
ነሐሴ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግና ካልከፋው አያጉረመርምም፣ አፈሙዙን አያዞርም፣ ጫካ ውሎ ጫካ አያድርም፣ ጀግናው ሰላም ሲኾን ያርሳል፣ ይነግዳል፣ ሰላም ሲታጣ ነፍጡን ከትራሱ ያነሳል፣ ሀገር ወደተደፈረችበት አቅጣጫ ይገሰግሳል፣ አልሞ ይተኩሳል፣ ምሽግ ይደረምሳል፣ ጠላቱን ይደመስሳል፣ ለእናት ሀገሩ ደም ያፈስሳል፣ አጥንት ይከሰክሳል፡፡
አትንኩኝ ሲል ሲነኩት፣ ተውኝ ሲል ሲገፉት ጀግናው ይቆጣል፣ መውዜሩን ወልውሎ፣ ሳንጃውን ስሎ ከቤቱ ይወጣል፣ በጫካ ውስጥ እያጉረመረመ ይቀመጣል፣ ከቤት ወጥቶ በጫካ የሚቀመጠው፣ በዱር በገደል እየተመላለሰ የሚያጉረመርመው አትንካኝ ሲለው የነካውን፣ ተወኝ ሲለው የገፋውን ድባቅ ለመምታት ነው፡፡
ሀገሩን ይወድዳታል፣ ከፍ ከፍም ያደርጋታል፣ በደሙ ያጸናታል፣ በአጥንቱ ያስከብራታል፣ በሞቱ ያኖራታል፡፡ ኢትዮጵያን ከነኩበት፣ ወሰኑን ከገፉበት፣ ክብሩን ከተዳፈሩበት ምቾትን ይረሳል፣ ቤቱን ይተዋል፣ ልጆቹን ጥሎ ጠላት ወደ መጣበት፣ ወሰን ወደተደፈረበት ይገሰግሳል፡፡
ምድሯ እልፍ ጀግና ይፈጠርባታል፣ እልፍ ደፋር ይወጣባታል፣ በጀግኖቿ ክንድ ተጠብቃ ኖራለች፣ በልጆቿ ጀግንነት ተከብራለች፣ ጠላቶቿን አስገብራለች፣ አንበርክካ ቀጥታለች፣ አዋርዳ መልሳለች፣ ከአፈር ጋር ቀላቅላቸዋለች፣ እንዳይመለሱ አድርጋ ሸኝታለች፡፡
በትዕቢት የገቡትን አስተንፍሳቸዋለች፣ በንቀት የመጡትን አንገታቸውን አስደፍታቸዋለች፣ በልጆቿ ጎራዴ ቀንጥሳቸዋለች፣ በልጆቿ አፈሙዝ ጥላቸዋለች፣ በሳንጃቸው ወግታቸዋለች፣ ያለ ጠላት ውላ ያደረችበት ዘመን አልተገኘም፡፡ አንደኛው ሲሸነፍ ሌላኛው እድሉን ሊሞክር ይነሳል፣ እርሱም ተሸንፎ ይመለሳል፣ እርሱም እንደቀደሙት አፈር ይለብሳል፡፡
ጀግኖች በሀገራቸው ሸለቆዎች፣ ሜዳና ተራራዎች እየተመላለሱ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ያስከብራሉ፣ ምሽግ ውለው ምሽግ እያደሩ ምድራቸውን ይጠብቃሉ፣ ወገናቸውን ያኮራሉ፣ ወራሪን ያሳፍራሉ፡፡ ዛሬም ሌላ ጠላት ተነስቷል፣ ዛሬም ጠላት በሀገርና በሕዝብ ላይ ጦርነት ከፍቷል፡፡ ጀግንነትን ከአባታቸው የወረሱት፣ አይደፈሬነትን መገለጫቸው ያደረጉት፣ አትንኩኝ የሚሉት፣ ጠላትን የሚያደቅቁት ጀግኖች በሀገርና በሕዝብ ላይ የተነሳውን እየመቱት፣ ክንዳቸውን እያሳረፉበት ነው፡፡ ተራራዎች እና ሸለቆዎች ጠላት እየወደቀባቸው፣ እየረገፈባቸው ነው፡፡
ክብርና የሀገር ፍቅር ጠንቅቀው ያወቁት፣ ጀግንነትን በደማቸው ያሰረጹት፣ ልበ ሙሉነትን ከአባቶቻቸው የተቀበሉት፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ለእናታቸው ፍቅር፣ ለኢትዮጵያውያን ክብር ሲሉ ሞትን ንቀዋል፣ ረሃብና ጥምን ረስተዋል፡፡ አንጥረው እየተኮሱ፣ በዱር በገደሉ ጠላትን እየደመሰሱ ነው፡፡ ሀገር በደም ነው የምትጸናው፣ ሀገር በአጥንት ነው የምትቆመው፣ ሀገር በመስዋእትነት ነው የምትረጋው፣ ሀገር በጀግንነት ነው የምትከበረው፣ ሀገር በጽናት ነው ከፍ ከፍ የምትለው፡፡
የትህነግ የሽብር ቡድን በመንጋ ወጥቷል፣ በሕዝብና በሀገር ላይ ተነስቷል፣ አዛውንትን ጧሪና ቀባሪ፣ ሕጻናትን አሳዳጊ እያሳጣቸው፣ ቀዬና መንደራቸውን እያፈረሰባቸው ነው፡፡ የሕዝባቸውን ሰቆቃ ያዩት፣ የሕዝባቸውን ስደትና እንግልት የተመለከቱት ጀግኖች እምብኝ ለሀገሬ ብለው ጠላትን ለመፋለም ተነስተዋል፡፡ ውሎና አዳራቸውን ጫካ ውስጥ አድርገዋል፤ ጠላታቸውን እየቀጡት ነው፡፡
❝ቤቴ በረሃ ነው ጫካ ነው አዳሬ፣
ማን ደጄን ረግጦት መቼ ተደፍሬ❞ ቤታቸው በረሃ ነው፣ ማደሪያቸው ጫካ ነው፣ ማን ይደፍራቸዋል፣ ማንስ ኾኖለት ያሸንፋቸዋል፣ በጋራውና በተራራው፣ በሜዳና በሸለቆው እየተመላለሱ ደጃቸውን ላለማስረገጥ፣ ተቅለብልቦ የገባውን፣ በእብሪት የመጣውን እያነጠፉት ነው፡፡
አንተ የአሸናፊዎች ልጅ ነኽ፣ አንተ የባለ ታሪኮች ዘር ነኽ፣ አንተ ከጀግኖች ምድር የተገኘህ ነኽ፣ እንኳን ወሬ ጦር የማይበግራቸው፣ ባሩድና ሀሩር የማይመልሳቸው፣ ማዕበል ኾነው የሚነሱ፣ አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት የሚተኩሱ ጀግኖች ልጅ ነኽ፡፡ አዳሬ ጫካ ነው፣ መኖሪያዬም በረሃ ነው፣ አትደፍሩኝም፣ አትነኩኝም በላቸው፣ ክብርኽን በክንድኽ አስከብር፣ ለነጻነትና ለአንድነት አብር፣ ተባበር፡፡
የሰው ወሰን አላለፍክም፣ የሰው ክብር አልነካኽም፣ ተነካኽ፣ ወሰንኽ ታለፈብህ እንጂ፡፡ ተነሱብህ እንጂ አልተነሳህባቸውም፣ ወጉኽ እንጂ አልወጋሃቸውም፣ እናትክን ደፈሯት፣ እህትክን አሰቃዩዋት፣ ልጅኽን ገደሏት እንጂ አልገደልክባቸውም፡፡ ተገፍተኽ እንዳልተገፋኽ፣ ተበድለኽ እንዳልተበደልክ፣ ተዘርፈኽ እንዳልተዘረፍክ፣ ሃብትና ንብረትኽ ወድሞ እንዳልወደመብኽ ዝም ያልከው ለሰላም ብለህ ነበር፡፡ አሁን ያ ቀርቷል፣ መገፋትኽ፣ መዘረፍኽ፣ ማዘንኽ ተረስቷል፣ የትናንቱ የሐዘን ድንኳን ሳይነሳ፣ ሌላ የሐዘን ድንኳን ሊያስጥሉህ፣ ወገኖችኽን በጅምላ ቀብረው ሊያሳዝኑኽ አሰፍስፈው ተነስተዋል፡፡ ተጠራርተው መጥተዋል፡፡
አንተም ከዳር ዳር ተጠራራ፣ አንድ ኾነኽ ተነስ፣ ጠላቶችኽን እንደለመዱት አሳፍረኽ መልስ፣ እምብኝ ያለውን በየጥሻው ደምስስ፡፡ የትህነግ የሽብር ቡድን ዳግም ወረራ በከፈተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖች ከሞቀ ቤታቸው፣ ከሚወዷት ቀያቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል፡፡ አስቀድሞ በሚያሰርጋቸውና በሚከፍላቸው ባንዳዎቹ አማካኝነት ደግሞ ያላደረገውን አደረኩ፣ ያልያዘውን ያዝኩ እያለ እያስወራ ነው፣ የሚያወሩትን አትስማቸው፣ የሚዋሹትን ታገላቸው፣ እየያዝክ ለሕግ አሳልፈኽ ስጣቸው፣ ቀዬና አድባርኽን ጥለኽ አትሰደድላቸው፡፡
አዲስ ዓመት በቀረበበት ፣ በግና ደሮው በሚገዛበት፣ ቤተ ዘመድ በሚጠያየቅበት፣ እናቶች ቤታቸውን በሚያሳምሩበት፣ ልጆች የአዲስ ዓመት እንቁጣጣሽ ይዘው በሚደሰቱበት፣ አባቶች ነጭ ለብሰው፣ ጭራቸውን እየነሰነሱ ልጆቻቸውን በሚመርቁበት በዚህ ወቅት ለስደት ተዳርገዋል፣ ከቀያቸው ርቀው ተሰደዋል፣ በዚያው የቀሩትም በሽብር ቡድኑ ጭካኔ ስቃይ ውስጥ ገብተዋል፡፡
የግልኽን ጉዳይ በጉያኽ ያዘው፣ በይደር ተወው፣ በአንድነት ተነስ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ለሚፈናቀሉት ድረስላቸው፣ በአዲስ ዓመት በስደት ለሚያሳልፉት አለኹ በላቸው፣ ተስፋ ላጡት ተስፋ ኹናቸው፣ የጨለመ ለመሰላቸው ብርሃን አሳያቸው፡፡ ጠላትን ቀጥተኽ ወደ ቀያቸው መልሳቸው፣ ኮርተኽ አኩራቸው፡፡ አንድ ከኾንክ አሸናፊው አንተ ነኽ፣ አንድ ከኾንክ ማንም አይደፍርኽም፣ ማንም አይችልኽም፡፡ አንድ ኾነኽ ተነስ፣ ወደ ድል ገስግስ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J