባዳ ወደ መግቢያዋ እየተሸኘች ስለሆነ ሞቃታማው አየር ደስ በሚል ነፋስ እየተተካ ነው፡፡ እረፍት ላይ ያሉት የሠራዊቱ አባላት በቡድን በቡድን ሆነው እየተንቀሳቀሱ ይነጋገራሉ፡፡ የተወሰኑት የሠራዊቱ አባላት ደግሞ ግቢው ውስጥ በሚገኝ የመረብ ኳስ ሜዳ ውስጥ ይጫዎታሉ፡፡ በዚህ መካከል ነበር አንድ እግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በክራንች እያነከሰ ንጹህ አየር ለመቀበል ሲንቀሳቀስ የነበረን ወታደር ያገኘሁት፡፡
ወታደር ቢሆንም ገራገር እና ትሁት ነው፡፡ ይህ ወታር እንኳን ሰዎቹ ግመሎቻቸው የኢትዮጵያን ሰንደቅ በርቀት ያውቁታል ከሚባልላቸው አፋሮች አብራክ የተገኘ ነው፡፡ አማርኛው ብዙ እንዲያዳምጡት ወዶ የሚያስገድድ አይነት ጣፋጭ እና ለዛ ያለው ነው፡፡ ሰላምታ ተቀያይረን ለብዙ ጊዜ እንደሚተዋወቅ ጓደኛሞች አድማሱን ከርቀት እያየን አብረን ቆመናል፡፡
ታሪኩ የወታደር ታሪክ ነው፡፡ አብዛኛው ወታደር ለሀገሩ ክብር፤ ለወገኑ ፍቅር እንደሚስተዋልበት ሁሉ እርሱም የሀገር ፍቅር ያለው ወታደር ነው፡፡ ውትድርናን ገና በወጣትነት እደሜ የተቀላቀለው ሙያ በመሆኑ ቢወደው እንኳን አይገርምም፡፡ ለሕዝብ ያለው ፍቅርም ከደረሰበት ግፍ እና መከራ በኋላ እንኳን አልደበዘዘም፡፡
ባሳለፈው አንድ ወር ውስጥ የደረሰበትን መከራ እና የተቋቋመውን ግፍ ሲናገር የትዕግስቱን እና የአርቆ አሳቢነቱን አድማስ መመልከት ቀላል ነው፡፡ ስለ ለበሰው ሬንጀር ሲል ደረቅ ዳቦ ተክልክሏል፡፡ ከ15 ዓመታት በላይ ስለማገልገሉ በማዕረግ ፋንታ እጅና እግሩ ተጠፍሮ ተደብድቧል፡፡ ከደመወዙ ቀንሶ ትምህርት ቤት ስለመገንባቱ እና የትግራይ አርሶ አደርን ሰብል ስለመሰብሰቡ የስድብ እና አስነዋሪ ዘለፋ ሰለባ ሆኗል፡፡
ከዚህ ሁሉ መከራ እና ውጣ ውረድ በኋላ ከደረሰበት ጉዳት ወጥቶ ሀገሩን በሙያው የሚታደግበትን ቀን ይጠባበቃል፡፡ “የምዋጋው ኢትዮጵያ ሰላም ስለሚያስፈልጋት ነው” አለኝ፡፡ ግራ ገባኝና ምን ማለት ነው? የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ሰላም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ነገር ግን አሸባሪው ትህነግ እያለ እንኳን ኢትዮጵያ ምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት እንኳን ሰላም አይኖራቸውም አለኝ፡፡ የዚያ ወታደር ትምቢታዊ ንግግር የገባኝ ዘግይቶ ነው፡፡ አዎ! አሸባሪው ትህነግ እያለ ኢትዮጵያ ፈጽሞ ሰላም አይኖራትም፡፡
ዓለም ሁሉ ሊያውቀው የሚገባው ነገር ቢኖር አሸባሪው ትህነግ ከሰላም የተጣላ እኩይ ድርጅት ስለመሆኑ ነው፡፡ አሸባሪው ትህነግ እንኳን ለቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወክየው ነበር ለሚለው የትግራይ ሕዝብ እንኳን ቅንጣት ታክል ኀላፊነት የሚሰማው ደርጅት አይደለም፡፡ አሸባሪው ትህነግ ኀላፊነት የሚሰማው ድርጅት ቢሆን ኖሮ ትምህርት ቤት መሄድ የሚገባቸውን ልጆች ወደ ግንባር አያሰልፍም ነበር፡፡
አሸባሪው ትህነግ ከራሱ የተጣላ፣ በትዕቢት የተወጠረ እና ስግብግብ የደም ነጋዴ ድርጅት መሆኑ ለኢትዮጵያዊያን ከተገለጠላቸው ውሎ አድሯል፡፡ ከስልጣን የመውረዱ ዋናው ምስጢርም የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸባሪው ትህነግን በሚገባ ማወቁ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሚጠበቀው ትልቅ ቁም ነገር ጠላቱን አምርሮ የሚጠላ ሕዝብ ማደራጀት ብቻ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀሪ የቤት ሥራ በመከራ ኢትዮጵያን የሚያጸናውን የመከላከያ ኃይል በጋራ ቆሞ በመደገፍ የኢትዮጵያን ትንሣዔ በአሸባሪው ትህነግ መቃብር ላይ ማጽናት ሊሆን ይገባል፡፡ መከላከያን ለመደገፍ በርካታ መንገዶች ቢኖሩም ትልቁ ድጋፍ ግን እርግጠኛ ያልሆኑበትን ጉዳይ ካለመናገር እና የጠላት ፕሮፖጋንዳ ሰለባ ካለመሆን ይጀምራል፡፡ ያኔ የመከላከያ ሠራዊቱ እውነተኛ ሥሪት እና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ይገለጻል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous article❝ቤቴ በረሃ ነው ጫካ ነው አዳሬ፣ ማን ደጄን ረግጦት መቼ ተደፍሬ❞
Next articleየኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን – የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር