
👉”ቡድኑ የአልቫንያ ኮምኒዝምን ሲከተል በመቆየቱ ነጻ አውጭ ቡድን ነኝ እያለ ያምታታ ነበር”
ደብረ ማርቆስ፡ ነሐሴ 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከምስረታው ሀገር የማፍረስን ዓላማ ያነገበ እና እድሜ ልኩን ይህንን እኩይ ዓላማ ሲፈጽም እና ሲያስፈጽም የኖረ ቡድን ከቶስ እንዴት ሀገር መምራት የሚለው አዎንታዊ ምግባር ይቻለዋል? ስለ ሀገር ማሰብ ሳይቻለው ስለ ሕዝብ የሚያስብ ሞራሉንስ ከየት ያመጣዋል ? የአሸባሪው ትህነግን እኩይ ባህሪ ምንጭ ሲታሰብ እነዚህ ተጠየቆች ክሱት መሆናቸው ግድ ነው። ሰላም ሲሉት ጦርነት ፣ አንድነት ሲሉት መከፋፈል ፣ ፍቅር ሲሉት ጥላቻ ካለ ይህ እኩይ ባህሪው ከምን ተጠናወተው? ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ያነጋገራቸው በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ መኮንን አለኸኝ (ዶ.ር) አሸባሪው ትህነግ ከመጀመሪያው ሲጠነሰስ ተላላኪ፣ ባንዳ እና የራሱ ማንነት የሌለው ሆኖ መጠንሰሱን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
አሸባሪው ትህነግ ሲመሠረት ጀምሮ ኢትዮጵያን የመከፋፈል እኩይ ተልዕኮ እንዲፈጽም እና እንዲያስፈጽም በመሥራቾቹ የተሰጠው ቡድን እንደሆነ በተግባር ሲረጋግጥ መኖሩን አሁንም እያረጋገጠው መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ ፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ማብራሪያ አሸባሪው ትህነግ መንግሥት ኾኖ ሥልጣን የመያዝ ዕድል ቢያገኝም የተመሰረተበት የተላላኪነት ሚናውን ለመወጣት በሶሻሊዝም ስም ሀገር ለመበተን የሚመቹትን አማራጮች ወስዷል። ለዚህም ቡድኑ ጎጠኝነት፣ አድሎአዊነት፣ ጠባብነት፣ ትምክተኝነት እንዲሁም ከኔ በላይ ነጻ አውጭ የለም ብሎ ማሰብ ዋና ዋና መገለጫዎቹ ናቸው።
የሽብር ቡድኑ ሕገመንግሥቱን ጨምሮ ያጸደቃቸው ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎቹ ዘረኝነቱን እና ጠባብነቱን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል ምሁሩ።
በተለይ ቡድኑ ተላላኪነቱ ጎልቶ ከሚታይባቸው ሥራዎቹ መካከል የተበደሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ ብሎ ሌሎች እንዲያምኑ መወትወት እና ከእኔ በቀር ነጻ የሚያወጣቸው የለም የሚለው አመለካከቱ በትረ መንግሥቱ በእጁ በነበረበት ወቅት በሥፋት የሚያነሳቸው ማሳያዎቹ እንደነበሩ ዶክተር መኮንን አንስተዋል።
“ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ምክር ቤት ናት፤ በዚህ ምክር ቤት ደግሞ የጨቋኝ እና የተጨቋኝነት ትርክት አለ፤” ብሎ ሌሎችን በማሳመን እና ከዚህ የሀሰት ትርክት እራሱን በማግለል “አንድ ጨቋኝ ብሔር አለ። እሱ ደግሞ አማራ ነው። በትረ ሥልጣኑ ከእሱ እጅ ካልወጣ ሀገር አንድ ኾና አትቀጥልም።” በማለት ሌሎች በአማራ ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ እና የእርስ በእርስ ጦርነቶች እና መገፋፋቶች አይለው እንዲወጡ በማድረግም የሁሉም እጅ ወደ አንድ ብሔር እንዲቀሰር ማድረግ የቻለ እኩይ ቡድን መኾኑም ሊዘነጋ አይገባም ብለዋል መምህሩ።
ዶክተር መኮንን እንዳብራሩት ሽብርተኛው ትህነግ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከውጭ የቅጥረኝነት ሸቀጡን ተሸክሞ መጣ። በዚህም ቡድኑ ባለፉት 27 ዓመታት ብቻ ያገኘው እርዳታ ኢትዮጵያ በአንድ መቶ ዓመታት ካገኘችው እርዳታ ጋር ሲነጻጸር ከ10 እጥፍ በላይ ይኾናል ብለዋል።
ቡድኑ በተለይ የአልቫንያ ኮምኒዝምን ሲከተል በመቆየቱ “ነጻ አውጭ ቡድን ነኝ” እያለ ያምታታ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያን የመበታተን ሥራውንም ሕዝቦችን በዘር፣ በቋንቋ፣ በጎሳ የመበታተን ሥራውን ፈጸመ ። ከዚያም አንዳንድ የውጭ ሀገራት በምሥራቅ አፍሪካ በተለይ ኢትዮጵያን ለመበታተን ለነበራቸው ፍላጎት የጎላ ሚናን ተጫወተ። በዚህም ታይቶ የማይታወቅ እርዳታ ጎርፎለታል። እነዚህ ተግባራት ሲገመገሙ ቡድኑ ኢትዮጵያውያንን የማበልጸግ፣ የማሳደግ እና እንደ ሀገር የማሻገር ሳይኾን ጠባብነትን እና የቡድን አመለካከትን በማጉላት ሀገር በማፍረስ ሴራ የተጠመደ ቡድን እንደሆነ ገልጸዋል።
ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ሂደቶችን በመግፋት ወደ ጦርነት እና ጥፋት መግባቱ ከአሸባሪው ትህነግ የተጠነሰሰበት ዓላማ እና ባሕሪ አንጻር ብዙም የሚገርም አይደለም ባይ ናቸው ምሁሩ፡፡
ዶክተር መኮንን እንዳሉት ተደጋጋሚ የሠላም አማራጭ የቀረበለት ይህ ቡድን በባሕሪው ድርድር አይገባውም። ምክንያቱም ድርድር ከሁለቱም ወገን አውቆ የሚተውት ጥቅም አለ። የሽብር ቡድኑ ግን ይህን ሳይኾን አሸናፊ መባልን፣ መርጦ መውሰድን ወይም በችሮታ እንዲሠጠው የሚፈልግ የራሱን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ ቡድን በመኾኑ የሠላም አማራጭ አይመቸውም ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ የሚታወቀው አሸንፎ ሀገር ሲገዛ ሳይኾን በድርድር ሥም ጊዜ ሲገዛ እና ለዳግም ጥፋት እጁን ሲዘረጋ ብቻ ነው። ይሕ የጥፋት እጁ ዳግም እንዳይዘረጋ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ በማበር ሊለበልበው እና ዳግም የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆን ማድረግ አለበት ሲሉ ዶክተሩ አብራርተዋል።
በተዳከመ ኀይል ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይቻልም ያሉት ዶክተር መኮንን ዳግም ጦርነት ማወጅ የሚፈልገውን ለመውሠድ የተጠቀመበት ሥልት ነው ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ የሰላም አማራጭ አይቀበልም። የተመሰረተበት ዓላማ ይህን እንዲቀበል አያስገድደውም ብለዋል ዶክተር መኮንን።
እንደ ምሁሩ አስተያየት ለዚህ ቡድን ምኅረት አስፈላጊ አይደለም።
በየጊዜው የሚያገረሽ በሽታው ሕዝብ እያስገበረ፣ ንብረት እያወደመ እንዲኖር ሊፈቀድለት አይገባም። የአማራ፣ የአፋር ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የማያዳግም ክንዳቸውን ሊያሳዩት ይገባል። አባቶች ሀገር ለትውልድ ያስረከቡበት የአድዋ ታሪክ ዛሬም ሊደገም ይገባል፤ ትናንት አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተው የተመለሱ የጥፋት ቡድኖች እጣ ሊገጥመው ግድ ኾኗል።
በተጨማሪ ለዚሕ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ራስ ወዳድ ቡድን ባርነት ሊላቀቅ ይገባል ሲሉ ዶክተር መኮንን ተናግረዋል። ለዚህም “አንድነታችን ኀይላችን፤ ኀይላችን ነጻነታችንን ይሠጠናል እና ከመቼው ጊዜ በላይ አንድ መሆን አለብን” ብለዋል፡፡
ሀገርን ምሁሩ ለሌባ አሳልፎ የሚሠጥ ባለሀገር የለም ብለዋል። ሀገር ማለት እናት፣ እህት፣ ልጅ፣ ትዳር እና ሕይወት መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የሽብር ቡድኑ ኅልውና ዳግም እንዳያቆጠቁጥ ሕዝባዊ አደረጃጀቶች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ትህነግ ለዳግም ጥፋት እጁን እንዳይዘረጋ የክልልም ኾነ የፌዴራል መንግሥት በጥምረት የሚሠሩበት ጊዜ አሁን መኾኑን አመላክተዋል።
ለአሸባሪ እና እኩይ ቡድን ሲባል የትግራይ ሕዝብ ለዳግም ሞት ራሱን አሳልፎ መስጠት የለበትም፤ የጀመረውን እምቢተኝነት ማስቀጠል አለበት ሲሉ መክረዋል ዶክተር መኮንን። “ተስፋ ለሌለው ቡድን አንዋጋም፤ ትናንት ያሳየን ደስታ የተሠረቀ እንጅ ሠርቶ ያመጣው አይደለም፤ እኛ የምንታወቅ በጠንካራ የሥራ ባሕል እንጅ በሥርቆት እና በማጭበርበር አይደለም፤ አሸባሪው ትህነግ አይወክለንም፤ ነጻ ልንወጣ ይገባል” ሊለው እንደሚገባ መክረዋል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼